Get Mystery Box with random crypto!

ዋና ዋና የህጻናት የባህሪ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው የህጻናት የባህሪ ችግሮችን ስናነሳ በርካታ እሮ | ሂላል ኪድስ Hilal Kids

ዋና ዋና የህጻናት የባህሪ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው

የህጻናት የባህሪ ችግሮችን ስናነሳ በርካታ እሮሮዎች ከወላጆችና ከአሳዳጊዎች እንሰማለን፡ ችግሮቹ ብዙዎች ቤት መከሰታቸው እንዳለ ሆኖ ችግሮቹን መረዳትና መፍትሄ መስጠቱም ቀላል አልሆነም፡ እንዲያውም ከአለምና ከአካባቢያችን ነባራዊ ሁኔታዎች ፈጣን ለውጦችን ተከትሎ የበለጠ እየተወሳበብን መፍትሄ ለማግኘትም እየከበደንና ከልጆቻችን ጋር መግባባትና ለሚያሳዩት ያልተገቡ ስነምግባሮች መልስ መሰጠት እንዳቃተን በበርካታ አጋጣሚዎች እየገለጽን እንገኛለን፡፡ ስለሆነም ይህን ተከታታይ ትምህርታዊ መጣጥፍ በልጆቻችን ዋናዋና የባህሪ ችግር አይነቶች፤ምክንያቶችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ሳደርግ የሚከተሉትን ነጥቦች ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡
በመጀመሪያ አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ችግር አለበት ለማለትና ጥሩ ስነምግባር አለው በምንላቸው ልጆች መካከል የሚታይና ግልጽ ልዩነትን ማስቀመጥ ከባድ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ባሕሪያትን ኖርማል (ጤናማ) ከሚባለው ልኬት አልፎ መቼ መጥፎና ልናርመው የሚገባው ደረጃ ላይ መድረሱን መለየት ይከብዳል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማወቅ ሁለት መንገዶችን ልንጠቀም እንችላለን፡
የባህሪው ፍጹም ወጣ ማለት፡-በወንድም ወይም በእህቶቻቸው ላይ አደጋ ማድረስ፤ ከፍተኛ የምግብና የእንቅልፍ እጦት፤
የባህሪው መደጋገም፡-ምንም ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ አለመቻል፤ብዙ ምግብ በተደጋጋሚ መብላት፤ቅጥ ያጣ እራስ ወዳድነት ማጎልበት፤እንግዶችን በጭራሽ ለማግኘት አለመፈለግ፡ (መታየትን መፍራትና መደበቅ) ወዘተ

ሁለቱንም ምክንያቶች (የችግሩ መጉላትና መደጋገም) በአንድ ላይ ባይከሰቱና በሆነ አጋጣሚ የተከሰተ ከሆነ ብዙ አያሳስብም፤ እንኳን ህጻናት አዋቂዎችም ከመሰል ስህተቶች አይወገዱምና፡፡ ልጁ መደበኛ (የተለመደ) ከሚባል ባህሪ ውጭ ከሆነብን በተቻለ መጠን በአካባቢያችን የሚገኙ የህክምናም ይሁን የስነልቦና ባለሙያዎችን ምክር መጠየቅ አስፈላጊና ተገቢም ነው፡ ካልተገኙ ከኛ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን ወላጆች ማማከርም ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በኋላ በምናነሳቸው ትምህርቶችና ወላጆች በሚያደርጉት ንባብ እና ክትትል መቼ የባላሙያዎችን ወይም የጎረቤትም ይሁን የወዳጅ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ግልጽ  እየሆነ ይሄዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡
ሌላው ባህሪንና የተለመዱ ስረአቶችን ለመቀየር በምንሞክርበት ጊዜ የሚገጥሙን ችግሮች አሉ

የችግሩ ሰለባ የሆኑት ልጆች ለመፍትሄዎች ያላቸው መልስ (ሪአክሽን) ላይ ያለ ልዩነት
በወላጆችና አሳዳጊዎች መካከልም ያለ የእውቀትና የመረዳት  ደረጃ መለያየት
አንድ የመፍትሄ ሃሳብ ለአንድ ልጅ ሲሆን ለሌላኛው ምንም ፋይዳ አለመኖር፤አንዳንድ ጊዜ ወላጆች ባለሙያዎችን ሊያማክሩ ይሄዱና እንደመፍትሄ የሚነገራቸውን በሙሉ ሞክረውት ግን ጥቅም ሳይሰጣቸው እንደቀረ ወይም ደግሞ ያንን ሃሳብ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ በኋላ ልጁ እንደባሰበትም የሚናገሩ ያጋጥማሉ፡፡
ልጆች እያደጉ ሲመጡና ማህበራዊ እውቀታቸው እየዳበረ ሲመጣ ሊቀንሱ የሚችሉ ባህሪያቶች ላይ የወላጆች ታጋሽ አለመሆን፤ ለምሳሌ
o ትእቢተኛነት
o በቶሎ መናደድ
o የተወሰኑ ምግቦችን በፍጹም አለመመገብ
ነገር ግን አብረው ሊያድጉ እንዲሁም በጊዜ ሂደት እየተባባሱ ሊመጡ የሚችሉ እንደውም በጊዜ መፍትሄ ካልተፈለገላቸው ወደፊት በልጆቹ ስብዕና ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ባህሪያቶች እንዳሉ መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ለምሳሌ 
o አንዳንድ ቀላል የሚመስሉ የጤና ችግሮች ለምሳሌ አልጋ ላይ መሽናት፤
o በጣም ተደባዳቢ መሆን (ወላጆች ስርዐት  ማስያዝ እስከሚያቅታቸው ድረስ)
o የወንድሞቹን ንብረት ማጥፋት መሰባበር፡ ማስቸገርና ከቁጥጥር ውጭ መሆን
ስለሆነም መጀመሪያውኑ በቤቱ ነገሮችን ስረዓት የሚያስይዝ ሰው መኖሩን እንዲገነዘብና ህግ እንዲያከብር፤ ለህገ-ወጥ ድርጊቶቹም ሀላፊነት እንዳለበት መማር ያስፈልገዋል፡፡
በቀጣይ በዋና ዋና የልጆች የስነባህሪ ችግሮች፤ ምክንያቶችና መፍትሄዎቻቸውን ይዤ እመለሳለሁ፡፡