Get Mystery Box with random crypto!

ለይለተልቀድር በአይን ትታያለች አንዳንዶች እግራቸውን ዘርግተው ወሬያቸውን እየፈጩ ሰማይ ሰማይ | 💫ፈዕለም የቁርአን ማእከል💫

ለይለተልቀድር በአይን ትታያለች

አንዳንዶች እግራቸውን ዘርግተው ወሬያቸውን እየፈጩ ሰማይ ሰማይ ያንጋጥጣሉ፡፡ የሚጠባበቁት ተወርዋሪ ኮከብ ነው፡፡ እሱን ሲያልፍ ሲመለከቱ “አኑረን አክብረን” ብለው በህብረት ይንጫጫሉ፡፡ ይሄ እዚህ ግባ የማይባል ባዶ እምነት ነው፡፡ ለይለተልቀድር አላህ በአንዳንድ ባሮቹ ቀልብ ላይ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ የመረጋጋት ወይም የመለየት ስሜት ከማሳደሩ ውጭ በአይን የሚታይ ነገር አይደለም፡፡ የሚታየው ምልክቶቿ እንጂ እራሷ አይደለችም።

ነገር ግን ሰዎች ሊጠመዱ የሚገባቸውም በዒባዳ፣ በዚክር፣ በሶላት፣ በዱዓእ፣ በቁርኣን እንጂ በወሬ መሆን የለበትም፡፡ ሰዎች የሚጠበቅባቸውን ከተወጡ ለሊቱ ለይለተልቀድር መሆኑን ባያውቁ እንኳን ትሩፋቷን አያጡም፡፡

ለይለተልቀድር እንደሆነ ውስጡ ያደረ ሰው ምን ያድርግ?

በተለይ ደግሞ ለሊቱ ለይለተልቀድር እንደሚሆን ውስጣችንን ከተሰማን ይበልጥ ልናተኩርበት የሚገባን ዱዓእ “አልሏሁመ ኢንነከ ዐፉውዉን ቱሒቡልዐፍወ ፈዕፉ ዐኒ” (“ጌታዬ ሆይ! አንተ በርግጥም ይቅር ባይ ነህ፡፡ ይቅር ማለትን ትወዳለህ፡፡ ስለሆነም ከኔ ይቅር በለኝ” የሚለው ነው።
[አልባኒ ሶሒሕ ብለውታል]

ስለዚህ ዋናው ልናተኩርበት የሚገባን በዱንያም በአኺራም ከአላህ ይቅርታን እንድናገኝ መጣጣር ነው፡፡

ግን ለምን አላህ ለይለተልቀድርን ስውር አደረጋት?

ዑለማዎች እንደሚሉት ታላላቅ ትሩፋቶች በሚገኝባቸው የረመዳን የመጨረሻ ለሊቶች ሙስሊሞች በዒባዳህ ይበራቱና ይጠናከሩ ዘንድ ነው አላህ ይቺን ለሊት ስውር ያደረጋት፡፡ እናም ለይለተልቀድርን እንዳታመልጣቸው ሲጣጣሩ ለይተው ቢያውቋት ሊኖራቸው ከሚገባው በበለጠ ይበልጥ በዒባዳህ ላይ ይቆያሉ፣ ይነቃቃሉም፡፡ በዚህም ይበልጥ ይጠቀማሉ፡፡ ለይተው ቢያውቋት ግን እሷ ብቻ ላይ አነጣጥረው ሌሎቹን ለሊቶች ሊዘናጉ ይችሉ ነበር፡፡ እናም መሰወሯ ነብዩ ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም እንዳሉት ለኛ ኸይር ነው፡፡ [ቡኻሪ]

አላህ ይቺን ታላቅ ለሊት ያድለን፡፡ የምንጠቀምባትም ያድርገን፡፡ ኣሚን፡፡
መልካም ሆኖ ካገኙት ሼር ማድረግ እንዳይረሱ፡፡ ሌሎችንም ተጠቃሚ ያድርጉ፡፡

(ኢብኑ ሙነወር...ሰኔ 29/2007

@IbnuMunewor