Get Mystery Box with random crypto!

ሕይወት ረጅም ጉዞ ነው! ዘመን ጎዳና ነው! ሕይወት ረጅም ጉዞ ነው፤ ሠው መንገደኛ ነው፡፡ ዘመ | እውቀትን ፍለጋ

ሕይወት ረጅም ጉዞ ነው! ዘመን ጎዳና ነው!

ሕይወት ረጅም ጉዞ ነው፤ ሠው መንገደኛ ነው፡፡ ዘመን ጎዳና ነው፡፡ ወሳጁ አዕምሮ ነው፡፡ ተሳፋሪው ልብ ነው፡፡ ሠው በየዕለቱ፣ በየሠዓቱና በየደቂቃው ጉዞ ላይ ነው፡፡ ጉዞውን በአቋራጭ ለመሄድ የሚሞክር አለ፡፡ ቀጥተኛውን መንገድ ይዞ ሳይታክትና ሳይደክም የአስተሳሰብ ውሃ ጥሙን፣ የአመለካከት በረሃውን ችሎ፣ አደናቃፊውን ሽፍታ ሃሳብ እያለፈ ወደዕጣፋንታው የሚነጉድም ብዙ ነው፡፡ የዘመንን ጎዳና አሳምሮ የሚመላለስ አለ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ የሕይወት መንገዱን እያበላሸ፣ ድልድዩን ሃሳብ እያፈረሠ፣ የትውልድ ባህሩን እያደፈረሠ፤ እኔ ብቻ ልለፍ እንጂ ሌላኛው የራሱ ጉዳይ ብሎ ኋላውንና ጎኑን ሳያይ፣ ሌላውን መንገደኛ ትቶና ንቆ ፊቱን ብቻ እያየ የሚጓዝ አለ፡፡ የሕይወት ጎዳና ማለቂያውና መጨረሻው ሞት መሆኑን የተረዳ ግን የሕይወት እርምጃው የተስተካከለ ይሆናል፡፡

ጋሊኖስ የተባለ ፈላስፋ እንዲህ ይለናል፡-

‹‹በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሠዎች ሁሉ አኗኗራቸው የመንገደኛ አኗኗር መሆኑን ሊያውቁ ይገባቸዋል፡፡ መንገደኛ ከደረሠበት ሐገር አድሮ ሲነጋ ተነሥቶ እንደሚሄድ ሁሉ እነሱም ከዚች ዓለም በሞት ተለይተው ይሄዳሉ፡፡›› በማለት የዓለም እንግድነታችንን ይናገራል፡፡

ብልህ ሠው ጉዞውን በድንብርብር አይጀምርም፡፡ አስቀድሞ በደመነፍስ ከመድፈር ይልቅ በመጠንቀቅ ጉዞውን ያጠናል፡፡ ጥንቁቅነት ፍራቻ አይደለምና ጥንቃቄው እንዲማር ያደርገዋል፡፡ ከተማረም ያያል፤ ካየም ያስተውላል፡፡ ካስተዋለም ዕውቀት ይኖረዋል፡፡ ዕውቀት ካለውም ይሠራል፡፡ ከሠራም ስጋዊ ዓለሙን አሸንፎ የወዲያኛው ዓለሙን በዕውቀትም፣ በግብርም፣ በእምነትም፣ በምክንያትም ይገነባል፡፡ ‹‹ካልተማሩ አያውቁ፣ ካላወቁ አይጸድቁ›› እንዲሉ አበው የሕይወት ጉዞው ስኬታማ ይሆናል፡፡

ሠው በውስጡም በውጪም ተጓዥ ነው፡፡ ሞኝ ሠው በራሱ ባልሆነ መንገድ የሌላን ሠው ዳና እየተከተለ ገደል ይገባል፡፡ ብልሕ ሠው ግን ራሱንና የራሱን መንገድ ለማግኘት ይጓዛል፡፡ ውስጣዊው ጉዞው የነፍስ ሲሆን፤ ውጫዊው ጉዞ የስጋ ነው፡፡ የነፍስ ጉዞው አሻጋሪ ሲሆን፤ የስጋው ጉዞው ግን የሆነ ጊዜ ላይ አላቂ ነው፡፡ ዕድሜ ገደብ አለው፡፡ የነፍስ ጉዞ የሃሳብ ሸንተረሩን አልፎ፣ ዳገትና ቁልቁለቱን ወርዶ ሠብዓዊነቱ ጋር ይደርሳል፡፡ የስጋዊ ጉዞ ግን ማጠናቀቂያው ሞት ነው፡፡

ከነገስታት አንዱ ዘመን እንዴት ያለ ነው ብሎ አንዱን ፈላስፋ ቢጠይቅ፡- ‹‹ዘመን ማለት አንተ ነህ፡፡ አንተ ሠላማዊ ስትሆን ዘመን ሠላማዊ ይሆናል፡፡ አንተ የከፋህ እንደሆነ እንዲሁ ይከፋል›› አለው ይባላል፡፡

እውነት ነው! ሠው ዘመኑን መፍጠር ባይችልም በዕድሜው ላይ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ጫና መፍጠር ይችላል፡፡ ሠው የራሱ ሠዓሊ ነው፡፡ ቀለሙ አስተሳሰቡ ነው፡፡ ሠሌዳው ሕይወቱ ነው፡፡ ብሩሹ ምግባርና ግብሩ ነው፡፡ በሕይወት ብሩሹ ዘመኑን አሳምሮ ይቀባል፤ አልያም አበላሽቶ አስጠዪ ያደርጋል፡፡

ዘመን ውበቱ የሚገለጠው በዘመኑ ውስጥ አፍቃሪና ተፈቃሪ አንድ የሚሆኑበት ፍቅር ሕያው ሲሆን ነው፡፡ ታናሽ ታላቁን ሲያከብር፣ ታላቅ ታናሹን ሲመክር፣ አዛውንት፣ አሮጊቶች በልጆቻቸው ተከብረው ሲጦሩ፣ ሠው በሠውነቱ ሲኖር፣ ጥላቻ፣ ጦርነት፣ መካካድ፣ መገዳደል፣ መወጋገዝ፣ መናናቅ፣ መጠላላት ወዘተ ክፉ ነገሮች ሁሉ ሲወገዱና ሲጠፉ ዘመኑ መልካም ዘመን ነው እንላለን፡፡ የዚህ ዘመን አባል የሆነ ትውልድ ጉዞው ስኬታማ ይሆናል።

ወዳጆች የዘመን ክፋቱና ክርፋቱ የሚጀምረው እርስበርስ በመለያየት ነው፡፡ ጥላቻ ፅንሠቱ ካለማወቅ የሚመነጭ ነው፡፡ ዕውቀት በፍቅር ሲሟሽ አዕምሮ በጥላቻ አይሠክርም፡፡ በጥላቻ ናላውን ያጣ ሠው የሚያደርገውን አያውቅም፡፡ አላዋቂ ሠው ዘመኑን እርም የሚያሠኝ ተግባር በገዛ እጆቹ ይፈፅማል፡፡ በፈፀመውም ክፉ ነገር ሲሰቃይ ይኖራል፡፡ በስቃዩም ደስታን ያጣል፡፡ ደስታ በማጣቱም በሕይወት ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ተስፋ በመቁረጡም ሕይወቱን ዓላማ የለሽ ይሆናል፡፡

ወዳጄ ሆይ ሕይወት ረጅም ጉዞ ነው፡፡ በዚህ ማለቂያ ባለው ጉዞ ቀሪ ታሪክ ሠርተህ ለማለፍ ልብህን በቅንነት፤ አዕምሮህን በመልካምነት መላልሶ መስራት ያስፈልግሃል፡፡ ቅንነት የጎደለው የሕይወት ጉዞ መጨረሻው አያምርም፡፡ ፍቅር ያነሠው ህይወት ብኩን ነው፡፡ ለትዝታህ የሚሆን እንኳን መልካም ነገር ማድረግ ሕይወትን ያድሳል፡፡ ስታረጅ መልካሙ ትዝታህ ያጫውትሃልና፡፡

‹‹ዘመን ማለት አንተ ነህ፡፡ አንተ ሠላማዊ ስትሆን ዘመን ሠላማዊ ይሆናል፡፡ አንተ የከፋህ እንደሆነ እንዲሁ ይከፋል››

እሸቱ ብሩ ይትባረክ

ቸር ጊዜ!
@Ewiketinfilega
@Ewiketinfilega