Get Mystery Box with random crypto!

‹‹የመውጫ ፈተና በትምህርት ጥራት ያለውን ችግር አንዱ የመፍቻ አማራጭ እንጂ ብቸኛ ርምጃ አይደለም | ኢትዮ ዩኒቨርስቲ መረጃ

‹‹የመውጫ ፈተና በትምህርት ጥራት ያለውን ችግር አንዱ የመፍቻ አማራጭ እንጂ ብቸኛ ርምጃ አይደለም›› – ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ

የዲግሪ ተመራቂዎች የመውጫ ፈተና በትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ከሚወሰዱ ስትራቴጂያዊ ርምጃዎች ውስጥ አንዱ እንጂ ብቸኛና የመጨረሻ ርምጃ አለመሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገለጹ፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ እንደሚተገበር በሚጠበቀው የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎች የመውጫ ፈተና ዙሪያ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የመውጫ ፈተና የትምህርት ጥራትን ማስጠበቂያ የመጨረሻና ብቸኛው ርምጃ አይደለም፡፡ ብቁ የሰው ሃይል በማዘጋጀት ወደ ኢኮኖሚ መግባቱን ማረጋገጫው አንደኛው መንገድ እንጂ ብቻውን የትምህርት ጥራት ሊያመጣ አይችልም፡፡

የመውጫ ፈተናው ተመራቂዎች በተማሩበት ሙያ፤ ዘመኑ የሚጠይቀውን እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት ገንብተው ስለመውጣታቸው የሚመዝን መሆኑንም ነው ዶክተር ሳሙኤል የተናገሩት፡፡

ባለዲግሪ ዋጋው አይታወቅም፡፡ ገበያው የሚለይበት አካሄድ የለውም፡፡ ዲግሪ በያዙ ተመራቂዎች መካከል በብቃት የሙያውን ምሉዕነት ተላብሶ የተመረቀው የትኛው እንደሆነ መመዘኛው የሚያረጋግጥ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

‹‹ሁሉም ዲግሪ አንድ አይነት ሆኖ አይታሰብም፡፡ ራሱ ለሚማረውም፣ የቤት ስራ እየተሰራለት የሚመረቀውም ባለዲግሪ ነው፡፡ ለሁሉም እኩል ዋጋ ሰጥቶ ወደ ገበያው መቀላቀል ተገቢ አይደለም›› ሲሉ ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡ በተለመደው አሰራር ቢቀጥል ከትምህርት ጥራት በላይ በኢኮኖሚው ኢ-ፍትሃዊነት እንዲነግስ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ምዘናው የሚሰጠው በመጀመሪያ ዲግሪ ላይ ብቻ መሆኑን፣ ትግበራው አገራዊ ፖሊሲ እንደመሆኑ በግል፣ በመንግስትም በየትኛውም ተቋም የሚማር ዲግሪውን የሚያገኘው ምዘናውን ካለፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፈተናው የሚዘጋጅበት፣ የሚያዝበትና የሚሰራጭበት ስርዓት ከሰው ንክኪ ነጻ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት ዴኤታው፤ ለምዘናው የመጀመሪያ ዲግሪ የሚመረቁትን በዓመት ከ150 እስከ 180 ሺ ማስተናገድ የሚችል አቅም መኖሩን ተናግረዋል፡፡

የሙያ ማሕበራት አቅማቸው ሲጎለብት የሙያ ፈተና ይሰጣሉ፣ የመውጫ ፈተና ስራን ከመንግስት ላይ እንደሚወስዱም ነው የጠቆሙት፡፡

ሂደቱን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ግልጸኝነቱ የተጠበቀ ለማድረግ እየተሰራበት መሆኑን ጠቁመው፤ ትምህርቶቹን የሚያዘጋጁ ተቋማትና መምህራን ዝግጅት ስራዎች እስከ ግንቦት 2015 ዓ.ም ይሰራሉ ብለዋል፡፡

መምህራንን በተለያዩ አማራጮች የትምህርት ደረጃቸውንና የመመራመር አቅማቸውን እንዲያሳድጉና የተለያዩ የማስተማር ሥነ ዘዴዎችንና ክህሎት ስልጠና እንዲወስዱ እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡

ተማሪዎቹ ብቁ ሆነው መውጣታቸውን ግብ አድርገው መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተልዕኮና በትኩረት እንዲለዩ ተደርጓል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪ ቆይታ ዘመን ወደ አራት ዓመታት እንዲያድግ ተደርጓል፡፡ ሂደቱ ተማሪዎቹ የከፍተኛ ትምህርት አውድን ተገንዝበው የሚፈልጉትን፣ መክሊታቸውንና አቅማቸውን ለይተው ማሳካት የሚችሉትን የትምህርት መርሃ ግብር መርጠው እንዲገቡ እንደሚያስችላቸውም አብራርተዋል፡፡

ተማሪዎች ሲገቡ እንጂ ለምን ወውጫ ላይ ይፈተናሉ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ቢሆንም ወደ ዩኒቨርሲቲ እያስገባን ያለነው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ተፈትነው መሆኑን መዘንጋት እንደማይገባ ገልጸው፤የመውጫ ፈተናውም ቢሆን፤ ዩኒቨርሲቲ ተምሮ ብቁ ሆኗል የሚለውን እንደማይገልጽም ነው ዶክተር ሳሙኤል የተናገሩት፡፡

የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ 1152/2011 የመውጫ ፈተና ሊሰጥ እንደሚችል በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የሪፎም አካል ነው፣ የሪፎም አጀንዳን መንግስት የሚመራው እንደመሆኑ ሂደቱን ትምህርት ሚኒስቴር መንግስትን ወክሎ መስራቱ የስልጣን ሽሚያም፣ መጣረስም እንደሌለውም አመልክተዋል፡፡
━━━━━━━━━━━━━━━━━
Join &
|||_Support us
@ethio_university_info
@ethio_university_info