Get Mystery Box with random crypto!

በኮርፖሬሽኑ ማቀዝቀዣ መጋዘንን የያዘ ሁለገብ ሕንጻ ለማስገንባት የመሰረት ድንጋይ ተጣለ የኢትዮጵ | Ethiopian Trading Businesses Corporation (ETBC)

በኮርፖሬሽኑ ማቀዝቀዣ መጋዘንን የያዘ ሁለገብ ሕንጻ ለማስገንባት የመሰረት ድንጋይ ተጣለ

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርት ጥራቱና ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ የሚያስችል ማቀዝቀዣ መጋዘንን ጨምሮ ሁለገብ ሕንጻ ለማስጀመር የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ ስነ-ስርዓት የካቲት 25/2015 ዓ.ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሺ ቶታል ነዳጅ ማደያ አጠገብ በሚገኘው የኮርፖሬሽኑ ይዞታ ውስጥ አከናወነ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የሁለገብ ህንጻው ግንባታ ከ 1.24 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እንደሚሰራና የሕንጻው ግንባታ በአራት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አያይዘውም በተለይም የማቀዝቀዣ ግንባታው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ሳይበላሹ፣ ጥራታቸውን እንደጠበቁ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚው ጋር እንዲደርሱ ለማድረግ እና አምራቹ ምርቱ ገበያ እንዲያገኝ ለማበረታታት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኮርፖሬሽኑ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሀሰን ሙሁመድ በበኩላቸው የሚገነባው ህንጻ ለሃገርና ለህዝብ የሚጠቅም መሆኑን በመጠቆም የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን እለት ታሪካዊ ቀን ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ህንጻው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በትጋት እንዲሰሩ ጠይቀው የስራ አመራር ቦርዱም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የሚገነባው ሕንጻ ሁለት መሰረት ያለው ባለ አስር ወለል ቅይጥ የአገልግሎት ህንጻ እና ዘመናዊ ባለማቀዝቀዣ መጋዘን የያዘ ሲሆን በተጨማሪም የገበያ ማዕከል፣ ላቦራቶሪዎች እና የመኪና ማቆሚያ ስፍራን ያካተተ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመተግበር የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች አቅርቦትን በጥራት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑ በስነ-ስርዓቱ ወቅት ተመላክቷል።