Get Mystery Box with random crypto!

ሩቅ አላሚው የቀድሞ የሙስሊም ወጣቶች ድርጅት 12ተኛ ክፍል ጨርሰው ለሚንከራተቱ ወጣቶች የውጭ የ | ፈትህ አባቦራ መስጂድ

ሩቅ አላሚው የቀድሞ የሙስሊም ወጣቶች ድርጅት

12ተኛ ክፍል ጨርሰው ለሚንከራተቱ ወጣቶች የውጭ የትምህርት እድል ሲያመቻች የነበረው የሙስሊም ወጣቶች ድርጅት
===============================
ያለፈን ጊዜ ገጽታ ለመረዳት በወቅቱ ይጻፉ የነበሩ ነገሮችን ማንበብ፣ሰዎችን መጠየቅ አንዱ መንገድ ነው ። ሰሞኑን በ1980ዎቹ ይታተሙ የነበሩ መጽሄቶችን ሳገላብጥ የማነበው ነገር እጅግ የሚያስገርም እና የሚያስደምም ሁኖ አግኝቼዋለሁ ።

በሰዓቱ የነበሩ ኡለማዎች፣ምሁራን ምን ያህል ተራማጅ እንደነበሩ አርቆ አሳቢነታቸውን ጭምር ያስታውልኩበት ነው ። ምናልባት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በዚህ ዘመን ራሱ የነሱን ያህል ሰፋ ያለ ራዕይ አለን ወይ ? ብየ ለማሰብ በግሌ እቸገራለሁ ። ለአብነት ያህል በ1980ዎቹ በሀገራችን ገነው ከነበሩ ማህበራት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ማህበር (ሙነዘማ ) አንዱ ነበር ። በሸይኽ ሰዒድ አህመድ ሙስጠፋ ይመራ የነበረው ይህ ታላቅ ማህበር በርካታ ተግባራትን ያከናወነ፣በሀገራችን የተለያዩ ቦታዎችም ላይ ቅርንጫፍ የነበረው ማህበር ነው ።

ካስደነቁኝ ተግባራቱ መካከል ለዛሬ አንዱን ላካፍላችሁ ።

ሙነዘማ በሰዓቱ በሶስት ቋንቋዎች በአማርኛ፣በእንግሊዝኛ እና በአረብኛ ያሳትመው የነበረ ዳዕዋ የተሰኘ መጽሄት ነበረው ። መጽሄቱ በሁለተኛ እትሙ ላይ ማህበሩ ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ባወጣው ዜና ላይ እንዲህ ይላል ።

የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ድርጅት ካሉት ዓላማዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው የሙስሊሙን ሁለተናዊ ግንዛቤ ማስፋት እና ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያበርክቱ ማዘጋጀት ነው ። ይህንኑ ዓላማ በተግባር ለመተርጎም ወጥኖ ከያዛቸው ፕሮግራሞች መካከል የ12ተኛ ክፍል ፈተና አጠናቀው የሚንከራተቱ ወጣቶችን ለመርዳት ና የሙስሊም ምሁራንን ቁጥር ለማበርከት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ዩንቨርስቲዎች ጋር በመጻጻፍ ተማሪዎች የውጭ የትምህርት እድል እንዲያገኙ አድርጓል። በዚህም ጥረቱ 22 ተማሪዎችን ወደ ተለያዩ ቦታዎች አወዳድሮ መላኩ ይታወሳል ።
ይህ በንዲህ እንዳለ  44 ወንዶች እና 11 ሴቶች በድምሩ 55 ወጣት ተማሪዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የውጭ የትምህርት እድል እንዲያገኙ በማድረግ ሰሞኑን ለጉዞ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል ይላል ።
----

ልብ በሉ ይህ እንግዲህ የዛሬ 30 አመት ገደማ የነበረው የኢትዮጵያ ሙስሊም ወጣቶች ማህበር ሲሰራ ከነበረው ስራ አንዱ ነው ። ዛሬ በዚህ ደረጃ ከፍ ያለ ውጥን ወጥነን እየሰራን ነው ወይ ? የሚለውን ራሳችንን እንጠይቅ ። በነገራችን ማህበሩ እንደዛ እያደረገ ወደ ውጭ ሲልካቸው የነበረው ዩንቨርስቲ መግባት ያልቻሉት ባክነው እንዳይቀሩ ነው ። ዛሬስ የት ነን ? የተማረው ቁጥር ከትላንት ዛሬ ቁጥሩ በርክቷል ። ከዚህ መካከል ለትውልዱ፣የትምህርት እድል፣የስራ እድል ላላገኘው የሚጨነቀው የትኛው ነው ?
ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ብርሃን እንሁን ። ከትላንት ከፍ እንበል ! በነገራችን ሙነዘማን በተመለከተ እንደ ሃሩን ሚዲያ ተከታታይ ዶክመንተሪ የመስራት እቅድ አለን ። መረጃ ልታካፍሉን፣በማንኛውም መንገድ ልታግዙን ለምትሹ በራችን ክፍት ነው ።

(አብዱረሂም አህመድ )
Abdurahim Ahmed




https://t.me/fethmedia
https://t.me/fethmedia
https://t.me/fethmedia