Get Mystery Box with random crypto!

ፅኑ ፍቅሩ ነው! የመጥፎ ልማድን ክብደት ፣ ለማቆም ወይም ለመቀየር በምንታገልበት ጊዜ እናው | ቁምነገር

ፅኑ ፍቅሩ ነው!

የመጥፎ ልማድን ክብደት ፣ ለማቆም ወይም ለመቀየር በምንታገልበት ጊዜ እናውቀዋለን ። ምንያህል እንደተቆጣጠረን ፣ ምንያህል እንደተዋሃደን ፣ ምንያህል ነብሳችንን እንደሚያስጨንቃት እንገነዘባለን ። አንወደውም ግን እንደጋግመዋለን ፤ ጠዓሙ መራራ ፣ ስሜቱም ጎምዛዛ ነው ነገር ግን እንደጣፈጠንና እንደተመቸን ለማስመሰል እንሞክራለን ። እየገደለን እንደሆነ እያወቅን እርሱን ተቀብለን በሌላ መንገድ መኖርን እንመርጣለን ። የዚህ ሁሉ ምክንያት መቀየሩን ወይም ማቆሙን ሳንፈልግና ሳንችል ቀርተን ሳይሆን ለማቆም ጠንካራ ምክንያት ስላጣን ነው ።

አዎ! እራስን መውደድ ፣ ለእራስ ማዘን ፣ እራስን መቀበል ፣ በእራስ መኩራት ምክንያት ካልሆነን ፣ ብርታት ካልሰጠን ፣ ፍላጎታችንን ካላጠነከረ መጥፎና አስከፊ የተባለውን የለውጥና የእድገት ጠር የሆነን አጉል ልማድ ማቆም እጅግ አስቸጋሪና አዳጋች መሆኑ አይቀርም ። ነገር ግን ከእኛ የሚበልጥ ፣ ሊቆጣጠረን የሚገባ ሌላ ትልቅ ሃይል ፣ ትልቅ ምክንያት አለ ። በእራሳችን እስክንጨክን ያደረገን ክፋት ፣ እራሳችንን እንድንጠላ ያደረገንን መጥፎ ስሜት የምንገታው ፣ እኔ ብቻ ልኑር የምንልበትን የከፋ እራስወዳድነትን የምናስቀርበት ፣ ደግነት የምናደርገው ፣ ሰላምን የምንመርጠው ፣ ለእራሳችን የምናዝነው ፣ ሰዎችን የምንረዳው ፣ የምናስብላቸው ፣ ቅንነት የሚዋሃደን ከፈጣሪ ፍቅር የተነሳ ነው ።

አዎ! ጀግናዬ..! ፅኑ ፍቅሩ ነው! አምላክህን ትወደዋለህ ፣ ታፈቅረዋለህ ፣ ዘወትር ትለምነዋለህ ፣ ትማፀነዋለህ ። ለአምላክህ ያለህ ፍቅር ገደብ የለውም ፤ በህይወትህ ሙሉ እንደርሱ የምታምነው ማንም የለም ። እምነትህ ፍቅርህን አጠነከረው ፣ ከወትሮው በተለየ ቁርኝትህን አጎለበተው ። እርሱ ቸር አባትህ የሚጠላውን እንድትጠላ ፣ የሚወደውን እንድትወድ ፣ የሚጠየፈውን እንድትጠየፍ ፣ የሚያቀርበውን እንድታቀርብ የሚያደርግህ አምላክህን መውደድህ ነው ።

አዎ! በእራስህም ሆነ በሰዎች ላይ የምታደርገውን ክፋት ፣ ጭካኔ ፣ በደል ፣ ስቃይ ለማንም ብለህ ሳይሆን የምትወደው አምላክህ ስለማይወደው ፣ የመረጠህ የመረጥከው አባትህ ስለማይመርጠው ፣ የዘላለም ገዢህ የዘላለም ንጉስህ እጁን ስለማያስገባበት ፣ ስለሚጠየፈው በእርግጥም አንተም ፣ ትጠየፈዋለህ ፣ ትተወዋለህ ። ፍቅሩን ማሰብህ ፣ መውደዱን በልብህ መያዝህ ከክፋት ፣ ከበደል ፣ ከሀጢያት እንድትርቅ ያደርግሃል ። ትወደዋለህና የሚወደውን አድርግ ፤ መርጠሀዋልና የመረጠውን ፈፅም ፤ በእራስህ ተስፋ ብትቆርጥ ፣ ብታዝን እንኳን ተስፋ ባደረከው ፣ በተማመንከው አምላክህ ፍቅር የተነሳ መልካም ፣ አዛኝና ልባም ሰው ሁን ።

ቸር ዋሉልኝ!!!

@enkopawiyan
@enkopawiyan
@enkopawiyan

            @betina21
https://youtube.com/channel/UCxka5u6a9gTqzyfgL8fRJZQ