Get Mystery Box with random crypto!

በአዲስ አበባ የተገደለው የፋኖ አባል ሽኝት አስክሬን በሌለበት ጎንደር ውስጥ ተደረገ #FastMer | FastMereja.com

በአዲስ አበባ የተገደለው የፋኖ አባል ሽኝት አስክሬን በሌለበት ጎንደር ውስጥ ተደረገ
#FastMereja
ባለፈው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ ከፖሊስ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የተገደሉት ሁለት የፋኖ አባላት ቤተሰቦች አስከሬናቸውን ሳያገኙ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ጎንደር ውስጥ መፈጸማቸውን ተናገሩ።

ፖሊስ በአማራ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የፋኖ ቡድን አባላት ናቸው ያላቸው ናሁሰናይ አንዳርጌ እና አቤኔዘር ጋሻው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሽብር ድርጊት ሊፈጽሙ ሲሉ ደርሶባቸው መገደላቸውን መግለጹ ይታወሳል።

የሁለቱ ወጣቶችን ሞት ተከትሎ ወላጆቻቸው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አስከሬናቸውን አግኝተው ቀብር ለመፈጸም ለፌደራል ፖሊስ እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ ሳያገኙ ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ መጠበቃቸውን ተናግረዋል።

በወቅቱ የሁለቱ ሟቾች እናቶች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፖሊስ አስከሬናቸውን ሰጥቷቸው ከቤተሰብ እና ከዘመድ ጋር ለመቅበር ለቀናት አዲስ አበባ ቢቆዩም ምላሽ ሳያገኙ በመቅረታቸው ሐዘናቸው መክበዱን ገልጸው ነበር።

ዛሬ ግንቦት 26/2016 ዓ.ም. ጎንደር ውስጥ አስከሬኑ በሌለበት በባህላዊ መንገድ በቤተሰብ እና በወዳጆች የሽኝት ሥነ ሥርዓቱ የተፈጸመው የናሁሰናይ አንዳር ጌ ሲሆን፣ በዚህም ወቅት በርካታ ሕዝብ ታድሞ እንደነበር አንድ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአቤኔዘር ጋሻው የሽኝት ሥነ ሥርዓትም በተመሳሳይ ቤተሰቡ አስከሬኑ ባላገኘበት ሁኔታ ቀደም ብሎ መከናወኑን የቤተሰቡ አባላት ገልጸዋል።

ሚያዝያ 4/2016 ዓ.ም. ፖሊስ የፋኖ ቡድን አባላት ናቸው ያላቸው ናሁሰናይ አንዳርጌ እና አቤኔዘር ጋሻው ከሀብታሙ አንዳርጌ ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ “የሽበር ጥቃት ለመፈፀም ተልዕኮ ይዘው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የፀጥታ ኃይሉ ደርሶበት” በተደረገ የተኩስ ልውውጥ መገደላቸውን ማስታወቁ አይዘነጋም።

ለሁለት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ አስከሬናቸውን ለማግኘት ቤተሰባቸው ለፖሊስ እና ለሚመለከታቸው የፌደራሉ መንግሥት አካላት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያርቡም ምላሽ ሳያገኙ መቅረታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የናሁሰናይ ቤተሰብ እንዳሉት አስክሬን ለማግኘት በአዲስ አበባ ፖሊስ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ድረስ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

“ሁለት ወር ሊሞላው ትንሽ ቀን ነው የቀሩት። ብዙ ደከምን። ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ ጠይቀን ምላሽ ስናጣ ተስፋ ቆረጥን።”

የሁለቱን ሟቾች አስከሬን አግኝተው ለመቅበር ቤተሰቦቻቸው ለፌደራል ፖሊስም ሆነ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ላቀረቡት ጥያቄ ሲሰጣቸው የነበረው ምላሽ “እኛን አይመለከትም” የሚል መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ ቤተሰቡ ለሟቾች ሽኝት ለማድረግ እና እርም ለማውጣት በአካባቢው ‘ደመር’ ተብሎ በሚታወቀው ባህላዊ ሥነ ሥርዓት አማካይነት ሐዘናቸውን ለመወጣት መወሰናቸውን የቤተሰብ አባሉ ገልጸዋል።

በዚህም ለናሁሰናይ አንዳርጌ ዘመድ አዝማድ እና ሌሎች ለቀስተኞች በተገኙበት ዛሬ ሰኞ ግንቦት 26/2016 ዓ.ም. ጉንደር ከተማ ውስጥ በሚገኘው አባ ጃሌ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ፍትሃት እና የሽኝት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የቤተሰብ አባል እና አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ በከተማው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ተሰማርተው እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

እንደ ቤተሰብ አባሉ ገለጻ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ለቀስተኛ ካለ አስከሬን በተካሄደው የስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደም ወደ ቤተ-ክርስቲያን እያመራ ሳለ “የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች የናሁሰናይ ፎቶ እና ስም ያለበትን ባነር በኃይል ተቀብለዋል” ብለዋል።

“ፒያሳ አደባባይ ስንደርስ ባነሮቹን አምጡ ሲሉ እኔ እራሴ እንዲወስዱ እንዲፈቀድላቸው አድረግሁ፤ ሁለት ባነሮች ወስደዋል። ከዚህ ውጪ የተፈጠረ ምንም ነገር የለም” ሲሉ አብራርተዋል።

በባነሮቹ ላይ ሰፍሮ የነበረው የናሁሰናይ ሙሉ ስም እና ማዕረግ፣ የትውድ ቀን እና ሕይወቱ ያለፈበት ቀን መሆኑን የቤተሰብ አባሉ ተናግረዋል።

ከናሁሰናይ ጋር አዲስ አበባ ላይ ተገድሎ የነበረው ሌላኛው የፋኖ አባል የአቤኔዘር ጋሻው ተመሳሳይ የደመር ሥነ ሥርዓት ቀደም ብሎ መከናወኑን እኒሁ የቤተሰብ አባል ጨምረው አስታውሰዋል።

ሚያዚያ 4/2016 ዓ.ም. ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ ከፖሊስ ጋር በተካሄደ የተኩስ ለውውጥ “ፋኖ መሪ ናሁሰናይ አንዳርጌ ቆስሎ ወደ ህክምና ከተላከ በኋላ ሲሞት፣ አቤኔዘር ጋሻው በተኩስ ልውውጡ ወቅት ተገድሏል” ሲል ፖሊስ መግለጹ ይታወሳል።

አዲስ አበባ ውስጥ በፖሊስ ከተገደሉት ሁለቱ በተጨማሪ ሀብታሙ አንድአርጌ የተባለው የቡድኑ አባል ጉዳት ሳይደርስበት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን እና በተኩስ ለውውጡ ወቅት አንድ ግለሰብ መገደላቸውን እንዲሁም ሁለት የፖሊስ አባላት መቁሰላቸው አሳውቆ ነበር።

ዘገባው የቢቢሲ አማርኛ ነው።