Get Mystery Box with random crypto!

. የዕርቅ ምንጭ ቅብዐ ሜሮን ✥ °°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°° ✥ አባ ጊዮርጊስ በ | ብራና ሚዲያ BRANA MEDIA

. የዕርቅ ምንጭ ቅብዐ ሜሮን
✥ °°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°° ✥

አባ ጊዮርጊስ በሰአታት ምስጋናው ለኢትዮጵያ ገበዟ የሆነውን ጠላት የሚያሳፍርላትን ሊቀ ሰማዕታት በሚያነሳበት "የቅዱስ ጊዮርጊሱ ስብሐተ ፍቁር" ክፍል እንዲህ ይላል

. ጊዮርጊስ ዓምድ
በቅብዐ በለሳን ጽሑድ
ንስእለከ በወልድ
ከመ ትናዝዘነ ነዓ እምኃዝን ክቡድ

«ፍጹም ንጹሕ የሆንክ በሜሮኑ ቅብዓት
ሰማዕቱ ጊዮርጊስ አምድና መሠረት
ስለ ወልድ ብለህ ስለአምላከ አማልክት
ደርሰህ አረጋጋን ከሐዘናችን ብዛት»
【መጽሐፈ ሰአታት ስብሐተ ፍቁር ዘቅዱስ ጊዮርጊስ】

ጭንቁንና መከራውን ያቀለለልን ኢትዮጵያን ሁሌም የማይረሳት አምላከ ቅዱሳን ፍጡነ ረድኤት ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስንና ማኅተመ እምነት ኃይለ ሃይማኖት ቅዱስ ሜሮንን የሰጠን አምላካችን የተመሰገነ ይሁን።

ሐዋርያዊቷ ቤተክርስቲያናችን ፣ ሲኖዶሳዊቷ አቅሌስያ ለ፫ኛ ጊዜ ቅብዐ ሜሮንን ለማፍላት በነበረው እጅግ አስደናቂ አገልግሎት ዛሬ ፯ኛ ቀን ጸሎቷ ሲከናወን አይተናል።
(

)

(በጸሎቷም አጋማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ መታሰቢያ ዕለት የዕርቅ ዜና መስማታችንን ድንገቴ ነው እንደማንል አምናለሁ)

ቅብዐ ሜሮን የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ የጸጋው ማሻገሪያ ነው። መንፈስ ቅዱስ ጰራቅሊጦስ ማለት ደግሞ መንጽሒ (የሚያነጻ)፣ መጽንዒ (የሚያጸና)፣ መስተፈሥሒ (ደስታን የሚሰጥ)፣ መስተሥርይ (ኃጢአትን ይቅር የሚል)፣ ናዛዚ (የሚያረጋጋ)፣ ከሣቲ (ምሥጢርን የሚገልጥ) የእግዚአብሔር መንፈስ ነው።
【መጻሕፍተ ሠለስቱ ሐዲሳት፣ ገጽ ፪፻፹፫)】

በቅዱስ መንፈስ ይኽ ሁሉ ይሠጣል ፦ ደስታን ፣ መረጋጋትን ፣ ጽናትን ፣ ሥርየተ ኃጢዓትን ፣ መንጻትን ፣ ማስተዋልን… እኛስ ከዚህ ውጪ ምን አጣን!?

ኀዘነተኞች አልነበርንም? የተቅበዘበዝን አልነበርንም? የተናወጽን አልነበርንም? በኃጢዓት የተዳደፍን አልነበርንም? የቆሸሽን አልነበርንም? ዞሮ ማየትና አስተውሎ መረዳት የራቀን አልነበርንም? በቸርነቱ ይታረቀን።

ምክንያቱ ደግሞ ይኽ ነው!

" ወእለሰ መንፈስ ቅዱስ አልቦሙ ይከውኑ ማኅደረ ለአጋንንት ርኩሳን፤ እስመ ጰራቅሊጦስ ይጸልእ ሐሰተ ወኵሎ ምግባረ እኩየ፤ ወዲያብሎስ ይጸልእ ምግባረ ጽድቅ ወምግባረ ሠናይ ⇨ መንፈስ ቅዱስ የሌለባቸው ሰዎች ለርኩሳን አጋንንት ማደሪያ ይሆናሉ ፣ መንፈስ ቅዱስ ሐሰትንና ክፉ ሥራን ሁሉ ይጠላልና ፣ ዲያብሎስም የጽድቅ ሥራንና መልካም ሥራን ይጠላል"
【መጽሐፈ ዲድስቅልያ ፴፫ ፥፪፻፱】

በሀገራች የሜሮን ሥርጭት ካለቀ (በተለይ በገጠሩ) 10 ዐመታት በላይ እንዳለፈ ሊቃውንት ይናገራሉ፤ ቅባት አሽገው የሚቸረችሩ ፣ በምግብ ዘይት «አጋንንት የሚያባርሩ» መበርከታቸው … በቅዱስ ቅብዕ ስለሚሠጠው አገልግሎት በመረጃ ማጣት ምእመናን ሲደናገሩ ታይቷል ፤ እንዲሁ ረሃብ ጦርነቱ ደዌ መቅሰፍቱ ከበረታብን መሰነባበታችንንም ልብ ይሏል።

የሥርዓት መጽሐፋችን እንዲህ እያለ ያመሰግናል

"እንደዚህ እናመሰግንሃለን ፦ የሁሉ ፈጣሪ ሆይ በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ስለገለጥክልን ሞት ስለሌለበት ስለዚህ ሜሮን መዓዛ ስለዚህ ዘይት እናመሰግንሃለን ፤ ክብር መንግሥት ኃይል ለእንተ ነውና ለዘለዓለሙ አሜን።"
【መጽሐፈ ዲድስቅልያ ፴፮፥፩】

የሜሮንን ክብር አናውቀው ብለን እንጂ ልጅ በኤጲስ ቆጶስ አልያም በቄስ የተጠመቀን ልጅ በቅብዐ ሜሮን ከብሮ ሲከብር ምዕመን ደፍሮ ሊታቀፈው እንደማይገባ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ያዛል
" ከዚህም በኋላ ዲያቆኑ ወንዶችን ይቀበላቸው ፣ ዲያቆናዊትም ሴቶችን ትቀበላቸው ፣ የተቀበሉት ማኅተም ሜሮን ማንም ማን ሊዳስሰው የማይችል ንጹሕ ቅዱስ ይሆን"
【መጽሐፈ ዲድስቅልያ ፲፮፥፴፭】

የአንዳንዶቻችን ጥያቄ ፦
"ሜሮን እንዴት በአደባባይ ይዘጋጃል? ¡"

ዛሬ ግን ስለ ሜሮን አፈላል ሳይቀር ከጳጳሳቱና ይኽን አጥንቶ መጽሐፈ ጸሎቱን አዘጋጅቶ ሥርዓቱን መርቶ ከቀረበው ሊቃውንት ጉባኤ በላይ እኔ አውቃለሁ የሚል ሥርዓት ነቃፊ አበውን በአደባባይ ዘላፊ «ተራ ሰው» ማየት በእጅጉ ያሳዝናል!

አንዳንድ መምህራን ግን በቅንነት "ኢትደዩ ባሕርየክሙ ቅድመ አሕርው" ያለውን ይዘው በቅንነት «እንደው በኅቡዕ ቢሆን» ሲሉ ተመልክቻለሁ፤ እንደግል ሐሳብ እኔ ግን ይህን ለማለትም የፌስቡክ አደባባይ ቦታው አይደለም የእናንተም በኅቡዕ ቢሆን እላለሁ።

አንድ አድራጊው መንፈስ ቅዱስ ስለሚያሠጠው ሜሮን አንድ የማያደርገንን የግል ሐሳብ ከማንሳት እንጹም
"ሀበነ ንኅበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስየ⇨ የአንተ በሚሆን መንፈስ ቅዱስ አንድ እንሆን ዘንድ አንድነቱን ሥጠን" እንዲል 【ቅዳሴ ሐዋርያት ቁጥር ፶፬】

ምሥጢረ ሜሮንን ምሥጢር የሚያስብለው በምሥጢር በመዘጋጀቱና በምሥጢር በመፈጸሙ ሳይሆን በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋን በማሰጠቱ ፣ ስንቀባው የሚታይ ቢሆን ያደረው ረቂቁ መንፈስ ቅዱስ የማይታይ በመሆኑ ነው" ቀንዲል (የመብራት ዘይት) ፣ ጥምቀት (ማየ ጸሎት) … ሲዘጋጅ ሲፈጸምም ሥርዓቱ በአደባባይ ነው። (ይህ ግን ለሁሉ አለመሆኑን ልብ ማለት ያሻል፤ እንደ ቁርባን ያለው በአደባባይ አይዘጋጅም አይፈጸምምና! )

ሁሉን አንድ ለማድረግ፣ የተጣሉትን ለማስማማት ለዕርቅ በተሠራው ሥርዓት እኛ ራሱ የሚለያይ ሐሳብ ማቅረባችን አባቶችን ለመንቀፍ ብርዕ ማንሳታችን ጤናማነታችንን የሚያስጠረጥር ነው… እንደው ምን አይነት ጉደኞች ነን!

ስለ ሁሉ የምናውቅ ሁሉን እኛ ካላጸደቅን እንግዳ ነገር ሲመጣ ከማድነቅ ከመጠየቅ ይልቅ ተችቶ መናቅ በዐደባባይ መሳለቅ የጤና ምልክት አይመስለኝም…

ይማረን ጥቂት ነጥብ ካለፈው ጽሑፍ ላጋራና ነገሬን ልቋጭ https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=5579714008743732&id=100001155652281

"ለእኛ ሜሮን ምናችን ነው?"

★ ማኅተመ እምነት ውእቱ
⇨ #የእምነታችን_ማኅተም_ነው! 【መጽሐፈ ምሥጢር】
°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°

"ክርስቶስ ፈጣሪዬና ተስፋዬ ነው የአባቱም ስም የድኅነቴ ዘወድ ነው፤ የመንፈስ ቅዲስም ስም የክብሬ መገኛ ነው፤ የመስቀሉም ክብር የመመኪያዬ ዘውድ ነው። እመቤቴ ድነግል ማርያምም የገነቴ በር ከፋች ናት፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የጥምቀቴ መገኛ ናት፤ ሐዋርያትም አጥማቂዎቼ ናቸው፤ ቅብዓ ሜሮንም የእምነቴ ማኅተም ነው፤ ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን፡፡"

★ ኃይለ ሃይማኖት ውእቱ
⇨ #የሃይማኖት_ኃይል_ነው 【መጽሐፈ ድድስቅልያ】
°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°

” ከተጠመቁም በኋላ ኤጲስ ቆጶሱ ቅብዐ ሜሮኑን ይቀባቸው ፤ በክርስቶስ በሞቱ አምሳል ተጠምቀዋልና ። ይኸውም ከበለሳን የተገኘ ቅብዓ ሜሮን የሃይማኖት ኃይል ነው ።”

★ ወቦቱ ይትገበር መድኃኒት ወፈውስ ወምክሆሙ ለኵሎሙ መሲሐውያወን
⇨ ድኅነትና ፈውስ የሚደረግበት የክርስቲያኖች ሁሉ #መመኪያችን_ነው 【መጽሐፈ ስንክሳር】
°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°°