Get Mystery Box with random crypto!

ክፍል 3 ......ከባለፈው የቀጠለ #ልጆቻችን ላይ ውሸትን ለማስወገድ የሚረዱን መንገዶች ❖ | ሂላል ኪድስ Hilal Kids

ክፍል 3
......ከባለፈው የቀጠለ

#ልጆቻችን ላይ ውሸትን ለማስወገድ የሚረዱን መንገዶች

❖ ልጆቻችን እውነት ከእስልምና (ከሃይማኖት) ትላልቅ እሴቶች መካከል አንዱና ዋናው መሆኑን እንዲያውቁ ማድረግ፡- ልጆች ውሸት እንዴት እንደሚጠላና የተወገዘ ነገር መሆኑንም ማስረዳት ያስፈልጋል፡ ውጤቱም የከፋ መሆኑን ልናመላክት ይገባል፡፡ ረሱል (ሰዐወ) እውነት ወደ በጎ ነገር ይመራል ሲሉ አስተምረዋል፡፡አንዲት ሴት ነበረች ይባላል፡ ስለውሸታሞች የከፋ ፍጻሜ የሚተርኩ ከ20 በላይ ተረቶችን በቃሏ አጥንታለች፡ እናም ሁሌም ልጆችን ስታገኝ ታወራላቸዋለች፡ በዚያም ምክንያት ካሉት ልጆቿ መካከል የ9 አመቱ ልጅ እቤት ውስጥ በስህተት እንኳ ውሸት እንዳይወራ እራሱን ዘበኛ አድርጎ ቀረ፡ ቀልድ እንኳን ሲነሳ እውነት እንዲሆን ያስጠነቅቅ ነበር፡፡(ተጠቀሙበት)

❖ ለልጆቻችን በምንም ምክንያት ውሸት ከቅጣት እንደሚያድናቸው ምልክት አለመስጠት፡- እንዲያውም እውነቱን ሲናገር ቅጣት እንደሚቀንስለትና ለሰራው ስህተት ምህረት እንደሚያስገኝለት ልናስረዳው ይገባል፡ ያ ካልሆነ ቅጣቱ የውሸቱና ያጠፋው ጥፋት ሆኖ እንደሚመጣ እናስረዳው፡

❖ ልጆቹ የዋሹበትን ምክንያት ማወቅ፡- ምክንያቱን አለማወቅ መፍትሄ ለማግኘት ይከብደናል፡፡ቅጣትን ፈርተው ከሆነ ቅጣቱን መቀነስ መልካም ነው፡ ልጁ ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑ እንዲሰማው ማድረግና ነገር ግን ያጠፋውን ጥፋት ዳግም እንዳይፈጽመው ማሳመን ከዚያም እነዚህን ጥፋቶች መደጋገም ሊያስከትል የሚችልውን ውጤት ማስረዳትም የግድ ነው፡ ለውሸቱ መነሻ የሆነው ሌሎችን ዝቅ አድርጎ መመልከቱ ከሆነ የምናስታውሰው ከሰዎች ጋር መልካም ግንኙት መመስረት መቻል እንዳለበት ለዚህ ደግሞ መከባበር የግድ መሆኑን ማስረዳት፡ ልጁ የሚዋሸው የሚዋሹ የቤተሰቡ አባላትን አይቶ መሆኑን ከተረዳን እንግዲህ ከራሳችን ጋር እውነተኛ ሂሳብ መስራት ያስፈልገናል፡ እራሳችንን ለማረምና ለሌሎች መበላሸትም ምክንያት የመሆናችንን ሃላፊነት መውሰድ ይጠበቅብናል፡ ምክንያቱ የዝቅተኝነት ስሜት ከሆነ በራስ የመተማመን መንፈሱን ማዳበርና እና ተጨባጩንም አምኖ እንዲቀበል ማሳመን፡ ያሉትን ጠንካራ ጎኖችን አጉልቶ ማሳየት እንዲያዳብራቸው ማስረዳት በራስ ለመተማመን ይረዳል፡፡

❖ ልጁን ውሸታም ነኝ ብሎ ራሱን እዳይቀበል መጠንቀቅ፡- የቱንም ያህል የዋሸን መሆኑን ብናውቅም፡ ምክንያቱ ነኝ ብሎ ከተቀበለው ስራው (መገለጫው አድርጎ) ሊይዘው ስለሚችል፡ ከኛ የሚጠበቅብን ካለበት መጥፎ አመል ለማላቀቅ መስራት ነው፡ ለምሳሌ ስለእውነተኞች ሲነሳ በጣም ማሞገስና ማወደስ፡ እውነት የተናገረባቸውን አጋጣሚዎቹን በሙሉ ማድነቅና ማበረታታ፡ ሲዋሽ ሲያጋጥመን እንደስህተት በመቁጠር እንዳይደግመው ማሳሰቢያ እየሰጠን ማለፍ፡ የመሳሰሉትን መጠቀም መልካም፡ ነው፡ በርካታ ውጤታማ ወላጆች ልጆቻቸውን ያሳደጉት አዎንታዊ ጎኖቻቸውን በማጉላትና ማበረታታት በመሆኑ ልጆቻቸው ካደጉ በኋላ እንኳ በልጅ ልጆቻቸው ላይ በማየት ተደስተዋል፡፡

በቀጣይ ሌሎች የልጆች የባህሪ ችግሮችን ይዘን የምንመለስ ይሆናል።