Get Mystery Box with random crypto!

ሐምሌ 8/2014 ዓ.ም በጎንደር፣ በወራቤ እና በጂንካ በተከሰተው ግጭት የተፈፀሙ ወንጀሎች የምር | የጉመር ወረዳ መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት

ሐምሌ 8/2014 ዓ.ም

በጎንደር፣ በወራቤ እና በጂንካ በተከሰተው ግጭት የተፈፀሙ ወንጀሎች የምርመራ ግኝት ይፋ ተደርጓል።

ከፍትህ ሚኒስቴር የተገኘው ምሉ መረጃ:
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በመተባበር በሚያዚያ ወር በጎንደር፣ በወራቤና በጂንካ አካባቢ በተከሰተው ግጭት የተፈጸሙ ወንጀሎችን የምርመራ ግኝት ይፋ አደረገ፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በመተባበር በሚያዚያ ወር በጎንደር እና በወራቤ ሀይማኖትን መሰረት አድርጎ እንዲሁም በጂንካና አካባቢው ማንነትን መሰረት አድርጎ በተከሰተው ግጭት የተፈጸሙ ወንጀሎችን የምርመራ ግኝት ይፋ አደረገ፡፡

የምርመራ ግኝቱን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ጸጋ እና በፌዴራል ፖሊስ በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙልኢሳ አብዲሳ በጋራ በመሆን ለሚዲያዎች አብራርተዋል፡፡

በጎንደር ሚያዝያ 18/2014 ዓ.ም በአንድ የእስልምና ኃይማኖት አባት ስርዓተ-ቀብር ላይ ለቀብር የሚሆን ድንጋይን ሰበብ በማድረግ በተከሰተው ግጭት በ20 ሰዎች ላይ ሞት፣ በ100 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንዲሁም በ1 መስጊድ ላይ ሙሉ በሙሉ ውድመት እና በ8 መስጊዶች ላይ ከባድ ጉዳት እንዲሁም በ2 መስጊዶች ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት መድረሱን አቶ ሙልኢሳ አብራርተዋል፡፡

አቶ ሙሊሳ በማብራሪያቸው ፖሊስ የ250 ሰዎችን የምስክርነት ቃል ተቀብሏል፤ ሌሎች ከወንጀል አፈጻተሙን የሚያስረዱ የተለያዩ ማስረጃዎችን አሰባስቧል፡፡ በዚሁም መሰረትም 509 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፉ ሰዎችን የመለየት ሥራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም መሰረት የተደራጀውን የምርመራ መዝገብ ለዐቃቤ ሕግ አስረክበናል ያሉ ሲሆን ዐቃቤ ሕግም የክስ መመስረት ሂደቱን ጀምሯል ብለዋል፡፡

በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ጎንደር የተፈጸመውን የሀይማኖት ግጭት መነሻ በማድረግ ወንጀሉን ከህዝብ ጋር ሆኖ ከመከላከል ይልቅ፤ አንዳንድ ጽንፈኛ ኃይሎች በጎንደር መስጊድ ተቃጥሏል ውጡና የክርስቲያን ቤቶችን አቃጥሉ በማለት በከተማው ማይክራፎን ይዘው በመቀስቀስ በ4 የኦርቶዶክስ እንዲሁም በ3 የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ ሲሆን፤ ጉዳት አድራሾቹ የሞተር ሳይክልና ገጀራዎችን በመጠቀም በ2 ሰዎች ላይ ሞት፣ በ79 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት እንዲሁም 12 በሚሆኑ በግለሰብና በንግድ ቤቶች ላይ ከባድ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ሲሉ አቶ ሙልኢሳ በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

ጂንካ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘም የአሪ ብሄረሰብ ዞን እንሁን በሚል የከተማውን ከንቲባ ጨምሮ ሻንካ /ወጣት/ የሚል ቡድን በማደራጀት ቅስቀሳ በማድረግ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በአማራ ተወላጆች ላይ ፈጸመዋል ያሉት አቶ መልኢሳ፤ በተጨማሪም 247 ሚሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ጉዳት ደርሷል፤ 1150 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል ብለዋል፡፡
አቶ ሙልኢሳ አክለውም የህግ ማስከበር ሂደቱን የፌዴራል ፖሊስ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንደሚቀጥል ተናግረው፤ ህብረተሰቡም ወንጀል ፈጻሚዎችን ከመደበቅ ይልቅ በማጋለጥ ወንጀልን በመከላከሉ ረገድ ከህግ አካላት ጋር በመሆን በጋራ እንዲሰራ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የክስ ሂደቶችን እና ጥልቅ የሆኑ የምርመራ ስራዎችን በተመለከተም በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑት አቶ ፍቃዱ ጸጋ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በጂንካ ማንነትን መሰረት ያደረገው ጥቃት ሚያዚያ 1 ቀን መፈጸሙን አውስተው፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግበት መቆየቱን የምርመራ ግኝቱ እንደሚያመላክት ተናግረዋል፡፡
ሚኒስቴር ዴኤታው አክለውም በደቡብ ኦሞ ዞን የተፈጸመው የወንጀል ምርመራ መሰረት የሚያደርገው ጂንካና አራት የአሪ ብሄረሰብ ተወላጆች የሚኖሩባቸው ወረዳዎች ላይ የተፈጠረውን ግጭት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአሪኛ ሸከን ወይም ወጣት ተብሎ የተደራጀ ቡድን፤ በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚኖሩ 16 የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ውስጥ እኛ ለብቻችን የጂንካን ከተማን ጨምሮ አራት ወረዳዎችን በመያዝ ዞን መሆን አለብን፤ የሚል ዓላማን በማንገብ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር በወረዳውም በዞኑም ያሉ የመንግስት ኃላፊዎች ጭምር ያደራጇቸው ወጣቶች፤ የዞን ጥያቄያችን የማይቀበለው የአማራ ብሄር ተወላጅ ነው ስለዚህ በመጀመሪያ የአማራ ተወላጅን ነው ከአካባቢው ማስወጣት ያለብን የሚል ይዘት ያለው ቅስቀሳ አድርገዋል ሲሉ አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ከመጋቢት 26/2014 ዓ.ም ጀምሮ የኑሮ ውድነትን ሰበብ በማድረግ የአማራ ነጋዴዎችን ሱቅና ቤት በመበርበር ተለያዩ ዕቃዎችን ወደ ማዘጋጃ ቤት ወስዶ በማከማቸት ሂደት ላይ ከቆዩ በኋላ በተለይ በወረዳዎች ላይ ሚያዚያ 21/2014 ዓ.ም የሸከር ዋነኛ አደራጅ የነበረው አቶ ማቲያስ በአማረው ተገድሏል በማለት ወሬ በማናፈስ በጂንካ ደግሞ ሰልፍ እንዲኖር በማድረግ አስቀድመው በለዩት የአማራ ተወላጆች ቤት ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የምርመራ ግኝታችን ያመላክታል ብለዋል፡፡
በዚህ ጊዜ ወደ 144 የአማራ ተወላጆች ቤት ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል 46 ቤቶች በድንጋይና በተለያዩ ቁሳቁሶች ጉዳት እንዲደርስባቸው መደረጉንም የገለጹት ሚኒስቴር ዴኤታው በተጨማሪም አንድ መስጊድ ተቃጥሏል፣ 232 የንግድ ድርጅቶች ተዘርፈዋል ጥቃቶቹም የተፈጸሙት በአማራ ብሄር ተወላጆችና በሌሎች የእነሱን መደራጀት አይደግፉም ያሏቸው ብሄሮች ላይ ነው ብለዋል፡፡

በሂደቱ 782 ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ከ782 ተጠርጣሪዎች ውስጥ በፌዴራል መንግስቱ ስልጣን ስር ይወድቃሉ የተባሉ 142 ተከሳሾች ላይ በፍትህ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ክስ ተመስርቶባቸዋለው፤ ሌሎቹ በዞን በወረዳ እንደየስልጣናቸው ክስ እንዲመሰረትባቸው መደረጉንም አቶ ፍቃዱ በመግለጫቸው አብራርተዋል፡፡
በወንጀሉም ላይ የጂንካ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ፣ የጂንካ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የጂንካ ከተማ ፋይናንስ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የደቡብ አሪ ወረዳ አስተዳደር፣ የጂንካ ዩኒቨርስቲ መምህርና የተለያዩ የመንግስት ሰራተኞች የተሳተፉበት ከመንግስት ፋይናንስ እየወጣ ለወጣቶቹ አበል በተለያየ መንገድ የተከፈለበት ሂደት እንደነበር የምርመራ ግኝታችን ያሳያል ብለዋል፡፡
ምርመራው በደረሰበት ልክም የመንግስት አስተዳደር ላይ ያሉ ሰዎች በወንጀሉ ውስጥ በመሳተፍ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ተረጋግጧል ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው እስከዛሬ ከመረመርናቸው በተለየ ከ8 ሰዎች ውጭ ሌሎቹ በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ በተጨማሪም ምንም የሰው ህይወት ሳይጠፋ 8 ሰዎች ላይ ብቻ የተለያያ ጉዳት ደርሷል፡፡ መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስና ልዩ ኃይል በቶሎ መግባታቸው ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ እንድንከላከልም አግዞናል፤ ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው ይህ ጉዳት የደረሰውም አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር የለም በሚል አመራሮቹ በወንጀሉ ላይ በመሳተፋቸው የጸጥታ አካላት እንዳይገቡ በማድረጋቸው ነው ብለዋል፡፡