Get Mystery Box with random crypto!

የብሔር ማንነት ቅዠት-2 ሰው ሁሉ ከተጸነሰበት ቀን አንስቶ አንድ ብሎ ለመሞትና ለመኖርም ጊዜውን | የስብዕና ልህቀት

የብሔር ማንነት ቅዠት-2

ሰው ሁሉ ከተጸነሰበት ቀን አንስቶ አንድ ብሎ ለመሞትና ለመኖርም ጊዜውን መቁጠር ይጀምራል፡፡ ሰው ከመጸነሱና ከመወለዱ ጀምሮ ምንም አይነት የብሄር” ይሁን የሃይማኖት ማንነት እንዲሁም ባህል የሚባልና ቋንቋም የለውም፡፡ በነጻ አዕምሮ ራቁቱን ይወለዳል፡፡ ነገር ግን ወላጆቻቸው እየኖሩ ያሉትን የኑሮ ደረጃና አስተሳሰብ በልጆቻቸው አዕምሮ ውስጥ እየጫኑባቸው ያሳድጓቸዋል፡፡ የሰው ሁሉ ደምና ዘረመል “ብሄር” የለውም፡፡ ሁሉም ሰው ደሙም ቢሆን ከአራት የደም አይነቶች (ኤ፣ ቢ፣ ኤቢ፣ ኦ) አንዱ ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ አሜሪካዊ ሰው ያለው የደም አይነት እንዲሁ አንድ ኢትዮጵያዊ ሊኖረው ይችላል፡፡ ምናልባት ከእናትና ከአባት የሚወረስ ነገዳዊ ዘረመል እንኳ በትውልዶች እየሳሳ በመሄድ በሂደት የሚጠፋ ነው፡፡
ስለሆነም አንድ ጊዜ ምናልባት ወደአስራሁለት ዓመት ገደማ ሊሆን ይችላል፡፡ በቢቢሲ ዜና፣ ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ ንጹህ ነጭ ሰሜን አሜሪካዊ የሚባል ዘረመል ሊጠፋ እንደሚችል የሳይንስ ተመራማሪዎች ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አሁንም የሚሳያው በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የዓለም ሀገራት መናኸሪያ በመሆናቸው ይህን ግምት መቀበል አስቸጋሪ አይደለም፡፡

ወላጆች ልጆችን ወልደው ካሳደጉ በኋላ ማንን አግበተውና የት ሄደው ኑሯቸውን እንደሚመሠረቱ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ በመሆኑም የማንንም ሰው በሀገር ደረጃም ይሁን በዓለም አቀፍ የመተዳደሪያ ኑሮውንና የሚናገረውን ቋንቋ የሚመራው የፍላጎትና የአቅርቦት የኢከኖሚያዊ የገበያ ትስስር የሚወስነው ሳይንሳና ፖለቲካ እንጂ፣ ማንም ሰው በ'ብሔር” ማንነት የአዕምሮው ቅዠት ስሜት እንደፈለገው የሚመራው አይደለም፡፡ ማንም ሰው ከአፍ መፍቻው ቋንቋ ውጪ ለኢኮኖሚና ለማህበራዊ ኑሮው የሚጠቅመውን ቋንቋ ተገዶ ሳይሆን ፈቅዶና ደስ እያለው ይለምዳል፡፡ ሰው ኑሮውን የጀመረው በቤተሰብ ሲሆን አድጎም ማህበራዊ፣ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ይሆናል፡፡

ምክንያታዊ ያልሆኑ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መንፈሳዊ ፍርሃቶች የመፍትሄያቸው መዳረሻ ምክንያታዊ ባለመሆናቸው ውጤታቸው ለሰው ልጅ ጥፋት ነው፡፡ የአሁኑ ዓለም ሰው የፍርሃቱ ምንጭ፣ ሰው በደመነፍስ ካገኘው በህይወት የመኖር ፍላጎቱና በየጊዜው በህይወት እንዳይኖር የሚያደርጉትን ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና መንፈሳዊ ችግሮቹን ለመፍታት በጊዜው እውቀት ከማጣቱ የተነሳ በችግሮቹ የመሸነፉ ውጤት ነው፡፡


የብሔር” ማንነት የቅዠት አዕምሮ ህመም መነሻው ችግርን በተረጋጋ አዕምሮ አጥልቆ በማሰብ ስለችግሩ ትክክለኛ ግንዛቤና ፍቺ ከማግኘት ይልቅ በድንጋጤ፣ በንዴት፣ በበቀል፣ በቅናት፣ በቁጭት ወዘተ በተቃኘ የፍርሃት አዕምሮ የሚመነጨውን የተሳሰተ የችግር ግንዛቤና ፍቺ ትክክል አድርጎ አዕምሮ በመወሰን የተሳሳተ መፍትሄ ሲታቀድ ነው፡፡ ያልነቃ ማህበረሰብ ችግርን ተገንዝቦ ትክክለኛ የችግርን ፍቺ ከመስጠት ይልቅ ወደተሳሳተ የችግር  ግንዛቤና ፍቺ መግባቱ በጣም ይቀርበዋል፡፡ በዋናነት በአፍሪካ አህጉር ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትን የተማሩም፣ ያልተማሩም የሚባሉት የማህበረሰብ አባላት የተያዙበት የአዕምሮ ቅኝት አጥብቆ በማሰብ ችግርን በትክክል የመገንዘብና ትክክለኛን ፍቺ የመስጠት ፍላጎታቸው የሞተ ነው፡፡

ይህም የአዕምሮ ቅኝት ለአዕምሮ ቅዠት ህመም እያጋለጣቸው በቀላሉ እንደተስቦ በሽታ ከሰው ወደ ሰው የሥነልቦና ችግር ተዛማች በሽታ እየሆነ ነው፡፡ ተዛማች የበሽታ አይነቶች ሲከፈሉ ምናልባት በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ እነርሱም ሥነልቦናዊና ሥነህይወታዊ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዋናነትም በአፍሪካ ውስጥ እንደኢትዮጵያ የመሳሰሉትን ሀገራት ከሥነ ህይወታዊ በሽታ ይልቅ የሥነልቦናዊ ህመም የሆነው የ” ብሔር” ማንነት ቅዠት እንደ ቫይረስ ተላላፊ የአዕምሮ በሽታ በመሆን የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ፣ ከኑሮ እያፈናቀለና እያሰደደ ይገኛል፡፡ እንዲያውም የሥነልቦና በሽታ የሆነው የ"ብሔር” ማንነት የአዕምሮ ቅዠት ህመም መለከፍ ለሥነ ህይወታዊ በሽታ እንዲሁም ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ለፖለቲካዊና ለኃይማኖታዊ ችግሮች መስፋፋት መሠረታዊ ተዛማች በሽታ ነው፡፡

ምንጭ- የብሔር ማንነት ቅዠት
ደራሲ- ሰብስቤ አለምነህ


@Human_Intelligence
@Human_Intelligence