Get Mystery Box with random crypto!

ምርጥ አጭር የፍቅር ታሪክ ወጣቱ ሲዲ ሊገዛ ወደ አንድ ሱፐርማርኬት ዘው ብሎ እንደገባ ነበር | Campus love ❤ Stories

ምርጥ አጭር የፍቅር ታሪክ


ወጣቱ ሲዲ ሊገዛ ወደ አንድ ሱፐርማርኬት ዘው ብሎ እንደገባ ነበር ዓይኑ
አንዲት ልጅ ላይ ያረፈው ፡፡ ደስ የምትል የምታምር ልጅ! ልጅቱ ሱፐርማርኬቱ
ውስጥ ካሉት ሻጮች መሃከል አንዷ ነች፡፡ ለረጅም ጊዜ የሚያውቃት ያህል ነው
የተሰማው፡፡ አንዳች ደስ የሚል ስሜት ሲስበው፣ ሄደህ አናግራት፣ አዋራት፣
አብረሃት ሁን ሲለው ይሰማዋል፡፡ ልጅቷን ወዷታል ፡፡ ግን ደግሞ እሱ እንኳንስ
እንዲህ በአጋጣሚ አይቶ የወደዳትን የማያውቃትን ልጅ ይቅርና፣ በወጉ
የተዋወቃቸው ልጆች አጠገብም ዓይናፋር ብጤ ነው፡፡
እና የልቡን በልቡ ይዞ በእፍረት እንዳቀረቀረ የልጅቷን ፊት ሰረቅ አድርጎ
እየተመለከተ ወደ ልጅቷ ቀርቦ ሲዲ እንደሚፈልግ ተናገረ፡፡
ልጅቱ በፈገግታ ተቀበለችው፡፡
“ሲዲውን ልጠቅልልህ…” አለችው፡፡
“እሺ !” ከእሷጋ የሚያቆየውን የትኛውንም አጋጣሚ እጅጉን ይፈልገዋል፡፡ ልጅቷ
ሲዲውን አሽጋ ሰጠችው፡፡
ሂሳቡን ከፍሎ ሊወጣ ነው፡፡ ቢችል ትንሽ ጊዜ አብሯት ለመቆየት አንድ
ተጨማሪ ዕቃ ቢገዛ ተመኘ፡፡ ግን ደግሞ ሌላ ሊገዛ የሚፈልገው ዕቃም ሆነ
አንዳችም ተጨማሪ ሳንቲም ኪሱ ውስጥ የለም፡፡
እናም ሳይወድ በግድ የሲዲውን ጥቅል በእጁ የልጅቷን ፍቅር በልቡ እንደያዘ
ወደ ቤቱ አመራ፡፡ ከዛን ቀን በኋላ የልጁ የዘወትር ተግባር የዐይን ረሃብ
የሆነችበትን ይህቺን ልጅ ለማየት ወደ ሱፐር ማርኬቱ እየሄደ ሲዲ መግዛት
ሆነ፡፡
በቃ ሁልጊዜ እንደዚሁ ነው፡፡
ማለዳውን የልጅቷን ፍቅር እያሰበ፣ መውደዱን እሽሩሩ ሲል አርፍዶ፤ የዐይን
ረሃቡ ሲበረታበት የአንድ ሲዲ መግዢያ ጥቂት ብሮች ከየትም ፈላልጎ ወደ
ሱፐር ማርኬቱ ይፈጥናል፡፡
አዎን፣ እዛ ሱፐርማርኬት ውስጥ ያ ምትሃተኛ ፊት በፈገግታ ተጥለቅልቆ
ያገኘዋል፡፡ ይሄ ሲታሰበው እንዳች ፍርሃት የተቀላቀለበት ለሰስ ያለ ደስታ
በውስጡ ሲያልፍ ተሰማው፡፡ ሱፐር ማርኬቱ ሲደርስ አንድ ደቂቃ እንኳ
የማይሞላው የዘወትር፣ የተለመደው የሲዲ ግብይት ይካሄዳል፡፡
“ሲዲ ፈልጌ ነበር” ይላል፡፡
“ልጠቅልልልህ … ?” ትለዋለች፡፡
“አዎ”
ሲዲውን ይዛ ወደ አንድ ጥግ ትሄድና የሲዲውን ጥቅል አምጥታ ትሰጠዋለች፡፡
ሂሳቡን ይከፍላል፡፡
ይወጣል፡፡
በቃ ይሄው ነው የዘወትር የዐይን ረሃቡ ማስታገሻ፡፡ በዚህች ቅፅበት በስርቆሽ
ያየውን መልክ ቀኑን ሙሉ በናፍቆት ሲያመነዥገው ይውልና፣
ደግሞ ነገ ሲመጣ…
በዚህ መልኩ አንዳችም የልቡን ስሜት የሚገልፅ ቃል ሳይተነፍስ፣ ፍቅሩን
ሳይገልፅላት፣ ሰርክ ሲዲ እንዳስጠቀለለ ወራት ተቆጠሩ፡፡
ልጁ ከቀን ቀን ትካዜና ብቸኝነት አመጣ፡፡ ጉዳዩ ግራ ያጋባት እጅጉን
የሚቀራረቡት የአክስቱ ልጅ ‘ምን ሆነሃል ?’ ስትል ጠየቀችው፡፡ ብዙም
ሳያንገራግር ጉዳዩን አጫወታት፡፡ ሳይፈራ ቀርቦ እንዲያናግራትና የልቡን
እንዲነግራት አደፋፈረችው፡፡
ግን የልጁ ዓይናፋርነት በየት በኩል ! እንኳንስ ቀርቦ ማፍቀሩን ሊገልፅላት
ይቅርና እንዲሁም ራሱ እንደ አንዳች ነው የሚፈራት፡፡
በስተመጨረሻ ግን ከብዙ ውትወታ በኋላ ሲዲውን ገዝቶ ሲወጣ የስልክ
ቁጥሩን አስቀምጦላት እንዲወጣ የአክስቱ ልጅ ባቀረበችለት ሀሳብ ተስማማ፡፡
‘አዎን፣ ቢያንስ ልጅቷ አንዳች ስሜት ላንተ ካላት መደወሏ አይቀርም፡፡ ያኔ
ልታወሩ ትችላላችሁ፡፡ ከፈለግክ የልብህን ትነግራታለህ፡፡ አለበለዚያ
መቀራረባችሁም ቢሆን አንድ ነገር ነው፡፡ ቀስ በቀስ የሚሆነው ይታያል፡፡
ካልደወለችልህም ይቀራል’ አለችው፡፡
ተስማማ፡፡
በቀጣዩ ቀን እንደተለመደው ሲዲ እንደሚፈልግ ተናገረ፡፡
“ልጠቅልልህ…” አለችው፡፡
አዎን !
ሲዲውን ልትጠቀልልለት ዞር እንዳለች ቀስ ብሎ የስልክ ቁጥሩ ያለበትን
ብጣሽ ወረቀት አስቀመጠላት፡፡
የተጠቀለለውን ሲዲ ይዛ ስትመጣ ሂሳቡን ከፍሎ በፍጥነት ሱፐርማርኬቱን
ጥሎ ወጣ፡፡
ከሱፐርማርኬቱ እንደወጣ ባከናወነው ድርጊት ረክቶ እፎይ አለ፡፡ ካልደወለችለት
ግን ከእንግዲህ ዓይኗን የሚያይበት ድፍረት እንደማይኖረው ተገነዘበ፡፡ ሀዘን
ተጫጫነው፡፡ ትካዜው በረታ፡፡ ባትደውልልኝስ ሲል ፈራ፡፡ አዎን፣ በዕርግጥም
እኔ ተራ ደምበኛ ነኝ እንጂ ምኗ ነኝ ሲል አሰበ፡፡ እና ምን ልሁን ብላ ነው
የምትደውልልኝ ! ፈፅሞ አታደርገውም፡፡ አትደውልልኝም ሲል ደመደመ፡፡
አለመደወልም ብቻም አይደል - ጉዳዩ ከዚህም የሚከፋበት ሁኔታ አለ፡፡ ጉዳዩን
የሱፐርማርኬቱ ሰራተኞች ሲያውቁበት፣ ‘ውይ ለካንስ ለዚህ ነውና በየቀኑ ሲዲ
የሚገዛው’ እያሉ ሲሳለቁበት ታየው፡፡
አፈረ፡፡
በቀን አንዴ ሳይሳለማት የማይውለውን የልቡን ንግሥት መቼም ቢሆን ላያያት
ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ ሲታሰበው እዛው በዛው ናፍቆቱ በርትቶ ሀዘን
ተቀራመተው፡፡ በሀሳብ እንደተዋጠ ደመነፍሱን ወደ አውራ ጎዳናው ወጣ፡፡
በቀጣዩ ቀን ረፋድ ላይ የልጁ ቤት ስልክ ጮኸ፡፡ ደዋይዋ ተፈቃሪዋ ልጅ ነች፡፡
ትላንት ልጁ በሰጣት ስልክ መደወሏ ነው፡፡
የባለታሪኩ የአክስት ልጅ ስልኩን አነሳች፡፡ በስልኩ በዛኛው ጫፍ ያለው
ልስልስ ያለ የሴት ድምፅ ልጁን እንደሚፈልግ ተናገረ፡፡
ምላሹ ግን ልብ ሰባሪ አሳዛኝ ዜና ሆነ፡፡
ልጁ በትላንትናው ዕለት በደረሰበት የመኪና አደጋ ለዘለዓለሙ አሸልቧል፡፡
ሞቷል…፡፡ ትላንት ሀዘን እንደተጫነው፣ በሀሳብ ተውጦ መንገድ ሲያቋርጥ ነበር
የመኪና አደጋው የደረሰበት፡፡
ልጅቷ ጆሮዋን ማመን አልቻለችም፡፡ አንዳች ክፉ ቀልድ ነው የመሰላት፡፡
ከልጅቷጋ የነበረውን ግንኙነት ጠንቅቃ የምታውቀው የልጁ የአክስት ልጅ
ልጅቷን ወደ ቤታቸው ጠራቻት፡፡
አንድም ሀዘንን መካፈል ነው፡፡ አንድም…
ልጅቷ እንደመጣች ሀዘን እንደደቆሳቸው ጥቂት ተጨዋወቱ፡፡ አልበሙን ከፍታ
አሳየቻት፡፡ ሁለት ልቦቻቸው የተሰበሩ እንስቶች! በስተመጨረሻ የልጁን ትዝታ
ለማደስ፣ ለዘለዓለም ያሸለበውን ልጅ ለማስታወስ ወደ ልጁ መኝታ ቤት ይዛት
ሄደች፡፡ ‘ይሄ መኝታ ክፍሉ ነበር፡፡ ሁልጊዜ እዚህ መስኮቱጋ ነበር ተቀምጦ
የሚያነበው እዚህጋ ደግሞ…’ እያለች አስጎበኘቻትና፣ በስተመጨረሻ፣
ቁምሳጥኑን ስትከፍት … ስፍር ቁጥር የሌለው የታሸጉ ሲዲዎች ክምር
ፊታቸው ተገጠገጠ፡፡ ልጅቷ በድንጋጤ ክው አለች፡፡ እነዛ በየቀኑ እየመጣ
የሚገዛቸው ሲዲዎች መሆናቸው ነው፡፡ ሁሉም እንደታሸጉ ናቸው፡፡ ከመሃከላቸው
አንዱም ከታሸገበት አልተፈታም፡፡
ልጅቷ በቀስታ አንዱን የታሸገ ሲዲ አንስታ እሽጉን ስትፈታ ከውስጡ አንድ
ብጣሽ ወረቀት ወደቀ፡፡ ወረቀቱ ላይ እንዲህ የሚል ተጽፏል፡፡ ‘…አንተ ልጅ…
በጣም ደስ ትለኛለህ ….ላገኝህ እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ ስልክ ቁጥር ልትደውልልኝ
ትችላለህ…..?’ ይልና ከሥሩ ስልክ ቁጥር ሰፍሯል፡፡ ሲዲውን ስትጠቀልልለት
ይሄን ማስታወሻ ፅፋ ውስጡ ያስገባችለት ልጅቷ ራሷው ነች፡፡
የሲዲውን እሽግ ከፍቶ ማስታወሻውን እንዳላየው ስታውቅ እንባዋ ፊቷን
አጠበው፡፡ አሁንም ሌላ የሲዲ እሽግ አንስታ ከፈተች፡፡ አሁንም ሌላ
ማስታወሻ…
‘…እባክህን አንተ ልጅ…ላገኝህ እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ ስልክ ቁጥር ደውልልኝ’
እንባዋ ፊቷን እያጠበው የሲዲዎቹን ጥቅል አንድ በአንድ ፈታቻቸው፡፡
ሁሉም የልጅቷን መልዕክት ይዘዋል፡፡
እባክህን አንተ ልጅ…በጣም ደስ ትለኛለህ …ላናግርህ እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ ስልክ
ቁጥር ደውልልኝ
እንባዋ አይኗን ጋረደው፡፡
አነባች፡፡