Get Mystery Box with random crypto!

መጥሪያ አደራረስ ሥነ -ሥርዓት እና ውጤቱ በፍትሐብሕር ጉዳይ ተከሣሽ ለሆነ ወ | Lawyer_Henok Taye⚖️Ethio Law🥇ኢትዮ ሕግ

መጥሪያ አደራረስ ሥነ -ሥርዓት እና ውጤቱ

በፍትሐብሕር ጉዳይ ተከሣሽ ለሆነ ወገን ከፍ/ቤት የሚላከውን መጥሪያ ለተከሳሹ ሊደርስ የሚችልበትን የተሻለ አማራጭ መንገድ በመለየት ሊላክ ይገባል፡፡ የመኖሪያ አድራሻው በግልፅ ለሚታወቅ ተከሳሽ ፍ/ቤቱ የሚልከውን መጥሪያ በፍ/ቤቱ ቅጥር ግቢ ብቻ እንዲለጠፍ በማድረግ ተከሳሹ አልቀረበም በሚል በሌለበት ጉዳዩ እዲታይ የሚሰጥ ውሣኔ ተገቢነት የለውም፡፡ በዚህ መንገድ በአግባቡ መጥሪያ እንዲደርሰው ያልተደረገ ተከሳሽ በሌለበት ታይቶ የተሰጠበት ውሣኔ እንዲነሣለት የሚያቀርበው አቤቱታ ተገቢነት ያለው ነው፡፡ ተከሳሽን በአግባቡ መጥራት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕጉ ከተቀመጡት የመስማት መብት ከሚረጋገጥባቸው መርሆዎች አንደ ነው፡፡ ይህን መርህ ባለመጠበቅ የሚሰጠው ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ በሕጉ አግባብ እንደተሰጠ አይቆጠርም፡፡ በመሆኑም ክሱ የቀረበለት ፍ/ቤት ወደጉዳዩ ሥረ-ነገር ገብቶ ተከሣሹን ባለዕዳ የሚያደርግ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፉት ተከሳሹን በአግባቡ ስለመጠራቱ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 105(1), 78. በሌላ በኩል ደግሞ ለተከሳሽ የተላከው መጥሪያ በጋዜጣ ጥሪ ሊደረግ የሚገባው ሌሎች አግባብነት ያላቸው የመጥሪያ አላላክ መንገዶች ቅደም ተከተላቸውን በጠበቀ መልኩ ከተከናወኑ በኋላ ነው፡፡ መጥሪያ በአግባቡ ደርሷል ለማለት የሚላክለት ሰው ስም በተሟላ ሁኔታ ተገልጾ መላክ ያለበት በአድራሻው መላክ አለበት፡፡ የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 94-110, 78, 70/ሀ/
ለአንድ የመንግስት ተቋም የተላከ መጥሪያ መጥሪያው በአግባቡ ለሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ካልደረሰ በስተቀር መጥሪያው ለተቋሙ መዝገብ ቤት ገቢ በመሆኑ ብቻ መጥሪያው እንደደረሠ ተቆጥሮ ክርክሩ ተቋሙ በሌለበት ሊታይ አይገበም፡፡ የመጥሪያ አሰጣጥ ዘዴና ቅደም ተከተል እንዲሁም መጥሪያው ለማን እንደሚሰጥ የሚመለከተው የፍትሐብሕር ሥነ ሥርዓት ሕግ ክፍል ዓይነተኛ ዓላማ ከሆኑት መካከል አንዱ ተከራካሪ ወገኖችን እኩል የመከራከር መብት እንዲኖራቸው በማድረግ ጉዳዩን ፍትሓዊ በሆነ አኳኋን ለመወሰን ማስቻል መሆኑን ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ መጥሪያ የሚደርስበትን ተገቢ መንገድና ለማን መድረስ እንዳለበት ማረጋገጥ ይገባዋል፡፡ መጥሪያ በተገቢው መንገድ ደርሶት ተከራካሪ ወገን ካልቀረበ ወይም መጥሪያን አልቀበልም ካለ ፍርድ ቤቱ ሊከተለው የሚገባው ስርዓትም በሕጉ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ ከእነዚህም ድንጋጌዎች መካከል አንደ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 70(ሀ)፣ 103፣ 104፣ 105፣ 106 እና 107 ስር የተመለከተው ሲሆን በእነዚህ ድንጋጌዎች መሰረት ተከሳሽ በላለበት ክርክሩ ታይቶ ውሳኔ ሊሰጥ የሚችለው መጥሪያው በአግባቡ የደረሰው መሆኑ ሲረጋገጥ ወይም መጥሪያውን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ ወይም ሊገኝ ያልቻለ መሆኑ ሲረጋገጥ ወይም መጥሪያውን ለመቀበሌ ፈቃደኛ አለመሆኑ ወይም ሊገኝ ያልቻለ መሆኑ ሲረጋገጥ ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ድንጋጌዎቹ መጥሪያው በትክክል ያልደረሰው መሆኑ ከተረጋገጠ ጉዳዩ ተከሳሽ በሌለበት እንዲታይ የማይታዘዝ ስለመሆኑ ያስገነዝባል፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 70(ሀ) ድንጋጌ ስር ላይ ‛መጥሪያው በትክክል መድረሱ“ የሚለው ሐረግ መኖሩም የሚያሳየው ስለመጥሪያ አሰጣጥና አደራረስ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 94 እስከ 110 ድረስ የተመለከቱት ሁኔታዎች በአግባቡ መሟላታቸውን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ አንድ ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ ታይቶ ውሳኔ ከተሰጠውም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 78 መሰረት መፍትሔ መጠየቅ የሚችል ስለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት መፍትሔ ሊጠየቅ የሚችለው አቤቱታ አቅራቢው በሚያቀርበው አቤቱታ ላይ የጥሪው ትዕዛዝ ‛በሚገባ ያልደረሰው“ መሆኑን በመጥቀስ ይህንኑ ማረጋገጥ ሲችል ነው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ድንጋጌዎች መገንዘብ የሚቻለው አንድ ሰው የመከራከር መብቱን እንደተወው የሚቆጠረው መጥሪያው በሕጉ በተዘረጋው ሥርዓትና ቅደም ተከተል መሰረት ደርሶት ክርክር ያለው መሆኑን እያወቀ ሳይቀርብ ሲቀር ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ በሕጉ የተዘረጋውን ስርዓት ተከትሎ አማራጭ የመጥሪያ አደራረስ ሥርዓት ከፈጸመ መጥሪያው ለተከሳሹ እንደደረሰ እንደሚቆጠርና በቂና ሕጋዊ ምክንያት ካለው ብቻ ወደ ክርክሩ እንድገባ የሚፈቀድ መሆኑን ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች ይዘትና መንፈስ ያስገነዝባል፡፡ ስለሆነም ማንኛውም ውሳኔ መሰጠት ያለበትም በሕጉ በተዘረጋው ሥርዓት መሰረት መጥሪያው መድረሱ በሚገባ የተረጋገጠና የተከሳሽ የመከራከር መብት የተጠበቀ መሆኑ ሲታወቅ ሊሆን ይገባል፡፡ የፍ/ሥ/ህ/ቁ 70/ሀ/፣78/2/፣96፣102
ከላይ በተመለከተው መሠረት ለተከሳሽ የተላከው መጥሪያ በአግባቡ መድረስ አለመድረሱ ሳይረጋገጥ ክርክሩ በሌለበት ይቀጥል በሚል ትዕዛዝ ተሰጥቶ ክርክሩ የቀጠለ እንደሆነ ክርክሩን ወደ ኋለ የሚመልስና ለአላስፈላጊ እንግልት የሚዳርግ ነው፡፡ ስለዚህ በሌለበት ክርክሩ ይቀጥል ለማለት መጥሪያው ለሚመለከታቸው ተከሳሾች መድረስ አለመድረሱን በአግባቡ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ መጥሪያ በአግባቡ ያልደረሰው ሰው ተከሳሽ በሌለበት የተሰጠው ውሳኔ እንድነሳለት የሚጠይቀው በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 78 መሠረት ሲሆን አንድ አንድ ጊዜ በስህተት ወይም ባለማወቅ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 358 መሠረት የውሳኔ መቃወሚያ የሚቀርብበት ጊዜም አለ፤ ይህ ደግሞ ተገቢነት ያለው አይደለም፡፡ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 358 መሠረት የውሳኔ መቃወሚያ የሚቀርበው ከጅምሩ በክርክሩ መግባት የነበረበት ግን በክርክሩ ውስጥ በከሳሽነት ወይም በተከሳሽነት ያልተጠቀሰ፤ በተሰጠው ውሳኔም መብቱ/ጥቅሙ የተነከ ሰው ነው፡፡ በክርክር ወቅት መጥሪያ አልደረሰኝም ብሎ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 358 መሠረት የውሳኔ መቃወሚያ የሥነ-ሥርዓት ህጉን የተከተለ አይደለም፡፡ የሰበር ውሳኔዎች ቅጽ 9 የመ/ቁ. 50022, ቅጽ 9 የመ/ቁ. 50376
t.me/ethiolawtips