Get Mystery Box with random crypto!

ሀገር ያጣ ሞት ደራሲ -ሄኖክ በቀለ 'አንዳንድ ታሪኮች ርእስ የላቸውም ተነግረው እንዳልተነገሩ | የስብዕና ልህቀት

ሀገር ያጣ ሞት
ደራሲ -ሄኖክ በቀለ

"አንዳንድ ታሪኮች ርእስ የላቸውም ተነግረው እንዳልተነገሩ ይረሳሉ። አንዳንድ ሰዎች አስታዋሽ የላቸውም —ኖረው እንዳልኖሩ ይቆጠራሉ። አንዳንድ ገድሎች አልተዘከሩም የባከኑ መሥዋዕትነቶች ይባላሉ። አንዳንድ ቅሌቶች ሰው ፊት አልታዩም እንዳልተፈጸሙ ሁሉ በጨለማ ውስጥ ይቀራሉ። አንዳንድ አወዳደቆች ከትዝብት ልብሳችንን አራግፈን እንቀጥላለን። አንዳንድ ሕዝቦች በወል ተረስተዋል ተጋርደዋል —ዙሪያውን ለመታሰቢያነት የቀረላቸው ምንም የለም። አንዳንድ ኮቴዎች በመረሳት ተጠቅተዋል —አንዳንድ ወኔዎች ለሞት ዳርገዋል። "

"ታሪክ የአሸናፊዎች መዋዕል ነው። ነገሥታት ከአፍ ከአፍ እየተቀለቡ ዘመን ሲሻገሩ ሕዝብ ግን ተረስቶ ባለበት ይቀራል። የሱሲንዮስ ጋሻ ጃግሬ ማን ይባላል? የሰሎሞን እቁባት ለሕይወቷ ምን አደረገች? ስሟ እንኳ አልተጻፈም። ሰሎሞን ሰባት መቶ እቁባት ቢኖረው የሰሎሞን ታሪክ ብቻ ነው —እነርሱ የታሪኩ ሟሟያ ብቻ ናቸው  ...እንደጊዜና ቦታ ያሉ የመተረኪያ አጥቆች። ዛሬ የቆምንበት ምድር ላይ ትላንት ማን ነበረ? ለነገሥታት “ዘራፍ!” ካለው ስንቱ ተረፈ?  ታሪክ መርጦ ያስታውሳል። አሸናፊ መሆን ያልቻሉት ለአጉል አሟሟት ይሯሯጣሉ። ምንም ያልሠሩት በጀግና ሰይፍ ላይ በመውደቅ ብቻ የሚታወሱ ሰማዕት ይሆናሉ። ሲኖሩ ሳይሆን ሲሞቱ ያወቅናቸው ለቁጥር ይታክታሉ። ለሞቱ ግድ የሌለው ሕዝብ “ከሞቴ አሟሟቴን” ይተርታል። “ወይ ግደልላት ወይ ሙትላት፣ የፈሪ ወዳጅ አታሰኛት!”ን ያንቋርራል —የምትወደው ሰው ከሞተባት በኋላ “የጀግና ወዳጅ” መባል ምን ይፈይድላታል?ይህ ሲደመር የምንኖርለት ዓላማ “ወይ መግደል፣ ወይ መሞት” ይሆናል። እናም ያስጨንቃል!!

መሪዎች በክፉም፣ በደጉም ከሰው አፍ ይውላሉ። “ከሕይወቴ የገዘፈ ዓላማ አለ” ብሎ የሚያስብ ነዋሪ በደምፍላትና በእልህ ተነሥቶ  ሁሉ የማይታወስ አጽም ለመሆን ይፈጥናል።"

ሀገር ያጣ ሞት
ገፅ 132

ይህን የመፅሀፍ ገፅ እያነበብኩ የሀገራችን ወቅታዊ ፓለቲካ ታወሰኝ ደራሲው የሚተርከው በሁለት መሳፍንቶች መካከል በተደረገ ጦርነት ህይወቱን ስላለፈ  የአንድ ወጣት ታሪክ ነው።

የዚህ ድርሰት አስገራሚው ታሪክ በሁለቱ መሳፍንት(ራስ አሊና ደጃፍ ውቤ) ጥጋብ ምክንያት በተደረገው ጦርነት ብዙ ህዝብ ካለቀ በኋላ በዛው እለት ሁለቱ መሳፍንቶች 
ፊት ለፊት ሲገናኙ ያደረጉት ንግግር ነው።

ገፅ 139

"ራስ ዐሊም፣ ደጃች ውቤም ቁጭ ብለው ማዘዝና የመኳንንትን ሕይወት መግፋት እንጂ መግቢያ፣ መውጫውን አብጠርጥረው የሚያውቁ ጎበዞች አልነበሩም። የፍርሃታቸውን ባመጣላቸው በኩል ሲፈረጥጡ አንድ ጠባብ መንገድ ፊት ለፊት ተጋጠሙ። መንገዷ ከአንድ ሰው ውጪ የማታሳልፍ ሆና ወይ መመለስ ወይ ገድሎ ማለፍ ግድ ሆነ። ሁለቱም ሲያምታቱና ሲያስመስሉ ኖሩ እንጂ የውጊያ ዕውቀትም ጀግንነትም የሌላቸው ስለነበሩ ጦርና ጋሻቸውን እንደሰበቁ ተፋጠው ቀሩ።

ቆይቶም ደጃች ውቤ
“ዐሊ እንደው ጥጋባችን እንጂ እኔና አንተ ደም መቃባት ነበረብን?” አሉ።

“ውቤ አንተ እምቢ! አልክ እንጂ እኔ መች ፈለግሁት? ባንዋለድም ዘመድ ነን። ወንድሜ ነህ!”

“ግዛት እንደሁ እኔም የእኔን፣ አንተም የአንተን እንደያዝን ጦራችንን አጠንክረን ካሣን መውጋት ሲገባን...”

“ሰይጣን ሰውሮብን እንጂ ሐሳብህ ሐሳቤ ነው!”

“በል አሁን በጀ በል! ሄደን ጦርነቱን እንፍታ።”

“እንዲያ” .....ሁለት ታሪኮች ተቃቅፈው ተሳሳሙ። እንደ ወዳጅ ተያይዘው ወደ ጦርነቱ ቦታ ጋለቡ።

ሽምጥ ጋልበው ሲደርሱ፤ ጦርነቱ አልቆ፤ ቦታው በሰው ሬሳ ተሞልቶ፤ አንዳንዱም ወድቆ ሲያጣጥር ደረሱ። ለሞቱ ወታደሮቻቸው በማዘንና በማልቀስ ፈንታም በሬሳው ላይ ወዲህና ወዲያ እየተመላለሱ ይስቁና ይቀላለዱ ገቡ።

“ይሄስ አንዴም የተኮሰ አይመስልም። ታቅፎት ተኝቷል።”

“ዐሊ ና እስቲ ወደዚህ ...ይህቺማ ሁለት እጇም፣ ሁለት እግሯም የለ! ባለጓጉንቸር ሳጥን መስላልሃለች።”

ሳጥን የመሰለው፤  ያ ጎበዝ ወጣት ደጃች ውቤን ከልቡ ይወደው የነበረ... የደጃች ውቤ መሰደብ ያንገበገበው የነበረ  ...ደሙ ተንዠቅዥቆ ያልሞተ ...የደጃች ውቤን ንግግር ሰምቶ ጸጥ ጭጭ አለ።

ምናልባትም ከመጨረሻው ህቅታ ጋር ነገሥታት ለሥልጣናቸው እንጂ ለሕዝቡ ግድ እንደሌላቸው እያሰበ፤ ከረፈደም ቢሆን እያብከነከነው ሄደ። “የት?” እንዳትሉ! ሰው ከሞተ ወዲህ መኖሪያውን ማን ያውቃል? ምናልባትም አብረውት የተከመሩት ብዙ ሺህ ሬሳዎች ካልሆኑ በቀር።

የእናቶች ለቅሶና ዋይታ ምድሩን አደበላለቀው። አንዳንድ ታሪኮች ርእስ የላቸውም የሞትህ ትንፋሽ በአንገትህ ሥር በሞቀህ ሰዓት የተገለጠልህን ስሕተት መቼ ታርመዋለህ? አንዳንድ ሰዎች ስም የላቸውም —ይህ ወጣት የጦርነት ታሪኩ አጥቅ ነው፤ የመተረኪያ አማሃይ፤ በምድር ፊት ስለፈሰሰው ደሙ ማን ግድ አለው? ....አንዳንድ ገድሎች አልተዘከሩም። አንዳንድ ቅሌቶች ሰው ፊት አልታዩም። ታሪክ የአሸናፊዎች መዋዕል ነው። በአሸናፊ ስም የሚወድቀውን ነፍስ ከእንስፍስፍ የእናት አንጀት በቀር ማንም አያስታውሰውም። ማንም!!"

.............

በኢትዮጵያ መንግስት እና በወያኔ መካከል የተደረገው ጦርነት ከብዙ ደም አፋሳሽ ግጭት በኋላ ጦርነቱ በሰላም ስምምነቱ መጠናቀቁ ይታወሳል። በሁለቱም ወገን ያሉ መሪዎች በየቦታው ተቃቅፈው ፎቶ መነሳት ላይ ይገኛሉ። በዚህ ጦርነት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፤ የነዚህ ሰዎች ታሪክ ግን ተረስቷል ፤ ሞታቸው ቁጥር ሆኖ አልፏል። ህይወታቸው ትርጉም ላለው ነገር እንዳለፈ ለመናገር እንኳን ያድግታል። የባከኑ መስዋዕቶች ሆኗል።ታሪክ የሚፅፈው የአሸናፊዎችን ገድል ብቻ ይሆናል።

“የጠገበ ሲያገሳው
ተግ ሲል ቀልቡን የነሳው
በመጨረሻ ጦርነት ያበቃል
ወታደሩ ያልቃል ንጉሥ ይታረቃል”

.......

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በአንዱ ፁሁፉ ላይ እንዲህ ይላል

"ለጊዜያዊ ይሁን ለዘለቄታ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል በፖለቲካ ውስጥ ብዙ አይነት ኢ-ሞራል የሆኑ ነገሮች እንደሚሰሩ ቢታውቅም፣ ባሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየታየ ያለው በየትኛውም መመዘኛ ዝቅጠቱን ማሳነስ የማንችለውን የመሰለ የፖለቲካ አመለካካትና ድርጊት ይታያል።

ጦርነት በሰላም እንዲቆም ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረስ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ   ይህ ሰላም ከኋላው የተሸከመውን  ከባድ የህዝብ ሰቆቃ የማይመጥን የፊት ገጽታ የሰውነት ቋንቋ እያሳዩ፣ ከወያኔ ሰዎች ጋር የነበረው ግጭት በአንድ ምሽት በስካር መንፈስ ዳንስ ቤት ውስጥ የተፈጠረ ችግር በሚመስል መልኩ፣ በሳቅና በፈገግታ የተሞላ ግንኙነት ምን ያህል በጦርነቱ የተጎዳውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ሊያስከፋ እንደሚችል ዞሮ ማሰብ አለመቻል የሰላም ስምምነቱ  ስሜት አልባ፣ ሃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች የተደረገ እንደነበር ማሳያ ነው።"

@Human_Intelligence
@Human_Intelligence