2021-08-27 16:40:31
ስታደርገው የነበረውን አታውቀውምና ራስህን ይቅር በለው!!
(ሙሉጌታ መንግስት አያሌው PHD - ፉዛዥ ኮንሶልቲንግ እና ዜን አካዳሚ ዋና አማካሪ)
የሰዎች ባህሪ ይለያያል። በአስተዳደጋቸው ምክንያት፣ በተለይ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ሰባት አመታት ምክንያት የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ገዢ ፍላጎቶችና ፍርሀቶች አሏቸው። በዚህ የተነሳ ምልከታቸው በተለያዪ ነገሮች ላይ ያተኩራል። አንዱ ያላየውን ሌላው ያየዋል።
ፍላጎቶቻቸውን እና ፍርሀቶቻቸውን የሚደግፉ የተለያዩ እምነቶች ያዳብራሉ። በአይምሯቸው የሚመላለሱ ሀሳቦች በአይነት ይለያያሉ። ምልከታቸውን የሚተረጉሙት ከልምዳቸው አንፃር ነው። ስለሆነም ተመሳሳይ ነገር ተመልክተው የሚተረጉሙት በተለያየ መልኩ ነው። የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ስሜቶችን በተለያየ መንገድ ያስተናግዳሉ። ቁጣን፣ ፍርሀትን፣ ሀዘንን፣ ፍቅርን፣ የመሳሰሉትን።
ተመሳሳይ ምልከታ በተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ስሜቶችን ይወልዳል። የንግግር ዘይቤያችን ይለያያል።ከሰዎች ጋር ስንሆን ያለን ባህሪ ይለያያል።የተለያየ ትምህርትና ልምድ አለን።ባህሪ ማለት ባጭሩ አይምሯዊና አካላዊ ልምድ ነው።ልምድ ህይወትን ያቀላል። በልምድ የተነሳ የተለያዩ ችሎታዎች አለን። የተለያዩ ድክመቶችም አሉን።
ታዲያ ለምን ብለህ በራስህ ባህሪ ትበሳጫለህ? ትናዳዳለህ? ራስህን ትጠላለህ?
ይሄ ማለት ግን "ምን ላድርግ ባህርዬ ነው" እንድትል አይደለም። ወይም አሳዳጊዎችህን እንድትጠላ።የትናንትህ እስረኛ አትሁን። ትናንት ዛሬህና ነገህን በእዳ አይያዝብህ።እዳህን ከፍለህ ነፃ ሁን።
እንዴት?
ራስህን በማወቅ።ከእውቀት ሁሉ የላቀው ራስን ማወቅ ነው። በፍቅር አካላዊና አይምሯዊ እንቅስቃሴዎችህን ተከታተል። ልክ መልካም ወላጅ ህፃን ልጁን እንደሚከታተል።
የትኛው ባህሪ ከየት መጣ?
መቃወም፣ ለመቀየር መጣር አያስፈልግም። ፍሬ የለውም።ግን ንቁ ሁን። በመንፈስ። ምንም ነገር ልምድ ስለሆነ ብቻ አታድርግ። በንቃት ወስነህ አድርግ።ነገሩን ስታደርግ በሙሉ አይምሯዊና አካላዊ ትኩረት አድርግ።
ብዙ ስራ ይጠይቃል። ግን እያንዳንዱ የልምምድ ቀን ይጠቅምሀል። ሁሌም ግን ራስህን በፍቅር ርህራሄ ተመልከት።ይሄን እያደረክ ደግሞ ሌሎች ሰዎችን በዚህ መልኩ ተረዳ። እመነኝ የሰዎች ክፋት አንተ ያወቅኽውን ባለማወቃቸው ነው። የሚያደርጉትን አያውቁም።
ታዲያ እንዴት ትቀየማለህ? እንዴት ትጠላለህ? እንዴት ትቃወማለህ?
የሰውን እውነተኛ ተፈጥሮ በየቀኑ በምታደርገው ልምምድ የምታውቅ አንተ፣ የሰዎች ማንኛውም ንግግርና ድርጊት እኮ መንፈስህን አያውከውም፣ አይረብሸውም።ከሁሉም በላይ ግን ሰዎችን በፍቅር በርህራሄ በመደነቅ ተመልከታቸው። ከትናንትህ ነፃ ለመውጣት የምታደርገውን ትግል ያግዘዋል። በእውነቱ ነፃነት ትጥቅ ትግል አይፈልግም። ንቃት፣ ፍቅር፣ መደነቅ፣ ርህራሄ፣ ቸርነት ለራስህና ለሌላው ብቻ ነው የሚፈልገው። መስዋእት ይፈልጋል። ልምድን የሙጥኝ ያለ ማለት፣ የመልቀቅ መስዋእት። የሀሰት አንተነትህን መስዋእት ማድረግ።
ነፃነት መወለድ ይፈልጋል። እውነተኛውን ማንነት መውለድ በመንፈስ ነው። አካላዊ ውልደት አንድ ጊዜ ነው፤ ይህኛው ግን በየቀኑ ነው።
እውነት ነው ከላይ ያለው ነገር? የታለ ዋቢ ማስረጃው? ምንጩ የታለ የተጠቀሰው?
እውነት የሚታወቀው በመልክ አይደለም። ወይም በደጋፊ ብዛት። እውነት የሚታወቀው በፍሬ ነው። ሞክሮ ፍሬውን በመመርመር ነው፡፡
ከሀገር አማን የተወሰደ
ደመራ ሚዲያ እና ኮምኒኬሽን
439 views13:40