Get Mystery Box with random crypto!

ውዱ አያታችን ጀግናው አያታችን ቄስና ገበሬ፣ ሰርቶ የሚኖረው እርሻ አርሶ በበሬ። በቀኝ እጁ | የኔ ማስታወሻ✍🏾በኪያብ🦋

ውዱ አያታችን

ጀግናው አያታችን ቄስና ገበሬ፣
ሰርቶ የሚኖረው እርሻ አርሶ በበሬ።
በቀኝ እጁ መስቀል እርፍ ይዞ በግራ፣
ቀን ሙሉ ይውላል ሲባርክ ሲሰራ።
ማሰርና መፍታት በሰማይ በምድር፣
ስልጣነ ክህነትን ሰጥቶት እግዚአብሔር።
ሰው ሁሉ የሚለው ይባርኩኝ መምህሩ፣
እርሱ ብቻ ነበር ላገሩ ለደብሩ።
ውዱ አያታችን ምነው ቸኮልክብን፣
ፀሀይዋ ሳትገባ በጊዜ ሄድክብን።
አራምባና ቆቦ ሆነን ተለያይተን፣
አንተ እኛን ናፍቀህ እኛም ናፍቀን አንተን፣
ወይ አንተ መጥተህ ወይ እኛ መጥተን፣
ሳታየን ሳናይህ ቀረን ተመኝተን።
በጀግንነት ወኔ ሁሌ እንደፎከርክ፣
ክንዴን ሳልንተራስ እኔ ደሴ እያልክ፣
አንድ ቀን ሳንጦርህ እንዳው ድንገት ሄድክ።
እግዚአብሔር ፈቅዶልን ሀሳባችን ሞልቶ፣
እኛም ተመርቀን አባዬም ቤት ሰርቶ፣
እድሜ ሕዝቅያስን አምላክ ላንተ ሰቶ፣
ብታየን ምን ነበር መቃብር ተከፍቶ።
እንዲህ ሳንገናኝ ከሆነ ነገሩ፣
ሌላ ምንም አንል ይቅለልህ አፈሩ፣
መንግስተ ሰማይን ያውርስህ እግዜሩ።
በአብርሃም ይስሐቅ ደግሞም በያዕቆብ፣
በቅዱሳንና በፃድቃን አጠገብ፣
ቅድስት ነፍስህን ያሳርፋት ኪሩብ።


ለቄስ ደሴ ወልደተክሌ መታሰቢያ ግጥም

ከልጅ ልጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው
/ / ዓ/ም

@Jerrysisayyy