Get Mystery Box with random crypto!

፩.፭. የፊደል ለውጥ በአንድ ቃል ውስጥ #ሙባእ የ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን ቤተክርስቲያን አምድ | ንግባእኬ ኀበ ጥንተ ነገር (ወደ ቀደመው ነገር እንመለስ)

፩.፭. የፊደል ለውጥ በአንድ ቃል ውስጥ


#ሙባእ

የ፲፱ኛው ክፍለ ዘመን ቤተክርስቲያን አምድ የነበሩት #ሊቁ_መልአከ_ብርሃን_አድማሱ_ጀንበሬ_ዝክረ_ሊቃውንት በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለው በገጠሙት ግጥም እንጀምራለን!!!


ባንዱ የሚጻፈው በሌላው ሲጻፍ፣
ቋንቋው ተበላሽቶ ይሆናል ጸያፍ።
የጸሐፊ ደዌ ያታሚ መከራ፣
ጠንቅቆ አለማወቅ የፊደልን ሥራ።
እንዳገኙ መጻፍ በድፍረት በመላ፣
የቋንቋ ደረመን የመጽሐፍ ቢስ ገላ።
ንባብ የሚያሳክክ ምስጢር የሚቆምጥ፣
መልክአ ትርጓሜ የሚለዋውጥ።


(የቅኔው አባት ሊቁ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ)

#ዘጠኙ_ፊደላተ_ግእዝ

በግእዝ ቋንቋ ተመሳሳይ ድምጸት እና አገልግሎት ያላቸው ፊደላት የሉም። እያንዳንዱ ፊደል የራሱ ድምጸት፣ ትርጉም እና አገልግሎት አለው።

በተለምዶ ሞክሼ ፊደላት እያልን የምንጠራቸው ዘጠኙ ፊደላት <<ሀ፣ሐ እና ኀ፤ አ እና ዐ ፣ ሰ እና ሠ፣ ጸ እና ፀ>> በተለምዶ አንድ አይነት ድምጸት እየሰጠን እንዲሁም ተመሳሳይ አገልግሎት ላይ እያቀያየርን እየተጠቀምን እንገኛለን። ይህ ፍጹም ስሕተት ነው! በግእዝ ሞግሼ ፊደል የሚባል ነገር የለም። ሞክሼ ማለት ተመሳሳ ማለት ነውና። እነዚህ ዘጠኙ ፊደላት በድምጽም በአገልግሎት የተለያዩ ናቸው።
እስካሁን ድረስ ያሉኝን ሁለት መረጃዎች ላቅርብ

፩) መምህር ዘርዓ ዳዊት በመርኆ ሰዋሰው በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ ፲፬ ላይ እነዚህን የፊደላት ድምጽ እንዲህ ብለው ጽፈዋል

ሀ እና አ---- ልል የጒሮሮ ድምጽ
ሐ እና ዐ--- ጠባቂ የጒሮሮ ድምጽ
ኀ ---- የታሕናግ ድምጽ

ሰ፣ሠ፣ጸ፣ፀ --- የጥርስ ድምጽ(በጥርስ የሚነገሩ)

፪) መምህር ደሴ ቀለብ ትንሳኤ ግእዝ በሚለው መጽሐፋቸው ገጽ ፭ ላይ ሥርዓተ ድምጸታቸውን እንዲህ ብለው ጽፈዋል

አ---- ኢነዛሪ የማንቁርት እግድ
ዐ---- ነዛሪ የጒሮሮ ፍትግ
ሀ ----ኢነዛሪ የማንቁርት እግድ
ሐ----ኢነዛሪ የጉሮሮ ፍትግ
ኀ ----- ነዛሪ የትናሕግ ፍትግ
ሰ ---- ኢነዛሪ የድድ ፍትግ
ሠ --- ነዛሪ የድድ ፍትግ
ጸ ----ኅዩል ኢነዛሪ የድድ ፍትግ



ከላይ እንዳየነው ሁለቱ የግእዝ መምህራን ተመሳሳይ በሚባል ደረጃ አስቀምጠዋል። የመጀመሪያ ላይ የተቀመጠው ጠቅለል ያለ ሀሳብ ሲሆን ሁለተኛው ላይ ግን በዝርዝር የተቀመጠ ነው።
ምናልባት የጥንቱ አማርኛ፣ ትግርኛ እና ትግረ ቋንቋዎች ይህን ስለሚጠቀሙ በቀላሉ ሊገባቸው ይችላል። የጥንቱ አማርኛ እነዚህን ፊደላት በግእዙ አጠራር ነበር የሚጠራቸው። ከጊዜ ሂደት በኋላ አማርኛው እየተቀየረ አንድ አይነት ድምጽ ይዘው በሚገኙበት ወቅት ደረስን።
ትግርኛ እና ትግረ ግን እስካሁን አ እና ዐ ፣ ሀ እና ሐ የተለያየ ድምጽ ሰጥተው ይጠቀሙበታል።


#የግእዝ_ፊደላት_የቦታ_ለውጥና_የሚያመጣው_የትርጉም_ለውጥ

ከላይ የጠቀስናቸው ፊደላት አንዱ በአንዱ ሲተካ ፍጹም የሆነ የትርጉም ለውጥ ያመጣል።

ለምሳሌ፦
መሀረ = አስተማረ
መሐረ = ይቅር አለ

ኀለየ = ዘመረ፣ አመሰገነ
ሐለየ = አሰበ

ማኅሌት = ዝማሬ፣ምስጋና
ማሕሌት (ሕሊና) = ሐሳብ፣ እሳቤ

አመት = ሴት አገልጋይ
ዓመት = ዘመን፣ ጊዜ፣ እድሜ

ሰአለ = ለመነ
ሠዐለ = ሥዕል ሣለ
ሰአሊ ለነ = ለምኝልን
ሠዐሊ ለነ = ሥዕል ሣይልን

ሰርግ = ጋብቻ፣ ሽልማት
ሠርግ = የመስኖ ቦይ፣ መሥረግ

ፈጸመ = ጨረሰ
ፈፀመ = ነጨ
ፍጹም = መጨረሻ
ፍፁም = የተነጨ
ፍፅም = ግንባር

መአደ = ሰፈረ፣ ከነዳ
መዐደ = ገሰጸ፣ መከረ
ምዕዳን = ምክር፣ ተግሳጽ
ምእዳን = መስፈሪያ

መዐተ = ተቆጣ
መአተ = በዛ፣ ብዙ ሆነ
ምእት = መቶ

አደመ = አማረ፣ ተዋበ
ዐደመ = ሴራ አሴረ

ሰረቀ = ሌባሆነ፣ ሰረቀ
ሠረቀ = ወጣ፣ ተገኘ፣ ተወለደ
ምስራቅ = የሌባ መገኛ፣ ሌባ ያለበት ቦታ
ምሥራቅ = የብርሃን፣ የፀሐይ መውጫ

#ልብ_በሉ

ክርስቶስ #ሰረቀ እምድንግል ብሎ አንድ ሰው ቢጽፍ ክርስቶስ ከድንግል ሰረቀ፣ ቀማት፣ወሰደባት እያለ ነው
ሎቱ ስብሐት በትክክለኛው ሲጻፍ ክርስቶስ #ሠረቀ እምንድንግል ነው። ክርስቶስ ከድንግል ተገኘ፣ተወለደ ለማለት።
ስማችሁን #ምስራቅ ብላችሁ የምትጽፉ የሌባ መገኛ ነኝ እያላችሁ ነው ምሥራቅ ነው ትክክለኛው
እግዚኦ መሀረነ - አቤቱ አስተምረን
እግዚኦ መሐረነ = አቤቱ ይቅር በለን


#ማጠቃለያ

ከላይ እንዳየነው የፊደል ለውጥ ሲኖር እጅግ ብዙ ለውጥ አለው። ፊደል ሲቀየር የቤተክርስቲያንን ሥርዓትና ቀኖና የመቀየር እና የማጣመም አቅም አለውና እንጠንቀቅ፣ እንጠንቀቅ እንጠንቀቅ። ከላይ መግቢያ ላይ የተለጠፈውን የመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬን ግጥም ልብ በሉ።

ስለሃይማኖታችን ማወቅ ስንጀምር ከፊደል እጀምር። ንባብ ይገላል ትርጉም ያድናል ይላል ቅዱስ ጳውሎስ። ትርጉም ደግሞ ከፊደል ጠባይ እና አቀማመጥ እና ትርጉም ይጀምራል!!!!

#ማሳሰቢያ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሠለጠንሁ በሚለው የሀገር ውስጥ ማኅበረሰብ ዘንድ እና ከውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አማርኛን ቆፍረው እየቀበሩት እንደሆነ ይታወቃል።
እባካችሁ ትክክለኛውን ፊደል ተጠቀሙ እባካችሁ።
#አለሁ ለማለት #አለው፣ #መጣሁ ለማለት #መጣው፣ #በላሁ ለማለት #በላው የምትሉ፣ #ነህ ለማለት #ነክ የምትሉ!!!

አለሁ እና አለው በትርጒም የማይገናኙ ቃላት ናቸው።

አለሁ= አለኹ፣ ሀለውኩ(በግእዝ)፣ I am alive, I am present
አለው = ቦቱ (በግእዝ)፣ He has, He owns
አለሁ መኖር አለመኖርን
አለው እርሱ ባለቤት መሆን አለመሆኑን የሚያመለክት ነው።

እስኪ ድንግል የተናገረችውን ይህን እዩት

እነሆ የጌታ ባርያ አለሁ እና
እነሆ የጌታ ባርያ አለው
የትርጒም ልዩነቱን ተመልከቱ መርምሩ። ልዩነታቸው የ እና ነው። የትርጒም ለውጡ ግን ብዙ ነው።

ከ "" እና ከ "" ጋር የተጣላችሁ ታረቁ። አለአግባብ ከ "" እና "" ጋር ፍቅር ውስጥ የገባችሁ ፍቅራችሁን በልክ አድርጉት! የሚመጣውን ትውልድም በቋንቋ ከመግደል ራሳችንን እናቅብ!

።።።።፡።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ባንዱ የሚጻፈው በሌላው ሲጻፍ፣
ቋንቋው ተበላሽቶ ይሆናል ጸያፍ።
የጸሐፊ ደዌ ያታሚ መከራ፣
ጠንቅቆ አለማወቅ የፊደልን ሥራ።
እንዳገኙ መጻፍ በድፍረት በመላ፣
የቋንቋ ደረመን የመጽሐፍ ቢስ ገላ።
ንባብ የሚያሳክክ ምስጢር የሚቆምጥ፣
መልክአ ትርጓሜ የሚለዋውጥ።

(የቅኔው አባት ሊቁ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ)

፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨


#ምንጭ፦
ዝክረ ሊቃውን በሊቁ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ
መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በአለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ
ትንሳኤ ግእዝ በመምህር ደሴ ቀለብ
መርኆ ሰዋሰው ዘልሳነ ግእዝ በመምህር ዘርዓዳዊት አድሐና
የአማርኛ ሰዋሰው በብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ
የአማርኛ መዝገበ ቃላት በደስታ ተክለወልድ

፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧፧
ፈጸምኩ ዘይእዜ ትምህርተ


@geezlisan