Get Mystery Box with random crypto!

ኦርቶዶክስን በኦርቶዶክሳውያን የማዳከም አዲስ ስልት! ባለፉት የታሪክ ገጽታዎቻችን ውስጥ በጉልበት | የኢትዮጵያ ታሪክና ጥበቦች

ኦርቶዶክስን በኦርቶዶክሳውያን የማዳከም አዲስ ስልት!

ባለፉት የታሪክ ገጽታዎቻችን ውስጥ በጉልበትና በይፋዊ ተቃርኖ ኦርቶዶክስን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ሲደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች ኹሉ አልተሳኩም፤ እንዲያውም የበለጠ ሲያጠናክሯትና ሲያስፋፏት ተስተዋሉ እንጂ፡፡ ለምሳሌ፡- በግራኝ አህመድ ወረራ ዘመን
ኦርቶዶክሳውያኑን በግዳጅ የማስለም ድርጊቶች ተፈጽመው ነበር፤ ሕዝቡም ወደ እስልምና ሲገባ አምኖበት ሳይኾን ተገዶ ስለነበር ጊዜ እስኪያልፍ በትዕግሥት ሲጠባበቅ ቆይቶ ነበር፡፡ እናም፥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እነዚያ የመከራ ዘመናት ሲያልፉ ሃይማኖታቸውን እንዲክዱ
ተገደው የነበሩ ምእመኖቿን መልሳ ወደ ጉያዋ ለመሰብሰብ እንዲያስችላት ‹‹አንቀጸ አሚን›› የተባለ የማስተማሪያ መጽሐፍ አዘጋጅታ፣ ‹‹መጽሐፈ ቄዴር›› የተባለ የማጥመቅያ ሥርዓትም
ሠርታ ተልእኮዋን መልሳ ለማጠናከር ችላለች። ኦርቶዶክሳዊነትን ለማክሰም የተሠራ ሴራ ጭራሹን እንዲጠናከር ዕድል መፍጠሩን ይኽ አንዱ የታሪክ ምስክርነት ነው፡፡
በኋላ በጣልያን ወረራ ጊዜም ካቶሊኮች የእስልምናውን ክንፍ በመደገፍ ሁለቱ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› በሚመስል መርሕ ተባብረው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ሲሠሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- በካቶሊኮቹ ሴራ ‹‹ሁለቱ እሾሆች›› የተባሉ ቅባትና ጸጋ በኢትዮጵያ ምድር በተተከሉ ጊዜ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እነርሱን ለመንቀል ትግል ላይ ስትጠመድ እስልምናው ደግሞ ድምጹን አጥፍቶ ውስጥ ውስጡን ሲስፋፋ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ በዚኽ ታሪካዊ ተሞክሮ መሠረት ደግሞ የጋራ ጠላትን እንዴት በትብብር መዋጋት እንደሚቻል ልምድ ተቀስሞበታል፤ ይበልጥ አዘምኖና አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም የታመነበት ይመስላል፡፡
አሁንም በግላጭ ኦርቶዶክሳውያንን አስገድዶ ለመጠምዘዝ መሞከር የማይታሰብ ነውና ሌላ ስልት አስፈለጋቸው! ይልቁንም፥ ተፈጥሯዊ በኾነ መንገድ (biological strategy) ቤተ ክርስቲያኒቱ ራሷን በራሷ እንድታጠፋ ኹኔታዎችን ማመቻቸት አዲሱ ስልት ተደርጎ የተያዘ ይመስላል፡፡ ይኽ ስልት አንድ እንዲጠቃ የተፈለገው ተቋም ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ መርዳት (helping the institution to self-suicide) የማድረጊያ ዘዴ ነው፡፡ ይኽ ተፈጥሯዊ
የመባሉም ምስጢር ችግሩን በሚመስል መፍትሔ የመከላከል ስልትን ስለሚከተል ነው፡፡
ለምሳሌ፡- በሥነ-ሕይወታዊ የጥናት ዘርፍ ትላትሎችን ከግብርና ሰብል ጥቃት ለመከላከል ሲፈለግ ለሰብሉ ጎጂ ያልኾኑ፣ ነገር ግን ትላትሎቹን የሚበሉ ሌሎች እንስሳት የማርባት ዘዴ
ማለት ነው፤ በዚኽ የተፈጥሮ ሚዛን (ecological balance) ይጠበቃል፡፡ ከሌሎች ስልቶች የበለጠም ውጤታማ ነው (ኬሚካልን የመሰሉ መፍትሔዎች ለጎጂ ተባዮች ተረጭተው
ጠቃሚዎቹንና ሰብሎችን ጭምር የሚያደርቁ ‹‹ጅምላ ጨራሽ›› ከመኾናቸውም በላይ ለአየር
ብክለት ስለሚያጋልጡ አይመከሩም)፡፡ ተባዮቹን የሚመስሉ ሌሎች ተጻራሪ ተባዮች ሲኾኑ ግን ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤ ስላላቸው በቀጥታ ከመገናኘታቸውም በላይ ጎጂዎቹ ተባዮችን አዘናግተው (ዘመድ መስለው) እንዲያጠቁአቸው ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡
ይኽንኑ ኹኔታ ወደ ተቋም ስናመጣው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ፊት ለፊት በመንግሥታዊ ሥልጣን ተጠቅመው፣ በሰይፍ አስፈራርተውና በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ተከራክረው ማሸነፍ
እንደማይቻል ከታሪክ የተረዱት አካላት አንድነቷን ለመክፈል መጠቀም የጀመሩት አዲሱ ስልት መኾኑ ነው፡፡ ይኽ ስልት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ በቀጥታና በይፋ የሚሰነዝረውን ጥቃት በይፋ ሳያሳውቅ (ለትችት በማያጋልጠው፣ ነገር ግን የተሻለ ውጤታማ በሚያደርገው መልኩ) እንዲያዳክማት የሚያስችላቸው ነው፡፡
ይኽ ተፈጥሯዊ ስትራቴጂ ‹‹ራስን በራስ እንዲያጠፋ የመርዳት›› መርሕን ስለሚከተል ቤተ ክህነቱ እንደተጻራሪ ክንፍ በፈረጃቸው የእስልምናና ሌሎች የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች ከመገዳደር ይልቅ በውስጡ ባሉት ሰዎቹ ተጠቅሞ፣ ስያሜውን በሚመስል ዘዴ፣ የራሱን ተልእኮ
የሚያፋጥንለት የሚመስለውን አሠራር መዘርጋት ይበልጥ ውጤታማ ያደርገዋል፡፡ መዋቅርን በመዋቅር፣ ጳጳስን በጳጳስ፣ ቤተ ክህነትን በቤተ ክህነት፣ ሲኖዶስን በሲኖዶስ፣ ማኅበራትን በማኅበራት፣ አሠራርን በአሠራር ተክቶ ከመጀመሪያው አቅጣጫዋ ወደ ሚፈለገው መሥመር ማስቀየስ፤ በሒደትም ግብዓተ መሬቷን ለመፈጸም እንደማለም ያለ ስልት ነው፡፡
ይኽ ከሰሞንኛ ኹኔታዎች አንጻር ምን ምን ነገሮችን እንድናስተውል ያደርገናል?

(1) ትናንት ‹‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነት›› እያሉ ሲያጨናንቁን የነበሩ ‹‹ኦርቶዶክሳውያን›› ወንድሞቻችን ዘግይተው ደግሞ በመስቀል አደባባይ ጉዳይ፥ ‹‹ሙስሊም ወንድሞቻችን
ቢያፈጥሩበት ምን ችግር አለበት?›› እያሉ ሲከራከሩን አስተውለናል፡፡ የገዛ ወገኖቻችን ከተቀናቃኞቻችን ጎን ኾነው ሞገቱን፤ ኦርቶዶክሳውያንን በኦርቶዶክሳውያን መዋጋት ይሏል ይኽ
ነው!

(2) ይኽንኑ ጉዳይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጠቅላይ ቤተ ክህነቷ አማካይነት ተቃውሞ ስታቀርብ መንግሥት ደግሞ የእርሷኑ ሌላ መዋቅር (የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን) ተጠቅሞ
‹‹ይቅርታ›› አስጠየቀ፤ በመዋቅራችን አማካይነት መዋቅራችንን አጠቃው ማለት ነው!

(3) ለኦርቶዶክሳዊ ቀኖናት ደንታ የሌላቸውና ከመሰል እሴቶች ሊያንሸራትቱን የሚሹ ተሓድሶዎች ‹‹ኦርቶዶክሳውያን›› መስለው፣ ለትግራይ ሕዝብም እንደተቆረቆሩ አስመስለው
በበዓለ ሃምሳ ጾም ዐወጁ፡፡ ይኽንን ሲያደርጉ ግን ‹‹የገዳም አባቶችና የትግራይ ሊቃነ ጳጳሳት አዘዋል›› እያሉ ነው፡፡ ከእኛው ጾምና ትእዛዘ አበው ጋር ታክከው የእኛኑ ቀኖና ለመናድ የሚደረግ ሌላኛው እንቅስቃሴ!

(4) በውስጣችን ኾነው፣ ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያንን አሁናዊ ጭንቀት መፍትሔ እንዳገኙ አስመስለው ‹‹ደጉ ንጉሥ ቴዎድሮስ ይገለጣል!›› የሚሉንም በዝተዋል፡፡ ለዚኽ ማሳመኛቸው
ደግሞ ‹‹ፍካረ ኢየሱስ›› እና ‹‹የገዳም አባቶች መልእክት›› የሚሉ የማግባቢያ አካሔዶችን ይጠቀማሉ፡፡ ገዳማውያኑ ግን በአንድነት ኾነው ‹‹መልእክቱ ከእኛ አይደለም!›› ማለታቸውን ልብ ይሏል፡፡

ይቀጥላል...