Get Mystery Box with random crypto!

ጾም የሥጋ ረሀብ አይደለም የነፍስ ምግብ እንጅ: አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ጾም የሥጋ ሥቃይ | ፍኖተ ቅዱሳን አበው

ጾም የሥጋ ረሀብ አይደለም የነፍስ ምግብ እንጅ:

አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ጾም የሥጋ ሥቃይ ሰማዕትነት ወይም መስቀል አይደለም ሥጋ ከነፍስ ጋር የሚተባበርበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ከፍ ከፍ የሚልበት እንጂ።

ስንጾም የመጾማችን ዕቅድ ሥጋችንን ለማንገላታት አይደለም ጠባዩን ለመግራት እንጂ። ይህ በመሆኑም አንድ የሚጾም ሰው መንፈሳዊ እንጂ ሥጋዊ ሰው አይሆንም ማለት ነው ።

ጾም መናኝ ነፍስ ስለሆነ በምናኔ ውስጥ ያለ ባልንጀራ ሥጋውን ይዞ ይጓዛል እንጂ ብቻውን አይጓዝም። ጾም ማለት የተራበ ሥጋ ማለት አይደለም የመነነ ሥጋ እንጂ።

ጾም የሥጋ ረሀብ አይደለም የሥጋ ልዕልና እና ንጽህና እንጂ ለመብላት የሚናፍቅ የሚራብ ሰውነት ያለበት ሁኔታ ማለትም አይደለም፤ መብላት ዋጋውን የሚያጣበትና ሰውነት ለመብላት ካለው ፍላጎት ራሱን የሚያላቅቅበት ሁኔታ እንጂ።

ጾም ነፍስ ከፍ ብላ ሥጋን ከእርስዋ ጋር ከፍ የምታደርግበት ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ ሥጋ ጓዙንና ሸክሙን የሚያራግፍበት ጊዜ ስለሆነ እግዚአብሔር ያለ ምንም እገዳ ለመንፈሳዊ ዘላለማዊነት ደስታ የሚሠራበት ጊዜ ይሆናል።

ጾም ማለት ነፍስና ሥጋ በኀብረት መንፈሳዊ ተግባር ለማከናውን የሚጠቀሙበት ጊዜ ነው። በጾም ወቅት ነፍስና ሥጋ የነፍስን ሥራ ለመሥራት ይተባበራሉ።

ይህም ማለት ለጸሎት ለተመስጦ ለክብርና ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆን ሕይወትን ለመጋራት ይተባበራሉ ማለት ነው።

ብጹዕነታቸው አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ