2022-06-29 20:16:13
ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ
“ስላዳመጥከኝ አመሰግንሃለሁ።” በቅርቡ እንዲህ ያለህ ሰው አለ? ይህ ምንኛ የሚያበረታታ አባባል ነው! ጥሩ አድማጭ የሆነ ሰው በሁሉም ዘንድ ይወደዳል ማለት ይቻላል። በችግር የተደቆሱ ወይም የተጨነቁ ሰዎችን ከልብ በማዳመጥ ልናጽናናቸው እንችላለን። ደግሞስ ጥሩ አድማጭ መሆን ከሌሎች ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን ‘እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ለመነቃቃት’ የሚያስችለን ዋነኛ መንገድ ነው።—ዕብራውያን 10:24
ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ጥሩ አድማጮች አይደሉም። ሌሎች የሚነግሯቸውን ጆሯቸውን ሰጥተው ከማዳመጥ ይልቅ ምክር መስጠት፣ የራሳቸውን ተሞክሮ መናገር ወይም አመለካከታቸውን መግለጽ ይቀናቸዋል። እውነትም ማዳመጥ ጥበብ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር . . . ራስ ወዳድ አይደለም” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5) ሌሎችን ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ የራሳችንን ፍላጎቶች ለመተው ፈቃደኛ መሆንን ይጨምራል። ይህም ሰዎች ቁም ነገር በሚያወሩን ሰዓት ቴሌቪዥኑን መዝጋት፣ ጋዜጣ እያነበብን ከሆነም ማስቀመጥ ወይም ሞባይል ስልካችንን ማጥፋት ሊጠይቅብን ይችላል። ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ ማለት ሌሎች ችግራቸውን ሲነግሩን በተመስጦ ማዳመጥ ማለት ነው። “እንዲህ ስትል በአንድ ወቅት ያጋጠመኝን ነገር አስታወስከኝ” እንደሚሉ ያሉትን ቃላት በመጠቀም ስለራሳችን ማውራት መጀመር የለብንም። እንዲህ ዓይነቱን ንግግር በሌላ ጊዜ በምናደርጋቸው ወዳጃዊ ውይይቶች ላይ መጠቀማችን ምንም ችግር የሌለው ቢሆንም አንድ ሰው ያጋጠመውን ከበድ ያለ ችግር ሲያወያየን ግን የራሳችንን ጉዳይ ልንተወው ይገባል። ለሌሎች ከልብ እንደምናስብ የምናሳይበት ሌላም መንገድ አለ።
የሌሎችን ስሜት ለመረዳት በማሰብ ማዳመጥ
“ሁላችሁ በአንድ ሐሳብ ተስማሙ፤ እርስ በርሳችሁ ተሳሰቡ፤ እንደ ወንድማማቾች ተዋደዱ፤ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 3:8) እርስ በርስ እንደምንተሳሰብ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ ለሌሎች ስሜት በመጨነቅና ስሜታቸውን እንደተረዳን በማሳየት ነው። “በጣም ያሳዝናል፣” “ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እንደተረዱህ ሳይሰማህ አይቀርም” እንደሚሉ ያሉትን ስሜታቸውን እንደተረዳንላቸው የሚያሳዩ ሐሳቦች መሰንዘር አሳቢነታችንን የምንገልጽበት መንገድ ነው። ሌላው ደግሞ ግለሰቡ የነገረንን በራሳችን አባባል በመድገም እንደተረዳነው ማሳየት ነው። ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ ሲባል ቃላቱን መስማት ብቻ ሳይሆን ስሜቱንም ጭምር ማስተዋል ማለት ነው።
ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ ከባድ ነው
በተፈጥሯችን ራሳችንን መከላከል ስለሚቀናን በእኛ የተበሳጨን ሰው ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ ማዳመጥ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ታዲያ ይህን ችግር እንዴት ልናስወግደው እንችላለን? ምሳሌ 15:1 “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል” በማለት ይናገራል። ግለሰቡ እንዲናገር በደግነት ማበረታታትና ከዚያም ቅሬታውን በሚገልጽበት ወቅት በትዕግሥት ማዳመጥ የለዘበ መልስ የምንሰጥበት አንደኛው መንገድ ነው።
አብዛኛውን ጊዜ እርስ በርስ መነታረክ ሁለቱ ግለሰቦች በፊት የተነጋገሩትን ነገር ከመድገም ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። ሁለቱም ሌላው ወገን እንዳላዳመጣቸው ይሰማቸዋል። አንደኛው ወገን ዝም ብሎ ቢያዳምጥ ኖሮ ሁኔታው እንዴት የተሻለ በሆነ ነበር! በእርግጥም ራስን የመግዛት ባሕርይ ማንፀባረቅ እንዲሁም ፍቅራዊ በሆነ መንገድና በጥበብ ሐሳብን መግለጽ አስፈላጊ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው” ይላል።—ምሳሌ 10:19
•••
ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ የማዳመጥ ችሎታ ይዘነው የምንወለደው ነገር አይደለም። ከዚህ ይልቅ በጥረትና ራስን በማሠልጠን የምንማረው ጥበብ ነው። በእርግጥም ይህ በጣም ጠቃሚ ችሎታ ነው። ሌሎች ሲናገሩ ማዳመጥ የፍቅር መግለጫ ከመሆኑም ሌላ ለደስታችንም አስተዋጽኦ ያደርጋል። እንግዲያው ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ የማዳመጥ ችሎታን ማዳበር እንዴት ብልህነት ነው!
•••
__
መልካም እውቀት የመቅሰም ጊዜ
https://t.me/dagihabeshaaa
https://t.me/dagihabeshaaa
https://t.me/dagihabeshaaa
28 views𝑑𝑎𝑔𝑖 , 17:16