Get Mystery Box with random crypto!

“ሀብታችንን፣ ዕውቀታችንን ያለምንም ስስት የአንድነታችን መገለጫ ለሆነው ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ | ቦሌ ኮሚዩኒኬሽን/Bole Communication

“ሀብታችንን፣
ዕውቀታችንን
ያለምንም ስስት
የአንድነታችን መገለጫ ለሆነው ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እናውላለን”

“ቦሌ 5150” በሚል ስያሜ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የጎዳና ላይ የዱላ ቅብብል ሩጫ ማዘጋጀቱን የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

መርሐ ግብሩን አስመልክቶ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምጸሐይ ሺፈራው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያዊያን የአንድነትና የልማት መገለጫ የሆነ አገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን አውስተው፣ ይህንን ታላቅ ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ የቦሌ ክፍለ ከተማ ባለፉት ጊዜያት በሀብት ማሰባሰብ ዘርፍ ሰፊ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡ በ2014 በክፍለ ከተማው ለግድቡ ግንባታ ሀብት ለማሰባሰብ የተያዘው ዕቅድ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ያመለከቱት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በ2015 በጀት ዓመትም የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ አዳዲስ መንገዶችን በመቀየስ አስተዳደሩ እየሠራ መሆኑንና የ “ቦሌ 5150” የጎዳና ላይ የዱላ ቅብብል ሩጫም የዚህ ተግባር አንድ አካል መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ታደሰ በበኩላቸው “ሀብታችንን፣ ዕውቀታችንን ያለምንም ስስት የአንድነታችን መገለጫ ለሆነው ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እናውላለን” በሚል መሪ ቃል ጥር 28 ቀን 2015 በዓይነቱ ልዩ የሆነ የጎዳና ላይ የዱላ ቅብብል ሩጫ እንደሚካሄድ ገልጸው፣ የውድድሩ መጠሪያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምር የሚያመነጨውን 5,150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን መሠረት በማድረግ 5,150 ሜትር የሚሸፍንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ ውድድር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዱላ ቅብብሉ ጎን ለጎን ድርጅቶች፣ ባለሀብቶች እንዲሁም መላው የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ቦንድ በመግዛት እንዲሳተፉ እንደሚደረግ የገለጹት ኃላፊው፣ በዚህ በይዘቱ የመጀመሪያ በሆነው የዱላ ቅብብል ሩጫና ተያያዥ መርሐ ግብሮች በበጀት ዓመቱ ከክፍለ ከተማው ለመሰብሰብ የታቀደውን ሀብት ለማሳካት መላው የክፍለ ከተማው ነዋሪዎችና የተለያዩ አጋር አካላት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ጥር 1/2015