Get Mystery Box with random crypto!

የእስረኞቹ እንቆቅልሽ አንተ እና ጓደኛህ በአንድ ወንጀል ተጠርጥራችሁ ታሰራችሁ፡፡ ሆኖም መርማሪ | የስብዕና ልህቀት

የእስረኞቹ እንቆቅልሽ

አንተ እና ጓደኛህ በአንድ ወንጀል ተጠርጥራችሁ ታሰራችሁ፡፡ ሆኖም መርማሪ ፖሊሶቹ ምንም አይነት ማስረጃ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ እናም ሁለታችሁም በተለያየ ክፍል እንድትሆኑ ተደረገ። መርማሪዎቹም ለየብቻችሁ ያሉትን አማራጮች አቀረቡላችሁ።


አማራጭ አንድ - አንተ ከተባበርክ እና ወንጀላችሁን ከተናዘዝክ ነገር ግን ጓደኛህ ዝም ካለ አንተን በነጻ እንለቅሃለን እርሱ ግን
አስራ አምስት አመታት ይታሰራል፡፡

አማራጭ ሁለት - ጓደኛህ ወንጀላችሁን ከተናዘዘ ነገር ግን አንተ ዝም ካልክ፣ እርሱ በነጻ ይለቀቃል... አንተ አስራ አምስት አመታትን ትታሰራለህ።

አማራጭ ሶስት- ጓደኛህም አንተም ከተባበራችሁን ሁለታችሁም አምስት አመታትን ትታሰራላችሁ፡፡

አማራጭ አራት- አንተም ጓደኛህም ካልተናዘዛችሁ፤ ሁለታችሁም ቀላል የሆነ የአንድ አመት እስራት ትታሰራላችሁ።

በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ብትሆን ምን ታደርጋለህ?
መናዘዝህ የተሻለ ውጤትን የሚያስገኝ ይመስላል፤ ጓደኛህን ብትከዳውና ብትናዘዝ  የሚገጥምህ በነጻ የመለቀቅ ዕድል ነው᎓᎓በተቃራኒው ዝም ብትልና ባትናዘዝ፣ የአንድ አመት ወይም የአስራ አምስት አመት እስራት ይጠብቅሃል።

ሆኖም አንተ ነጻ ሁነህ ጓደኛህ አስራ አምስት አመታትን በእስር ቤት ሲማቅቅ ማየት ምን አይነት ስሜት ይፈጥርብሃል?

እናም ይህ እንቆቅልሽ የሚያስነሳው መሰረታዊ ጥያቄ “እንደ ማህበረሰብ ማሰብ” ወይስ “እንደ ግለሰብ ማሰብ” የሚል ይሆናል። ለሁላችንም የተሻለ አማራጭ የሚሆነው እንደ ማህበረሰብ ማሰብ ነው፤ ሆኖም ሌላኛው ሰው ምን እንደሚያስብ አናውቅምና ለራሳችን
መልካም የሚሆነውን ለማድረግ ስንል ራስ ወዳድ እንሆናለን፡፡ እኔ እንኳ ባልስርቅ ሌላው ይሰርቃል የሚል ሃሳብ ይፈጠራል። ይህ አስተሳሰብም በድሃ አገራት ላለው የሙስና እና ስርዓት አልበኝነት አንዱ ምክንያት ነው፡፡

ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አሳ የሚሰገርበት ሃይቅ አለ ብለን እናስብ። አሳ አስጋሪዎች በዚህ ሃይቅ ውስጥ ያሉት አሳዎች በራስ ወዳድነት ያለ ልክ የሚያጠምዱ ከሆነ፣ የአሳዎቹ ቁጥር ተመናምኖ በአንድ አመት ውስጥ ሃይቁ አሳ አልባ ይሆናል። ሆኖም ግን አግባብ ባለው ሁኔታ በልክ እና በመጠን የሚያሰግሩ ከሆነ፣ የአሳዎቹ ቁጥር አይመናመንም፤ እንዲያውም ከአመት ወደ አመት የሚያገኙት የአሳ ቁጥር እየጨመረ ይመጣል።

እዚህ ላይ ዋነኛ ጥያቄው መተማመን የሚለው ነው፡፡ አሳ አስጋሪዎቹ በመጠን ሊያሰግሩ ቢስማሙም አንዳቸው ሌላኛውን እስካላመኑ ድረስ ስምምነታቸው ዋጋ አይኖረውም፡፡ ልክ በሁለት ክፍሎች ውስጥ ለብቻቸው ተቀምጠው እንዳሉ እስረኞችም ይሆናሉ፡፡

ምንጭ- ፍልስፍና ከዘርዓ እስከ ሶቅራጠስ
ዝግጅት-ፍሉይ አለም

@Zephilosophy
@Zephilosophy