2021-12-15 07:41:20
+++በዓለም እጅግ ውዱን ነገር አምጡልኝ!+++
በቀደመው ዘመን የሚነገር አንድ አፈ ታሪክ እንዲህ ይላል:
እግዚአብሔር ለቅዱሳን መላእክቱ "ወደ ምድር ሄዳችሁ እጅግ ውድ የሆነውን ነገር አምጡልኝ" አላቸው።
በዚህም መሠረት አንዱ መልአክ ፤ ሌላውን ሰው ለማዳን ብሎ ራሱን አሳልፎ የሰጠን ሰው "የደም ጠብታ" ይዞ ወደ እግዚአብሔር ቀረበ ፤ እግዚአብሔርም ተመልክቶ "የከበርከው መልአክ ሆይ! እውነት ነው! በእኔ ዘንድ ይህ ደም ውድ እና የከበረ ነው ፤ ነገር ግን ይኼ በዓለም ካሉት ሁሉ እጅግ ውዱ እና የከበረ ነገር አይደለም" አለው።
ሌላ መልአክ ደግሞ ፤ የታመሙትን ለማዳን ሕክምና ስትሰጥ በአሰቃቂ ሕመም ተይዛ የሞተችን ነርስ "የመጨረሻ እስትንፋስ" ይዞ ወደ እግዚአብሔር ቀረበ ፤ እግዚአብሔርም ተመልክቶ ፈገግ ብሎ "የከበርከው መልአክ ሆይ! እውነት ነው! በእኔ ዘንድ ስለ ሌሎች ራስን አሳልፎ መሥጠት በጣም ውድ እና የከበረ ነው ፤ ነገር ግን ይኼ በዓለም ካሉት ሁሉ እጅግ ውዱ እና የከበረ ነገር አይደለም" አለው።
በመጨረሻም አንድ መልአክ ፤ ንስሓ ገብቶ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ "የአንድ ኃጢአተኛን ዕንባ" በትንሽ ብልቃጥ ይዞ ወደ እግዚአብሔር ቀረበ ፤ እግዚአብሔርም ፊቱ በደስታ በርቶ እንዲህ አለ "የከበርከው መልአክ ሆይ! እውነት ነው! በዓለም እጅግ ውድ የሆነውን ነገር ይዘህልኝ መጥተኻል ፤ የመንግሥተ ሰማያትን በር የሚከፍተው የንስሓ ዕንባ!"
Source and Image Credit: John Henry Harkonen [From Philokalia]
@Slehiwetwe ይቀላቀሉን።
4.4K viewsΠαρακαλώ συγχωρήστε μας, 04:41