Get Mystery Box with random crypto!

ንዜኑ ትንሣኤከ ቅድስት እግዚኦ..... እንቋዕ አብጻሕክሙ ለበዓለ ትንሣኤ ቅድስት ለእግዚነ ወአም | ንግባእኬ ኀበ ጥንተ ነገር (ወደ ቀደመው ነገር እንመለስ)

ንዜኑ ትንሣኤከ ቅድስት እግዚኦ.....

እንቋዕ አብጻሕክሙ ለበዓለ ትንሣኤ ቅድስት ለእግዚነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ።


ትንሣኤ

ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በዘመነ ብሉይ ኹሉም የሰው ልጆች በአዳም ኃጢአት ምክንያት እየተኰነኑ በሞተ ነፍስ ተይዘው ለርደተ ሲዖል ይዳረጉ ነበር ። (፩ኛ ቆሮ ፲፭ ÷፳፪)

"ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ከዚያም እስከ ክርስቶስ ድረስ ሞት ነገሠ፤" ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ (ሮሜ ፭÷፲፬)

በዚኽም ምክንያት አበ ብዙኀን አብርሃም እና ሌሎች ደጋግ አባቶች እንኳ ሳይቀሩ የወረዱት ወደ ሲዖል ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ "ጽድቃችንም ኹሉ እንደመርገም ጨርቅ ነው፤" (ኢሳ ፷፬ ÷፮) ኤርምያስም "ለሥጋ ለባሽ ኹሉ ሰላም የለም፥ ስንዴን ዘሩ እሾኽንም አጨዱ፡፡" (ኤር ፲፪÷፲፫)ብለዋል።

በዚኽ ምክንያት የብሉይ ኪዳን ዘመን - ዘመነ ፍዳ፣ ዘመነ ኵነኔ፣ ዘመነ ጽልመት ተብሏል፡፡ በዚኽ ዘመን እነ ቅዱስ ዳዊት፡- "አንሥእ ኃይለከ ወነዓ አድኅነነ፤ ኃይልኽን አንሣ እኛንም ለማዳን ና" እያሉ ወልድን ተማጽነዋል፡፡ (መዝ ፸፱÷ ፪)

ይኽም የሚያመለክተው በዚያ በጨለማ ዘመን ኾነው ተስፋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ እንደነበረ ነው፡፡ በሞት አጠገብ ሕይወት÷ በመቃብር አጠገብ ትንሣኤ እንዳለ ተስፋ እንዲያደርጉ የሚያደርጋቸው የክርስቶስ ትንሣኤ ነውና፡፡ ያን ጊዜ ከሲዖል እንደሚወጡ፥ የተዘጋች ገነትም እንደምትከፈትላቸው ያውቃሉና፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤን፣ የአዳም ልጆች በጠቅላላ “ትንሣኤ ዘጉባኤን” በተስፋ እንዲጠብቁ ኾነዋል፡፡ ይኽም ተስፋ ሃይማኖት እንዲይዙ ምግባር እንዲሠሩ፣ ምድራዊውን ንቀው ሰማያዊውን እንዲናፍቁ አድርጓቸዋል፡፡

ዛሬ ከ፪ሺህ አዝማናት በላይ ቆይተን እንደ ነብየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት “አቤቱ ኃይልኽን አንሣ እኛንም ለማዳን ና” እያልን መጮኽ ያለብን ጊዜ ላይ ነን፡፡ በክርስቶስ ትንሣኤ ዘለዓለማዊ ብርሃን ወጥቶልናል፣ በመቃብር አጠገብ ትንሠኤን ዓይተናል፤ ነገር ግን ምግባራችን ስላልቀና ለመከራ ቸነፈር ተላልፈን ተሰጠን፡፡ "አቤቱ ማረን" እንበለው! እሱም በምሕረቱ ይጎበኘናል፣ በብሉይ የተዘጋው ገነት በሐዲስ ተከፍቷልና፤ በክፋታችን ልክ እንደተራራቅን በእግዚአብሔር ፍቅርና በልቡና መመለስ እንቀራረባለን፤ ክፉ የተናገረው አንደበት ከጨርቅ፣ ክፉ ያደረገ እጅ ከአጓንት እንዲላቀቅ፣ ለአንደበታችን መልካም ንግግርን ለእጃችንም መጽዋትን ልምድ እንድናደርግ ፈጠሪ ይርዳን፡፡

በክርስቶስ ትንሣኤ ያገኘነው ጸጋ ታላቅ ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን ወጥተናል ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናል፣ ሙታን የነበርን ሕያዋን፣ ምድራውያን የነበርን ሰማያውያን፣ ሥጋውያን የነበርን መንፈሳውያን ኾነናል፡፡ "ሞት ኾይ÷ መውጊያኽ የት አለ? ሲዖል ኾይ ድል መንሣትኽ የት አለ?" የምንል ኾነናል፡፡ ሆሴ ፲፫÷፲፬ ፣ ፩ኛቆሮ ፲÷፶፭፡፡

በዘመናችንም ከመጣብን ሞት አምላከ ቅዱስ ያሬድ በቸርነቱ ትንሣኤውን እንዳሳየን - ከቸነፈሩም ጠብቆ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ እንዲያወጣን የዘወትር ጸሎታችን ነው፡፡



መልካም የትንሣኤ በዓል ይኹንልን

ምንጭ፦ ውሉደ ያሬድ ሰ/ት/ቤት