Get Mystery Box with random crypto!

ቢራቢሮዎቹ ለምን ይሸሹኛል ??? !!! “ቢራቢሮዎችን በተከታተላችኋቸው ቁጥር ከእናንተ እየሸሹ ይ | የስብዕና ልህቀት

ቢራቢሮዎቹ ለምን ይሸሹኛል ??? !!!

“ቢራቢሮዎችን በተከታተላችኋቸው ቁጥር ከእናንተ እየሸሹ ይሄዳሉ፡፡ እነሱን መከታተል ትታችሁ ግሩም የሆነና የሚያምር የአትክልት ቦታ ብትሰሩ ግን ራሳቸው ወደ እናንተ ይመጣሉ” ይባላል፡፡ ይህ አባባል እኛ በጥብቅ ከምናሳድደውና ከምንከታተለው ይልቅ በበለጠ ሁኔታ ማንነታችን ሰዎችንና ሁኔታዎችን ወደ እኛ የመሳብ ኃይል እንዳለው ጠቋሚ ነው፡፡

ምናልባት በውስጣችን ያለውን፣ ምልከታ፣ ዝንባሌና የአጠያየቅ ሂደት ብንለውጥ በተከታተልናቸው ቁጥር እየራቁን ከሚሄዱ ሁኔታዎች እንተርፍና በተለወጠው ማንነታችን ለእኛ የሚመጥኑ ነገሮችን መሳብ እንጀምራለን፡፡

“ቢራቢዎሮዎቹ በተከታተልኳቸው ቁጥር ለምን ይርቁኛል?” የሚለው ጥያቄ፣ “እኔ ለቢራቢሮዎቹ አመቺ ሁኔታን ለምን አልፈጠርኩላቸውም?” በሚለው መቀየር የግድ ነው፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ . . . 

“ሰዎች ለምን ሁል ጊዜ ይህንና ያንን ነገር ያደርጉብኛል?” የሚለው ጥያቄ፣ “እኔው ራሴው ለምን ሰዎቹ ደጋግመው ያንን ነገር እንዲያደርጉብኝ እፈቅድላእለሁ?” ወደሚለው ይቀየርልን፡፡

“ሁል ጊዜ ለምን ጥሩ እድል አይገጥመኝም?” የሚለው ጥያቄ፣ “ማግኘት የምፈልገውን ነገር ለምን በርትቼ በመስራት አላመጣውም?” ወደሚለው ይቀየርልን፡፡

“ሁኔታዎቼ ለምን አይለወጡም?” የሚለው ጥያቄ፣ “ለምን እኔ በሁኔታዎቼ ላይ ያለኝን አመለካከት አልለውጥም?” ወደሚለው ይቀየርልን፡፡

“ሰዎች ለምን አይወዱኝም፣ ለምንስ አይፈልጉኝም?” የሚለው ጥያቄ፣ “ለምን እኔ የሚወደድና የሚፈለግ ማንነትና ባህሪይ አላዳብርም?” ወደሚለው ይቀየርልን፡፡

የቀረውን ራሳችሁን በመቀየር ሁኔታችሁን መቀየር የምትችሉባቸውን ሌሎች ሃሳቦች ጨምሩበትና ወደለውጥ!!!

ዶ/ር እዮብ ማሞ