Get Mystery Box with random crypto!

ከአሉታዊው ዑደት ወደ አዎንታዊው ዑደት! ራስን መግዛት፣ መቆጣጠርና ዲሲፕሊንን ማዳበር ከሚሰጡን | የስብዕና ልህቀት

ከአሉታዊው ዑደት ወደ አዎንታዊው ዑደት!

ራስን መግዛት፣ መቆጣጠርና ዲሲፕሊንን ማዳበር ከሚሰጡን ጥቅሞች ሁሉ እጅግ የላቀው ጥቅም በራሳችን ላይ ያለንን አመለካከት የማስተካከል ጥቅም ነው፡፡ ላብራራው፡፡

አንድን ማድረግ እንደማይገባን የምናውቀውን ነገር የማድረግ ምርጫ ፊታችን ሲመጣ እና ራሳችንን በመግዛት ላለማድረግ ስንወስን ነገሩን በማድረጋችን ምክንያት ከሚመጣው አደገኛ ውጤት ራሳችንን እንደምንጠብቅ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም፣ ከዚያ በላቀ ሁኔታ የምናገኘው ትልቁ ጥቅም ለራሳችን ያለን ክብር የመጨመሩና በራሳችን ላይ ያለን አመለካከት ከፍ የማለቱ ጉዳይ ነው፡፡

አንድን ማድረግ የሚገባንን ተገቢ ነገር ለማድረግ ስናስብ ምንም እንኳን በወቅቱ የወረደው ስሜታችን ባይፈቅድልንም ራሳችንን በመቆጣጠርና በማዘዝ ለማድረግ ስንወስንና ስናደርገው ነገሩን በማድረጋችን ምክንያት የሚመጣውን ጥቅም ማግኘታችን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም፣ ከዚያ በላቀ ሁኔታ የምናገኘው ትልቁ ጥቅም የዲሲፕሊን ሰው መሆናችንን ከማወቃችን የሚመጣው የራስ-በራስ ምልከታ ከፍ የማለቱ ጉዳይ ነው፡፡

ብዙ ሰዎችን የያዘው ዑደት ይህንን ይመስላል፡- ከጤና-ቢስ ነገር ለመቆጠብ ራሳቸውን ስለማይገዙና ጥሩ ነገርን ለማድረግ ዲሲፕሊኑን ስላላዳበሩት በራሳቸው ላይ ያላቸው አመለካከት እጅግ የወረደና በዝቅተኛነት ስሜት የተመታ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በራሳቸው ላይ ያላቸው አመለካከት እጅግ የወረደ ሲሆን ራሳቸውን ስለሚጥሉ ራስን ለመግዛትም ሆነ ለዲሲፕሊን ያላቸው ተነሳሽነት የወረደ ይሆናል፡፡ ይህንን ዑደት አሉታዊ ዑደት እንለዋለን፡፡

ማድረግ የማይገባቸውን ያለማድረግ ራስን መግዛትና ማድረግ የሚገባቸውን የማድረግ ዲሲፕሊን የሚለማመዱ ሰዎች ደግሞ በስኬት ዑደት ውስጥ ራሳቸውን ያገኙታል፡፡ በሕብረተሰቡ መካከል ዘላቂ ስኬት ውስጥ የሚታዩ ሰዎች የዚህ ስኬታማ ዑደት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ይህንን ዑደት አዎንታዊ ዑደት እንለዋለን፡፡

የዛሬ ውሳኔያችሁና አጀንዳችሁ ከአሉታዊው ዑደት ወደ አዎንታዊው ዑደት የመሸጋገር ይሁንላችሁ! 

ዶ/ር እዮብ ማሞ
@Human_Intelligence