Get Mystery Box with random crypto!

ራስህን ጠብቅ! ፓስወርድህን አጥብቅ! (World Password Day!) (እ.ብ.ይ.) ዲጂታል ጦ | የስብዕና ልህቀት

ራስህን ጠብቅ! ፓስወርድህን አጥብቅ!
(World Password Day!)
(እ.ብ.ይ.)

ዲጂታል ጦርነቱ ተጧጡፏል፡፡ የዓለም ሐያልነት ፉክክር በቴክኖሎጂ ስልጣኔ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ሐገራት ቴክኖሎጂ ያልነካውና ያልደረሰበት የለም፡፡ ንብረቶቻችን፣ ጥሪቶቻችንና ገንዘቦቻችን እንደጥንቱ ጊዜ ዘመድ ወይም ወዳጅ ጋር በታማኝነት በአደራ የምናስቀምጥበት፣ ከመሬት በታች ቆፍረን የምንደብቅበት፣ በቤታችን ሳጥን ውስጥ ቆልፈን የምንሸሽግበት ጊዜ እያበቃ ነው፡፡ ዛሬ ቁልፉ ዘምኗል፣ ማስቀመጫውም ረቅቋል፡፡ ግዢዎቻችንንም ሆነ ሽያጮቻችንን የምናቀላጥፈው፣ የዕለት ተዕለት የሕይወታችንን መስተጋብር የምናስኬድበት፣ ገንዘባችንን ወደፈለግነው ቦታ የምናዘዋውረው መረጃ ቴክኖሎጂው በቀደደልን አዲስ መንገድ ሆኗል፡፡ ሁሉ ነገር በእጃችን መዳፍ ቁጥጥር ውስጥ እየሆነ ነው፡፡ የምንፈልገውን ማዘዝ፣ የምንሻውን ማንበብ፣ ማዳመጥና ማየት የምንፈልገውን ሁሉ የምናደርገው በገዛ የእጃችን ስልክ ነው፡፡

የሆነው ሆኖ በዘመናዊው ዓለም አሰራር ስራ ለመቀጠር፣ ትምህርት ለመማር፣ የፍርድ ቤት ክርክሮችን ቀጠሮ ለማስያዝ፣ ለአየር በረራ፣ የሆቴል አልጋ ለመከራየት፣ ወዘተ ስራዎቻችንን ለማቀላጠፍ እንዲረዳን ደግሞ የመጠቀሚያ ስምና የይለፍ ቃል (Username amnd Password) የግድ ያስፈልገናል፡፡ ግላዊ ሃሳቦቻችንን የምናንፀባርቅባቸው፣ ከሌላው ጋር የምንከራከርባቸው፣ የምንማማርባቸው፣ የምንደዋወልባቸው፣ የምንዝናናባቸው፣ ያሻነውን የምናደርጋባቸው እነፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ዩቱብ፣ ሚሴንጀር፣ ወዘተ ሁሉም የማህበራዊ ሚዲያዎች ያለ ጠንካራ የይለፍ ቃል አደጋ ላይ ይጥሉናል፤ ደህንነታቸውም ካልተጠበቀ ከጥቅማቸው በላይ ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡

በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ የኮምፕዩተርን የይለፍ ቃል እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ያስተዋወቀው ታዋቂው አሜሪካዊ የኮምፕዩተር ሳይንቲስት ፈርናንዶ ኮርባቶ (Fernando Corbato) ሲሆን ዓላማውም በጊዜው የነበሩ ተመራማሪዎች ግላዊ የምርምር ፋይሎችን እንዲጠቀሙ ለመፍቀድ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2005 ዓ.ም. “Perfect Passwords” በሚል ርዕስ መፅሐፍ በማሳተም ለመጀመሪያ ጊዜ ፓስወርድ ቀን ሊሰየምበት እንደሚገባ ሃሳብ ያነሳው ሰው ደግሞ ማርክ ብሩኔት (Mark Brunett) የተባለ ፀሐፊ ነበር፡፡ ከስምንት ዓመታት በኋላ ሃሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ የሳይበር ደህንነት ባለሞያዎች እ.ኤ.አ. በ2013 ዓ.ም አድርገውት በነበረው ዓመታዊ ስብሰባ የፈረንጆቹ የግንቦት (May) ወር በገባ በመጀመሪያው ሐሙስ የዓለም የፓስወርድ ቀን መታሰቢያ እንዲሆን ተስማምተው ቀኑን አፅድቀውታል፡፡ ይሄ እንዲሆን ዋናውን ሚና የተጫወተው ታዋቂው የኮምፕዩተር ዕቃዎች አምራች የሆነው ታላቁ የአይቲ ኩባንያ ኢንቴል (Intel) ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የዛሬው ሐሙስ ግንቦት 5 ቀን 2022 ዓ.ም የዓለም የፓስወርድ ቀን ለአስራአንደኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡

የዓለም የፓስወርድ ቀን ለምን አስፈለገ ለሚለው ጥያቄ ባለሞያዎቹ ሲመልሱ የሕይወት መስተጋብራችን ድሮ ከነበረው እየተለወጠ በመምጣቱና ሁለመናችን ወደዲጂታል ዓለሙ እየተቀየረ በመሆኑ ምክንያት የቴክኖሎጂው አጠቃቀማችን ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆንና ጥብቅ የይለፍ ቃል እንደሚያስፈልገን ለማስገንዘብ ነው፡፡ ጥንቃቄው አንደኛ የመጠቀሚያ ስማችንንና የማለፊያ ቃላችን አለመዘንጋት ሲሆን ሁለተኛውና ዋናው ጉዳይ ግን የይለፍ ቃላችን (Password) በቀላሉ አየር በአየር በሚዘርፉ የመረጃ መንታፊዎች (ዘመናዊ ሌቦች) በቀላሉ እንዳይዘረፍ ቁልፋችንን ማዘመን እንደሚጠበቅብን ለማሳሰብ ነው፡፡

ዘመኑ የወለዳቸው፣ ለዓለም ስጋት እየሆኑ የመጡት የመረጃ መንታፊዎች አይደለም ግለሰብን ቀርቶ ትላልቅ ግዙፍ ተቋማትን እየተገዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በያንዳንዷ ሰከንድ 921 የይለፍ ቃሎች (Passwords) ጥቃት ይከፈትባቸዋል፡፡ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ደግሞ ይሄ ቁጥር እጥፍ ሆኖ አድጓል፡፡

ዋናው ቁምነገር እንዴት ነው የይለፍ ቃላችንን በቀላሉ የማይደፈርና ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የምናደርገው የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ የዘርፉ ባለሞያዎቹ እንደሚመክሩት ተጨማሪ መግቢያዎችን (Logins) መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ አንደኛው Two-factor authentication የሚባል ሲሆን ከመጠቀሚያ ስምና ከይለፍ ቃል በተጨማሪ ማንም ሌላ ሰው ሊያውቀውና ሊደርስበት የማይችለውን የሚስጥር ጥያቄዎችን በመሙላትና እሱን በመመለስ ወደመረጃ መረቡ የምንገባበት ዘዴ ነው (ለምሳሌ የመጀመሪያ ፍቅረኛ ስም፣ የእናት ስም፣ ወይም የትውልድ ቀንና ቦታ፣ ወዘተ)፡፡ ሁለተኛው የፊት አሻራን (Face Recognition) መጠቀም ነው (ምናልባት ይሄኛው ዘዴ በቅርቡ ሶስትና አራት አመታት ውስጥ በተመረቱ ዘመናዊ ስልኮች ውስጥ የሚገኝ መላ ነው)፡፡ ሶስተኛው ዘዴ ደግሞ Single-Use code የሚባል ሲሆን ወደመረጃ መረቡ ለመግባት የፈለገው ሰው ማን እንደሆነ ለማረጋገጥ መግቢያችንን ከኤሜላችን ጋር በማስተሳሰር ወደኢሜላችን ኮድ ወይም የሚስጥር ቁጥሮች እንዲላክን በማድረግ እኛ ራሳችን ስለመሆናችን የምናረጋግጥበት መንገድ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ.. ዘመኑ ረቅቋል፤ ዘመናዊ ሌባውም የዛኑ ያህል ተመንጥቋል፡፡ ስለዚህ ለአፍህም ለይለፍ ቃልህም ዘብ ቁም፡፡ አዕምሮህን ከክፉ ሃሳብ፣ አፍህን ክፉ ከመናገር፤ የማለፊያቃልህን ከመረጃ መንታፊዎች አድን፡፡ ራስህን ጠብቅ! ፓስወርድህን አጥብቅ!

ቸር ጊዜ!

____
እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሐሙስ ሚያዚያ ፳፯ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም.

@Zephilosophy
@Zephilosophy