Get Mystery Box with random crypto!

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚያዚያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ለሰላም ስምምነቱ ስኬት-የሁሉም ወገን ቁርጠኝነ | የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ _ Commandos and Airborne Command

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚያዚያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም

ለሰላም ስምምነቱ ስኬት-የሁሉም ወገን ቁርጠኝነት

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የቆየውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት በፌዴራል መንግስትና በሕወሃት መካከል በደቡብ አፍሪካና ናይሮቢ የሰላም ስምምነትና ማስፈፀሚያ ሰነዶች መፈረማቸው ይታወሳል፡፡

ይህ ርምጃ በዋነኝነት ጦርነት በተካሄደበት አከባቢ ያሉ ነዋሪዎችንና በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ በእጅጉ ያስደሰተ ቢሆንም የስምምነቱን ዘላቂነት በጥርጣሬ የሚመለከቱ ወገኖች ቁጥር ግን ቀላል የሚባል አይደለም፣ በዚህ ላይ በአንዳንድ ወገኖችና ሚዲያዎች የሚቀርቡ አሉታዊ ዘገባዎች የሕዝቡን ጥርጣሬ ይበልጥ አሳድገውታል፡፡

‹‹ ዕውን የሰላም ስምምነቱ በአንዳንድ ወገኖች እንደሚባለው ተስፋ ቢስ ነው ወይንስ የሚጨበጡና ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች እየታዩበት ነው?

በሠላም ስምምነቱ መሠረት እስካሁን ምን ምን ተግባራት ተከናወኑ?

የስምምነቱን ተፈፃሚነት የሚያመለክቱ ምን ተጨባጭ እውነታዎች አሉ?

በአንዳንድ ወገኖች እንደሚወራው ሕወሐት የሰላም ስምምነቱ ዕውን እንዳይሆን የማደናቀፍ ተግባር እየፈፀመ ነው ወይንስ ለስኬታማነቱ እየሰራ ነው?

በሚሉት ጥያቄዎችና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መከታ መፅሄት ከክቡር የኢፌዲሪ ጦር ሐይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ቃለ ምልልስ አካሒዷል፡፡

ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ሂደቱን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ የሚከተለውን ብለዋል ፦

"የሰላም ሒደቱን አስመልክቶ አንዱ መነሳት ያለበት ጉዳይ ወደ ሰላም የመጡት ሁለቱም ወገኖች የነበራቸው መንፈስ ምን ይመስላል? የሚለው ነው ይሕ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ይሕንን አስመልክቶ ብዙ ውዥንብር አለ:"ስምምነቱ የተፈረመው ለጊዜ መግዣ እንጂ ከልብ ተግባራዊ ሊደረግ ታስቦ አይደለም፤ የሕወሐት ሐይሎች ምሽግ በመቆፈርና ተዋጊዎቻቸውን በማሰልጠን ለአራተኛ ዙር ጦርነት እየተዘጋጁ ነው" የሚል ውዥንብር በስፋት የሚያሰራጩ ወገኖች አሉ::÷ እነዚህ የተሳሳቱ መረጃዎች ከተጨባጭ ሁኔታው ጋር  ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸውና  ሕዝብን ዕምነት ለማሳጣት ታልሞ የሚነዙ የሀሰተኛ ኘሮፓጋንዳዎች ናቸው ።

ወሬዎቹ ስምምነቱን ከማይፈልጉና፣ ከጦርነቱ ከሚያተርፉ  ሐይሎች የሚመነጩ ናቸው።
ኢትዮጵያ ሳትፈልግና ተገዳ የገባችበት ጦርነት ተቋርጦ ሰላም እንዲሰፍን በኢፌዴሪ መንግስት በኩል ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፍተኛ ፍላጎት፣ ተነሳሽነትና  ቁርጠኝነት ነበር:፣ ዘግይተውም ቢሆን የሕወሐት አመራሮችም ጦርነቱን በድርድር ማቆም አማራጭ የሌለው ርምጃ መሆኑን ተገንዝበው ወደ ሰላም መጥተዋል፡፡

በአንዳንድ ምክንያቶች መዘግየቶች ቢታዩም ሁለቱም ወገኖች ለስምምነቱ ተፈፃሚነት እየሰሩ ናቸው፤የሐገራችንን ሰላም በዘለቄታው በማረጋገጥ የወደሙትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተቋማትን መልሰን በመገንባት የሕዝቡን ሕይወት የመለወጥ ጉዳይ ሁሉም ወገኖች ሊረባረቡበት የሚገባው የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡

በመጀመሪያ በደቡብ አፍሪካ፣ ቀጥሎ በኬኒያ ናይሮቢ በተደረጉ ስምምነቶችና የማስፈፀሚያ ሰነዶች መሰረት በሁለቱም በኩል ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቷል። ፌዴራል መንግስት ሰብዓዊ እርዳታ፣ ባንክ፣ ስልክ፣ መብራት እና የመሣሠሉ አገልግሎቶች እንዲመለሱ አድርጓል። ሠራዊቱን ከውጊያ አላቋል።

ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን እና የሀገር ሽማግሌዎችን ወደ መቀሌ በመላክ መተማመን እንዲፈጠር ብዙ ርቀት ተጉዟል።

በህወሐት በኩልም  በጎ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ። ሠራዊቱን ወደ ካምኘ አስገብቷል። ከባድ መሣሪያዎችን ለመንግስት ማስረከብ ጀምሯል። ስምምነቱ በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ እንዲሆንና ተቀባይነት እንዲያገኝ ህዝቡን አወያይቶ መግባባት ላይ ደርሷል።

የሠላሙ አስፈላጊነት በእጅጉ የታመነበት በመሆኑ ለስኬታማነቱ ከልብ የሚሠሩ የህወሐት አመራሮች አሉ።  በርግጥ ከጉዳዩ ክብደት አንፃር አሁንም የሚቀሩና ጊዜ የሚፈልጉ በርካታ ስራዎች መኖራቸው እሙን ነው።

ስምምነቱ ምህረትን የሚያካትት በመሆኑ የተከሰሱ ሰዎችን ክስ ማንሳትና የመሳሰሉትም ቀጣይ ተግባራት ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡  የቀሩ ትጥቆችን የማስፈታቱ ሂደትም የሚቀጥል ይሆናል።

የህወሀትን ተዋጊ ሀይል ወደ ካምፕ ማስገባት ፣ትጥቅ ማስፈታትና  ከህዝቡ ጋር እንዲቀላቀሉ የተሀድሶ ስልጠና መስጠት DDR /disarmed dimoblized and rehablitate/ የስምምነቱ አካል ናቸው። ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተተግብሯል ማለት የሚቻለውም እነዚህ ስራዎች ከተከናወኑ በኋላ ነው።

እስካሁን ህወሀት ተዋጊ ሀይሉን  ወደ ካምፕ በማስገባቱ  የመጀመሪያው ስራ ተተግብሯል።
ትጥቅ ማስፈታትና የተሀድሶ ስልጠናዎቹ  ደግሞ የሚቀጥሉ ናቸው ።

በአጠቃላይ የሰላም  ስምምነቱ አተገባበሩ በፌዴራል መንግስቱም ሆነ በሕወሃት በኩል በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ይገኛል ማለት በሚቻልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው። ይሁንና በአንዳንድ መገናኛ ብዙሀን በተለይም በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚነዙ አፍራሽ አሉባልታዎች አሉ።

አሁን ላይ ህዝቡም ሆነ አመራሩ ጦርነትን አይፈልጉም። ጉዳቱንም በሚገባ ተረድተውታል።
ይሁንና በዜጎች መካካል አንድነት እንዳይኖር፣ ልዩነት እንዲፈጠር፣ ኢትዮጵያ እንድትዳከም የሚሠሩ የውጭ ጠላቶቻችንና የውስጥ ባንዳዎች የሰላም ስምምነቱ ስኬታማ እንዲሆን አይፈልጉም  ለሆዳቸው የተገዙ ባንዳዎችን እኩይ ድርጊትና የቀጣሪዎቻቸውን ፍላጎት በመረዳት በጋራ መመከት የህልውና ጉዳይ መሆኑ መታወቅ አለበት።

ለሠላም ሲባል የሚተገበሩ በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ። በመንግስት እና ህውሐት መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት ጦርነቱን የሚያባብሱ ተግባራት ይቅሩ ብለናል።
ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ አካሄድ መከተል ግድ ስለሚል ፉከራ፣ ሽለላና የአሸናፊነት መፈክር ማንፀባረቅ አይፈለግም። ከቆምንበት መጀመር እንደሚያስፈልግ ሁለታችንም ተግባብተናል።
የሠላም ስምምነቱን በተፈራረሙት ሐይሎች በኩል  ነገሮችን የማባባስና ሠላምን የሚያደፍረስ ፍላጎት የለም። በዚህም ሆነ በዚያ በኩል ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም ሠላም የማይፈልግ ሐይል መኖሩ ግን እየታየ ነው።

የኢትዮጵያን ጠላቶች ማድመጥ አያስፈልግም። ባንዳም ቢሆን በታሪካችን ጠፍቶ አያውቅም።
ሌላው ቀርቶ በታላቁ የጥቁር ህዝቦች ድል የአድዋ ጦርነት ወቅት እንኳ በሺህዎች የሚቆጠሩ ባንዳዎች ነበሩ።

‹‹ግጭት ተፈጥሯዊ ነው። በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ምክንያቶችና በተለያዩ አካላት ሊከሰት ይችላል። አለመግባባትን በሠላም መፍታት የሰው ህይወት መጥፋትንና የንብረት ውድመትን ለማስቀረት ሲባል ለሠላም መረታት ሐላፊነት የሚሠማቸው አመራሮች ተግባር ነው። በመሆኑም ለሠላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን እየተሠራ ሲሆን የእስካሁኑ ጉዞም ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል›› ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፡፡

በጦር ሐይሎች ጠቅላይ መምሪያ በየሦስት ወሩ የሚታተመው መከታ መፅሔት ቁጥር 1 ህትም ላይ  የተወሰደ

ወሳኝ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ቻናሉን ይቀላቀሉ

https://t.me/CommandoAndAirborneCommand

YouTube