Get Mystery Box with random crypto!

ተረኛው ጨባጭ! “አንድ ሰው ሕጻን ሆኖ ሲወለድ እጁን (መዳፉን) ጨብጦ ነው፤ አንድ ሰው ሸምግሎ | የስብዕና ልህቀት

ተረኛው ጨባጭ!

“አንድ ሰው ሕጻን ሆኖ ሲወለድ እጁን (መዳፉን) ጨብጦ ነው፤ አንድ ሰው ሸምግሎ ሲሞት ደግሞ እጁን (መዳፉን) ዘርግቶ ነው” ይላል ካልታወቀ ምንጭ የተቀዳ እውነተኛ አባባል፡፡

ለአንድ ሕጻን አንድን ነገር በእጁ አስይዛችሁት ካወቃችሁ ልጁ የያዘውን ነገር በቀላሉ እንደማይለቅ ትደርሱበታላችሁ፡፡ አንድ ሕጻን ልጅ እጁን ጨብጦ መወለዱ ሁሉን ለመያዝ፣ ሁሉን በእጁ ለማስገባትና ሁሉን ነገር በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ የመሞከሩ ምልክት ነው፡፡

አንድ ሰው ሸምግሎ ሲሞት እጁን ዘርግቶ መሞቱ ደግሞ ሁሉን አይቶት፣ ሞክሮት፣ ጨብጦና “የእኔ ነው” ብሎ በመጨረሻ ምንም ነገር የእርሱ እንዳልሆነና አንድ ቀን ሁሉም ነገር ከእርሱ ቁጥጥር ውጪ እንደሚሆን የመገንዘቡ ምልክት ነው፡፡  

እውነታው ይህ ነው፡- ተወልደን በልጅነት ባሳለፍንበት ወቅትና ሸምግለን ከዚህ አለም ወደመሰናበት በምንደርስበት ወቅት መካከል ባሉን እንደ ጥላ በሚያልፉት አመታቶቻችን መያዝና መቆጣጠር በምንችለውና በማንችለው መካከል መለየት አስፈላጊ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ነገ ሁሉንም ነገር ትተነው እንደምናልፍ በመገንዘብ ዘመናችንን እንዳናባክነው እናስተውል፡፡

እጅህ በገባው ነገር ደስተኛ ሁን፣ ለመልካም ነገር ተጠቀምበት፡፡ እጅህ ለማስገባት ያልቻልከውን ነገር ለማስገባት ሞክር፣ ነገር ግን ሁሉን ካልያዝኩ በማለት ዘመንህን አታስበላ፡፡

ለጊዜው ነው እንጂ ምንም ነገር በቋሚነት የአንተ አይደለም፡፡ የእኔ ነው ብለህ የምታስበው ሁሉ ለጊዜው በአደራ የተሰጠህ ነው፡፡ ዛሬ አንተ የምትኖርበትን ቤትና ትናንት መሬት የእኔ ነው ብሎ የሚኖርበት ሰው ነበር፡፡ ዛሬ ግን የአንተ ነው፡፡ ነገ ደግሞ ይህንን ስፍራ ሌላው ተረኛው ጨባጭ ይረከበዋል፡፡

ቁም ነገሩ ዛሬ በእጅህ ያለውን መልካም ነገር  የመልቀቂያህ ጊዜ እስከሚመጣ ድረስ ለመልካም ዓላማ የመጠቀምህ ጉዳይ መሆኑን ላስታውስህ፡፡

ዶክተር እዮብ ማሞ
@Human_Intelligence