Get Mystery Box with random crypto!

የተከበራችሁ የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ባለሀብቶች፣ እን | ቦሌ ኮሚዩኒኬሽን/Bole Communication

የተከበራችሁ የቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች፣
አርሶ አደሮች፣
ወጣቶች፣
ሴቶች፣
ባለሀብቶች፣
እንኳን ለከተራና ጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
የጥምቀት በዓል አገራችን ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው ታላላቅ ባሕላዊ ቅርሶች መካከል አንደኛው ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የባሕልና የሳይንስ ድርጅት (ዩኔስኮ)ም ይህንን ታላቅ በዓል በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ መዝግቦታል፡፡
ይህ ታላቅ በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያዊያን የጋራ በዓል ነው፡፡ በዚህ በዓል ከኢትዮጵያዊያን ባሻገር ከመላው ዓለም የሚመጡ ቱሪስቶችና ሚዲያዎች ወደአገራችን በብዛት የሚጎርፉበትና የሚታደሙበት በመሆኑ ለአገራችን የገጽታ ግንባታ እና ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በእጅጉ ከፍተኛ ነው፡፡
ዘንድሮም የከተራና የጥምቀት በዓልን በታላቅ ድምቀት ለማክበር በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ በክፍለ ከተማችንም በዓሉ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በሰላም እንዲከበር የክፍለ ከተማው አስተዳደር ከባለድርሻ አካላትና ከመላው ሕዝባችን ጋር በጥምረት እየሠራ ይገኛል፡፡

የጥምቀት በዓል ሕዝባዊ የአደባባይ በዓል ነው፣ በመሆኑም በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ሁላችንም የጋራ ኃላፊነት አለብን፡፡ በዘንድሮው በዓል የአገራችንን ሰላም የማይሹ ኃይሎች እኩይ ዓላማቸውን በበዓሉ ወቅት ለማስፈጸም ሙከራዎችን ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ መንግሥት እነዚህን የሰላም ማደፍረስ ሙከራዎች በብቃት የማክሸፍ ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፣ በክፍለ ከተማችንም መሰል ተግባራትን ለመፈጸም የሚደረጉ ሙከራዎች በሰላም ወዳዱ ሕዝባችንና በጸጥታ አካላት የተቀናጀ ርብርብ እየከሸፉ ይገኛሉ፡፡
ሰላማችንን ማስጠበቅ የጋራ ኃላፊነታችንን ነው፡፡ ልማትና ብልጽግናችን ዕውን የሚሆነው ሰላም ሲሰፍን በመሆኑ የጥምቀትን በዓል ስናከብር ሰላማችንን ለመጠበቅ ዘብ ልንቆም ይገባል፡፡ በመሆኑም መላው የክፍለ ከተማችን ነዋሪዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሰላም ሠራዊት፣ እንዲሁም የክፍለ ከተማችንና የወረዳዎቻችን አመራሮች በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ በባለቤትነት መንፈስ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም ድርሻችንን እንድንወጣ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

ዓለምጸሐይ ሺፈራው
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ