Get Mystery Box with random crypto!

አንድ ነጥብ ለአስተውሎት ~ በጣም ከምንሸወድባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ በእውቀት የሚበልጡንን መሻይ | Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)

አንድ ነጥብ ለአስተውሎት
~
በጣም ከምንሸወድባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ በእውቀት የሚበልጡንን መሻይኾች ልንጠቀምባቸው አለመቻላችን ነው። በሃገራችን የመንሃጅ ግንዛቤ በጣም የሳሳ እንደሆነ ማንም የማይክደው ሐቅ ነው። ይሄ ክፍተት ደግሞ ብዙ መሻይኾች ላይ ይጎላል። ለወቅታዊ ኪታቦችና ለኢንተርኔት የቀረበው ወጣት #አንፃራዊ በሆነ መልኩ ትንሽ ሻል የሚልበት ሁኔታ አለ። በንፅፅር ነው እያወራሁ ያለሁት። ትንሽ እውቀት የራሱ ብዙ ድክመት አለበትና የማንክደው ብዙ ጣጣ እያመጣብን ነው። ሌሎችን ችግሮች ለጊዜው ልተውና በተነሳሁበት ጉዳይ ላይ ያለውን ላንሳ። ድርቅና (ዒናድ) ሳይሆን የግንዛቤ ችግር ያለባቸውን መሻይኾች መቅረብ እንጂ መራቅ ለሁሉም አይበጅም። ይሄ ማግለልና መግፋት ለነሱም፣ ለኛም፣ ለቆምንለት አላማም፣ ለወገናችንም የሚበጅ አይደለም፡፡ እና ተውሒድና ሱናን መውደድ፣ የሱና ዑለማዎችን ማክበር፣ ለደሊል እጅ መስጠት ካሸተትንባቸው ክፍተቶችን ብናይ እንኳ ከመራቅ ይልቅ መቅረባችን ነው የሚያተርፈን።

1ኛ:- ለነሱም ውለታ መዋል ነው። እኛ ችላ ስንላቸው በሌሎች ይጠለፋሉ። ይሄ ከዚህ ቀደም በስፋት ተከስቷል። እኛ ስንርቃቸው የሌሎች ሲሳይ ሆነዋል። በራሳችን ላይ ጠላት አብዝተናል። ካለፈው ልንማር በቃ ልንል ይገባል፡፡
2ኛ:- ለሰፊው ህዝበ ሙስሊም፦ እነዚህ መሻይኾች ህዝብ ዘንድ የተሻለ ቦታ ስለሚኖራቸው የነሱ መጠንከር ለህዝብ ይተርፋል፡፡ እኛ ባግባቡ ካልቀረብናቸው ግን ሌሎች አካላት የሱናን ደዕዋ በጥላቻና በስጋት እንዲመለከቱ አድርገው ይሞሏቸዋል። ይሄ ደግሞ ዞሮ ዞሮ ዳፋው ለህዝብ ነው የሚተርፈው።
3ኛው:- ጥቅም ለራሳችን ነው፡፡ እኛ ትንሽዬ የመንሃጅ ግንዛቤ አለችን ማለት (ያውም ከኖረ) ከነሱ በእውቀት በለጥን ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ከነጭራሹ እውቀት አለን ማለትም አይደለም። እነሱ ዘንድ መንሃጅ ላይ የግንዛቤ ክፍተት መታየቱ እውቀት የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለሁለቱም ወገን የሚበጀው መቀራረቡ ነው። እነሱ ዘንድ ያለውን ክፍተት ከቻልን ኪታብ እየገዛንላቸው ፣ ካልሆነ እያዋስናቸው፣ የታላላቅ ዑለማዎችን ንግግር እያሰማናቸው፣ በአደብ እየተከራከርናቸው ለመሙላት መጣር አለብን። በተለይ ኪታብ መስጠት ያለው ዋጋ ቀላል አይደለምና በዚህ ላይ ልንረባረብ ይገባል። የኛን ጅህልና ደግሞ ቁጭ ብሎ በመማር መግፈፍ አለብን። ይህን ስናደርግ ለራሳችንም፣ ለመሻይኾቹም፣ ለወገናችንም ትልቅ ውለታ እንውላለን። ለደዕዋችን መፋፋትም ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡ የማወራው ከላይ እንደገለፅኩት ተውሒድና ሱናን መውደድ፣ የሱና ዑለማዎችን ማክበር፣ ለደሊል ራስን ዝቅ ማድረግ፣ ቅንነት ስለሚታይባቸው መሻይኾች ነው።
መቼም በርካታ መሻይኾችና ዱዓቶች ተሰውፍ እና ሌሎችም የተሳሳተ መስመር ውስጥ ከቆዩ በኋላ እንደተመለሱ ይታወቃል። ከአላህ በኋላ ለዚህ መመለሳቸው የተለያዩ ሰበቦች ይኖራሉ። ዛሬም እነዚህን ሰበቦች ችላ ልንላቸው አይገባም። ዛሬም ክፍተት ያለባቸው ሰዎች ሲገጥሙን በመወያየት፣ መረጃ በመለዋወጥ፣ በችግራቸው ከጎናቸው በመቆም ልናቀርባቸው ይገባል። አንተ ትላንት በተለያዩ መስመሮች ላይ አልፈህ መጥተህ ሌሎች ወደሱና እንዳይገቡ በር ለመከርቸም አትታገል። ያለፍክባቸውን አባጣ ጎባጣ መንገዶች መለስ ብለህ አስተውላቸው።
=

ግንቦት 28/2013

https://t.me/IbnuMunewor