Get Mystery Box with random crypto!

'ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ' ፊል 4፥4 አንተ ደስታህን ከሰዎች አትጠብቅ ሰዎች ባስደ | ትምህርተ አበው

"ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ" ፊል 4፥4

አንተ ደስታህን ከሰዎች አትጠብቅ ሰዎች ባስደሰቱህ ቅጽበት ያስከፉካል ምድራዊ የሆነ ደስታ ፍጹም አይደለም ዘለቄታም ላይኖረው ይችላል ደስታህ በዚህ ምድር አይሁን ይልቁኑ ፍፁም ደስታ ከላይ መሆኑን አስተውል (ያዕ1፥17) ስለዚህ ደስታህን ከሰዎች አትጠብቅ ደስታህንም በዚህ ምድር አላፊ በሆነ ቁሳቁስም አትወስን።

በጌታ ግን ሁሌ ጊዜ ደስ ይበልህ በማግኘትም በማጣትም፤በማትረፍም በመክሰረም፤
በመራብም በመጥገብም......
በሁሉ ደስ ይበልህ ዛሬ ያስከፋህ ማጣት ነገ ያስደስትሃልና ተስፋ ሰንቅ እንጂ ተስፋ አትቁረጥ እግዚአብሔር በሙላት ብቻ የሚመሰገን አምላክ አይደለም በማጣትም ጭምር እንጂ (ኢዮ 1፥17) እግዚአብሔር በመስጠት ብቻ የሚያስደስት አይደለም እኛ ልጆቹ ቀኝና ግራችንን የማናውቅ ነንና በመከልከልም ጭምር ነው (ማቴ 20፥22) ስለዚህ ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበልህ።

በእግዚአብሐር ለመደሰት ጎተራህ ሙሉ መሆን አይጠበቅበትም፣
በህይወትህ ስኬታማ መሆን አይጠበቅብህም፣መሻቶችህ በሙሉ ሊሟሉ አይገባቸውም፣ብቻ ምንም ሳይኖረንም በጌታ ደስ ይበልህ ምንም የሌለን ሲመስለን ባለ ፀጎች ነንና (2ቆሮ 6፥15) ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን ሁሌ ጊዜ በጌታ ደስ ይበለን።

ማስተዋል እየተሳነህ ነው እንጂ የሉኝም ከምትላቸው ቁሳቁሶች ይልቅ በነፃ የተሰጠህ ዋጋ የማንትከፍልባቸው ብዙ ጸጋዎች አሉህ እስኪ አስተውል ማየት የሚያስከፍል ቢሆን፣መስማት የሚያስከፍል ቢሆን፣የሚተነፍሰው አየር የሚያስከፍል ቢሆን....... የምድር ኑሮህ ህልውና ውስጥ ይወድቅ ነበር። ምን አለኝ የሚለውን ትተህ በተሰጡህ ጸጋዎች ደስ ተሰኝተህ አመስግን።

ይልቅስ ሁላችንም ከነብዩ ዕንባቆም ጋር አብረን ደስተኞች እንሁን
"ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፥ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፥ የወይራ ሥራ ቢጐድል፥ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፥ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፥ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ፥እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ"
ዕንባቆም 3፥17

"የክርስቶስን ምሥጢር እንድንነግር እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤
ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ" ቆላ 4፥3



ዲ/ን ፍቃዱ ጎንፋ (ዘፍቁረእግዚእ)
ሐምሌ2፥2014ዓ.ም