Get Mystery Box with random crypto!

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞ ✞✞✞ እንኩዋን ለቅ | የደብረ ዘይት ደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል ወ ደብረ ብስራት ቅዱስ ገብርኤል ፈለገ ጥበብ ሰንበት ት/ቤት መዝሙር እና ኪነ-ጥበብ ክፍል(የፈ/ጥ/ሰ/ት/ቤት ደብረ ዘይት)

✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞

✞✞✞ እንኩዋን ለቅዱሳን "ሠለስቱ ደቂቅ" እና "አባ ሖር ገዳማዊ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞

" ታኅሣሥ 2 "

+*" ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ "*+

=>አናንያ: አዛርያና ሚሳኤልን እንዲያው በቀድሞው አጠራር ሠለስቱ ደቂቅ (ሦስቱ ሕጻናት) እንላቸዋለን እንጂ ለእኛስ በእድሜም: በጸጋም: በትሩፋትም አባቶቻችን ናቸው::

+ቅዱሳኑ የወቅቱ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአቄም ልጆች ናቸው:: ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን አቃጥሎ ሕዝቡን ሲማርክ አብረው ተማርከው ባቢሎን ወርደዋል::

+ንጉሡ ከምርኮ ወጣቶች ለቤተ መንግስት ሲመርጥ ሦስቱ ቅዱሳንና ዳንኤል ተመርጠው የምቾት ሕይወት ተዘጋጅቶላቸው ነበር:: ነገር ግን በምግብና በአምልኮ ከአሕዛብ ጋር መተባበርን አልፈለጉምና ምርጫቸው ጾምና ጸሎት ከቆሎ ጋር ሆነ:: ምንም እንኩዋ በቤተ መንግስት ውስጥ ቢኖሩ: ምንም የነገሥታት ልጆች ቢሆኑ ለእነርሱ ከእግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ አልነበረምና በጥሬ ቆሎ ተወስነው ኖሩ::

+አምላካቸው ከሃሊ ነውና በውበትም ሆነ በጥበብ በባቢሎን ምድር ከነርሱ የሚደርስ አልተገኘም:: ንጉሡም በባቢሎንና በአውራጃዋ ላይ ሾማቸው:: ስማቸውንም በአማልክቱ ስም ሲድራቅ: ሚሳቅና አብደናጐ አላቸው::

+ከነገር ሁሉ በሁዋላ አሕዛብ ቀንተውባቸዋልና የክፋት አዋጅን አሳወጁ:: ናቡከደነጾር 60 ክንድ ቁመት ያለውን የወርቅ ምስል አቁሞ ስገዱ ቢላቸው አይሆንም በማለታቸው ተቃጥለው እንዲሞቱ እሳት ተፈረደባቸው:: ነበልባሉ ከጉድጉዋዱ ወደ ላይ 49 ክንድ ቢነድም ቅንጣት ያህል ፍርሃት አልጎበኛቸውም::

+ወደ እሳቱም ሲጥሏቸው መልዐከ አድኅኖ ቅዱስ ገብርኤል ደርሶ አዳናቸው:: ከሆነው ነገር የተነሳም አሕዛብ አፈሩ:: ናቡከደነጾር ግን ከዙፋኑ ተነስቶ የቅዱሳኑን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ::

+ከዚያች ቀን በሁዋላ አናንያ: አዛርያና ሚሳኤል በአት አጽንተው: በጾምና በጸሎት ተወስነው ኑረዋል:: ነፍሳቸው ከሥጋቸው ስትለይ ታላቅ ንውጽውጽታ ሆኗል:: ቅዱስ ዳንኤልና ናቡከደነጾር ተሯሩጠው ቢሄዱ ሦስቱም በአንድነት ዐርፈው ተገኝተዋል:: ንጉሡ በእጅጉ ይወዳቸው ነበርና በወርቅ በተለበጠ ሳጥን ቀብሯቸዋል:: ስሞት ከመካከላቸው ቅበሩኝ በማለቱ ዛሬ ድረስ ለበቁ አባቶች የአራቱ መቃብር ባቢሎን ውስጥ ይታያል::

+ቅዱሳን አናንያ: አዛርያና ሚሳኤል (ሲድራቅ: ሚሳቅና አብደናጐ) ያረፉት ግንቦት 10 ቀን ሲሆን ዘመኑም ከክርስቶስ 500 ዓመት በፊት ነው:: ይህቺ ዕለት ደግሞ ናቡከደነጾር ወደ እሳት ሲጥላቸው መልአከ እግዚአብሔር እነርሱን ያዳነበት ቀን ናት::

+አምላካቸው ከአሳት ባወጣቸው በዚህ ቀንም:-
"ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ::
ስቡሕኒ ውዕቱ ወልዑልኒ ውዕቱ ለዓለም::" የሚለውን ምስጋና ፈጣሪ ገልጾላቸው ደርሰውታል:: በእሳቱ ውስጥ ሆነው ተናግረውታል::

+ድርሰታቸው 2 ወገን ሲሆን ባለ ስድስት አንቀጹ ምስጋናቸው ከ600 ዓመት በሁዋላ ክርስቶስ እንደሚወለድ የሚያሳይ ነው:: ሌላኛውና 33 አንቀጾች ያሉት ምስጋናቸው ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ለ33 ዓመታት እንደሚመላለስ ያጠይቃል::

+ቅዱሳን ሠለስቱ ደቂቅ ካረፉ ከ900 ዓመታት በሁዋላ (ማለትም ከክርስቶስ ልደት በ400 ዓመታት) ታላቁ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ቤተ ክርስቲያንን አንጾላቸው ነበርና አጽማቸውን ሊያገኝ ተመኘ::

+ወዳጁን ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ጠርቶ "አባ! አጽመ ቅዱሳንን ባቢሎን ወርደህ አምጣልኝ?" አለው:: ቅዱሱ ሐጺር ዮሐንስም በደመና ተጭኖ ባቢሎን ገባ:: በቅዱሳኑ መቃብር ፊትም ሰግዶ አለቀሰ:: ሠለስቱ ደቂቅም "ወዳጃችን! ምን ሆንክ?" አሉት::

+ቅዱሱም መልሶ "ወደ ግብጽ እንሒድ:: አባ ቴዎፍሎስ ይፈልጋቹሃል" አላቸው:: እነሱም "ለቅዱሱ ቴዎፍሎስ እንዲህ በለው:: እግዚአብሔር ዋጋህን ይክፈልህ:: ግን አጽማችን እስከ ዓለም ፍጻሜ ባቢሎንን አይለቅም:: ለክብርህ ግን እንመጣለን::"

+"ለምልክትም ይሆን ዘንድ መብራት ሳታበራ በሌሊት ጠብቀን በለው" ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺርን ባርከው ሸኙት:: ሐጺርም መጥቶ መልአክቱን አደረሰ:: በዕለተ ቅዳሴ ቤታቸው ቅዱሳን:- ቴዎፍሎስ: ቄርሎስ: ሐጺር ዮሐንስና ሌሎችም ከምዕመናን ጋር በጨለማ ሳሉ ቤተ ክርስቲያኑ ቦግ ብሎ በራ::

+እጅግ የሚደነቅ ብርሃንም ከበባቸው:: በብርሃኑ መካከል ሠለስቱ ደቂቅ ሲያልፉ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ሕዝቡም በደስታና በዝማሬ የቅዱሳኑን ቅዳሴ ቤት አክብሯል::

+"+ አባ ሖር ገዳማዊ +"+

=>በዚህ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን ከጻድቃንም: ከሰማዕታትም አሉ:: ከጻድቃኑ መካክል: በተለይም ከታላላቆቹ አንዱ ቅዱስ አባ ሖር ነው:: አባ ሖር በዘመነ ጻድቃን የነበረና በደግነቱ የሚታወቅ ክርስቲያን ነው::

+በዓለም ያለውን በጐነት ሲፈጽም ድንግልናውን እንደ ጠበቀ ገዳም ገባ:: በዚያም በአገልግሎት ተጠምዶ ዘመናትን አሳለፈ:: ከዚያም መነኮሰ:: ከመነኮሰ በሁዋላ ደግሞ አበውን በማገልገል: በጾምና በጸሎት: በበጐው ትሕርምት ሁሉ የተጠመደ ሆነ:: ግራ ቀኝ የማይል ("ጽኑዕ ከመ ዓምድ ዘኢያንቀለቅል" እንዲሉ አበው) ብርቱ ምሰሶ ሆነ::

+ሰይጣንም አባ ሖርን በብዙ ጐዳና ፈተነው:: ከእርሱ ጋር መታገል ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት በገሃድ ተገለጠለት:: "አንተኮ የምታሸንፈኝ በአበው መካከል ስለ ሆንክ ነው:: በበርሃ ብቻህን ባገኝህ ግን እጥልሃለሁ" ሲል ተፈካከረው::

+አባ ሖርም የዳዊትን መዝሙር እየዘመረ ጭው ወዳለ በርሃ ገባ:: በዚያም ሰይጣን ታገለው:: ግን ሊያሸንፈው አልቻለም:: ምክንያቱም ኃያሉ እግዚአብሔር ከጻድቁ ጋር ነበርና:: ሰይጣን እንደ ተሸነፈ ሲያውቅ እንደ ገና ሌላ ምክንያት ፈጠረ::

+አሁንም በገሃድ ተገልጦ ተናገረው:: "በዚህ በበርሃ ማንም በሌለበት ብታሸንፈኝ ምኑ ይደንቃል! ወደ ከተማ ብትሔድ ግን አትችለኝም" አለው:: ቅዱስ ሖር ግን አሁንም ሰይጣንን ያሳፍር ዘንድ በፈጣሪው ኃይል ተመክቶ ወደ ዓለም ወጣ::

+"እግዚአብሔር ያበርሕ ሊተ ወያድኅነኒ: ምንትኑ ያፈርሃኒ - እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው:: የሚያስፈራኝ ማነው!" ሲል (መዝ. 26:1) ይጸልይ ነበር:: በከተማም በነበረው ቆይታ አልባሌ ሰው መስሎ ደካሞችን ሲረዳ: ነዳያንን ሲንከባከብ: ለድሆች ውሃ ሲቀዳ: እንጨት ሲሰብር ይውልና ሌሊት እንደ ምሰሶ ተተክሎ ሲጸልይ ያድራል::

+ሰይጣን በዚህም እንዳላሸነፈው ሲያውቅ ከሰዎች ጋር በሐሰት ሊያጣላው ሞከረ:: ፈረስ ረግጦ የገደለውን አንድ ሕጻን ሲያይ ሰይጣን ሰው መስሎ ወደ አባ ሖር እየጠቆመ "እርሱ ነው ረግጦ የገደለው" አላቸው:: የሕጻኑ ወገኖች ቅዱሱን ሲይዙት አባ ሖር "ቆዩኝማ" ብሎ የሞተውን ሕጻን አንስቶ ታቀፈው::

+ጸልዮ በመስቀል ምልክት አማተበበትና "እፍ" ቢልበት ሕጻኑ ከሞት ተነሳ:: ለወላጆቹም ሰጣቸው:: ይሕንን ድንቅ የተመለከቱ የእስክንድርያ ሰዎችም ይባርካቸው ዘንድ ሲጠጉት ተሰውሯቸው በርሃ ገባ:: ውዳሴ ከንቱን ፈጽሞ ይጠላት ነበርና::

+ጻድቁ አባ ሖር ቀሪ ዘመኑን በበርሃ አሳልፎ በዚህች ቀን በክብር ዐርፏል::