Get Mystery Box with random crypto!

“Books are the mirrors of the soul.”―Virginia Woolf ዛሬ ዛሬ ከሀ | የስብዕና ልህቀት

“Books are the mirrors of the soul.”―Virginia Woolf

<<ያም ያም እየተነሳ ፀሐፊ ነኝ ይላል፡፡ የሚታተመው መጽሐፍ ቢበዛ የሚረባው ግን ጥቂት ነው፡፡>> ዛሬ ዛሬ ከሀገሬ አንባቢዎች የምሰማው ቅሬታ ነው፡፡ በዚህ አባባል ውስጥ ድብቅ 'ጽሑፍና ጸሐፊ'ን ማግነን አለች፡፡ 'ያም ያም' ፀሐፊ መሆን ካልቻለ 'ፀሐፊ' መሆን ያለበት ምን አይነት ሰው ነው? የታተመው ሁሉ ጥሩ መጽሐፍ ካልሆነ 'ጥሩ መጽሐፍ' ምን አይነት ነው?
ሀገራችን በጽሑፍ ቀደምት ነን የሚሉ ሊቆች ቢኖሯትም፤ ጸሐፊ የሚከበርባት ሀገር ግን አይደለችም፡፡ በተለይ የፈጠራ ፀሐፍት እንደ ወፈፌና ጸረ-ሀገር ነው የሚታዩባት፡፡ ሥለዚህም የፈጠራ ጽሑፍ ይዘው ወደ መጽሐፍ ገበያ ከሚወጡት ውስጥ ሥሟን ያገነኑ፣ ቅዱስነቷን የመሰከሩ እንጅ ጉድፏን የነቀሱ፣ እንከኗን ያወሱ፣ አውስተውም ይታረም ያሉ አይነበቡም፡፡

ስሻ ወደ መጽሐፍ ገበያ ዘወር ዘወር እላለሁ፡፡ ሻጭ ወዳጆቼ ጋርም ተቀምጨ የገዥውን የንባብ ትኩረት ለማየት እሞክራለሁ፡፡ በብዛት የሚጠየቁና የሚሸጡትን እያሰብኩ 'እነዚህ መጻሕፍት አንባቢው ላይ የሚጨምሩለት ምን ነገር አላቸው?' ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ አብዛኞቹ ከማኅበራዊ ሚዲያ የተሻለ መረጃ የማይሰጡ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ ቢያንስ መንፈሳዊ አገልግሎት አላቸው፡፡ ለማሰብ የሚሆኑት ወይም ምናብን የሚያነቁት ግን በቀን ውስጥ ላይጠየቁ ይችላሉ፡፡ ይህን እያሰብ መልሼ ሌላ ጥያቅ እጠይቃለሁ 'ሰው የሚያነበው ለምንድን ነው?' ብዬ፡፡ ምክንያታችን ልዩ ልዩ ሊሆን ይችላል፡፡ የተሻለው መልስ ግን 'የተሻለ ሰው' ለመሆን የሚለው ይመስለኛል፡፡ ያላወቁትን ማወቅ፣ ያልደረሱበት ላይ መድረስ፡፡ 'ማንበብ ጎደሎ ያደርጋል' ማለትም ለተሻለ ንባብና እውቀት ፍለጋ ያነሳሳል ማለት ይመስለኛል፡፡ ጥያቄው 'አውቀን ለምን?' የሚለው ነው፡፡ ሰው ነንና ኹልጊዜም በመሰራት ሂደት ላይ ነንና፤ ድክመታችንን ለመለየት፣ ያነሰንን ለማወቅ፣ ያላሰብነውን ለማሰብ ከሁሉም አስቀድሞ ደግሞ 'ማሰብ'ን ለማወቅ የተደራጀ፣ የተሰደረ ነገር ያስፈልገናል፡፡ በእኔ ቤት ይህ ነገር መጽሐፍ ነው፡፡ ማሰብ የሚያስለምድ መጽሐፍ፡፡ ማሰብ የሚያስለምድ እንጅ በእሱ መንገድ የሚያሳስብ አላልኩም፡፡
“Come to the book as you would come to an unexplored land. Come without a map. Explore it and draw your own map.” – እንዲል Stephen King

ማሰብ ሰው የመሆን ሂደትን የማወቅ ሂደት ነው፡፡ ሰው መሆን ዲበአካላዊና ህላዌያዊ ጥያቄዎች የሚነሱበት ነው፡፡ ከየት መጣሁ ወዴት እሄዳለሁ? ለምንና እንዴት ነው የምኖረው? መኖሬ የመወለድ ጣጣ ነው ወይስ ዓላማና ትርጉም አለው? ሕይወት ምንድን ናት? ፍቅር፣ ሐዘን፣ ደስታ፣ናፍቆት፣ ጥላቻ፣ ወሲብ ምንድን ናቸው? የሰው ልጅ ምናብና የፈጠራ አቅም እስከ የት ነው? ተፈጥሮ ምንድን ናት፣ እንዴትስ ነው የምትሰራው? እኔን ከተቀረው ተፈጥሮ ጋር ምን ያገናኝ፣ያስተሳስረኛል? ግለሰብ እና ማኅበረሰብ ምንድን ናቸው፣ ምንና ምን ናቸው? ኃይማኖት ምንድን ናት? መንፈስ እና ነፍስ የሚባሉ ነገሮች አሉ የሉም? እውነት ምንድን ናት? ሀሰትስ? ተፈጥሮ ፈጣሪ አላት? እንዴትና በምን ሁኔታ ወደ ህላዌ መጣን?
የሰው ልጅ የህልውና ታሪክ ምን ይመስላል? ከየት ተነስቶ የት ደረሰ? መድረሻውስ የት ነው?
እኒህና መሰል ጥያቄዎች የማሰብ ሂደትን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በማሰብና በማሰቢያ አካላችን መካከልም አንዳች ተኣምራዊ መስተጋብር መኖሩም ይገባናል፡፡ በርግጥ እነዚህ ነገሮች እያሰብኳቸው ያለሁት ማሰቢያ አካሉ ሥላለኝ ነው ወይስ ቀድሞ ታስቦና ታቅዶበት የተዘጋጀልን ነው? ብለው እንዲጠይቁም ይረዳል፡፡

እዚህ ለመድረስ ደግሞ ግብዓት ያስፈልገናል፡፡ ግብዓቶቹ ከሥሜት አካላትና ከህይወት ልምድ የሚገኙ ናቸው፡፡ እንደ ኤምፔሪስስቶች ገለፃ፤ እኛም በኑሮ እንደሚገባን፡፡ መጻሕፍት ደግሞ ላቅ ያሉት የግብዓት ምንጭ፡፡ መጻሕፍት የሰው ልጅ የማሰብ ጉዞ (Evolution of mind) ሰነድም ናቸው፡፡ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ የሚነግሩን፡፡ መጻሕፍታችንን አይተን እንደ ሀገር የማሰብ ጉዟችንን መገምገም እንችላለን፡፡ ምናልባት ጥንታዊ የኃይማኖት መዛግብትን ጠቅሰን እንፎክር ካላልን የእኛ የሚያኮራ አይደለም፡፡ ስለማያኮራም መሸሸጊያ ፍለጋ ታሪክ እንጠቅሳለን፡፡ መጻሕፍት የነፍስ መስታዎት ናቸው እንዳለች ውልፍ፡፡ የእኛ የአሁን የገበያ ላይ መጻሕፍትም የነፍሳችን መስታዎቶች ናቸው፡፡ እነሱን አይተን ራሳችንን ማወቅ እንችላለን፡፡ አንዳች ረብ ከሌላቸው እኛም እንዲያ ብንሆን ነው፡፡ 

“Reading furnishes the mind only with materials of knowledge; it is thinking that makes what we read ours.” – ይላልና ሊቁ John Locke
[... ናትናኤል ዳኛው...]