Get Mystery Box with random crypto!

በመስማቱ 'ምንድነው? የሚሰማው' ብሎ ባለሟሎቹን ሲጠይቃቸው 'ቅዱስ ላሊበላ እየተገረፈ ነው' አሉት | ቤተ ውዳሴ

በመስማቱ "ምንድነው? የሚሰማው" ብሎ ባለሟሎቹን ሲጠይቃቸው "ቅዱስ ላሊበላ እየተገረፈ ነው" አሉት ንጉሡም ወዲያውኑ እንዲያመጡለት አዘዘ። ሲመለከተውም በሰውነቱ ላይ ምንም የግርፈት ምልክት አላየበትም ንጉሡም ጻጽቅና እውነተኛ መሆኑን ፈጣሪም ከግርፋትና ከጥፍት ከልሎታልና "እንኳንስ ሊሞት ግርፋቱ አልተሰማውም" በማለት እጅግ አደነቀ። ከባድ ሀዘንም ተሰማው። "አምላኬን በድያለሁ የማይገባ ሥራ ሰርቻለሁ" ብሎ ቅዱስ ላሊበላ በሕዝቡ መካከል "ከዛሬ ጀምሮ መንግሥት ለአንተ ይገባል በግፍ አስገርፌሀለሁ በድዬሀለሁም ይቅር በለኝ" በማለት ከጫማው ወድቆ ይቅርታ ከጠየቀው በኋላ መንግሥቱን አስረክቦ መንኖ ለመሔድ ወሰነ።

የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ቅዱስ ላሊበላም "ለይቅርታው ይቅር ብብያሁ ነገር ግነ መንግሥት የእግዚአብሔር ገንዘብ ናትና መንግሥትህን የምቀበለው ከእግዚአብሔር እንጂ ከአንተ አይደለም አንተም በዙፋንህ መቆየት አለብህ እኔ ግን መልካም ፈቃድ ከአምላኬ እስካገኝ ድረስ እጠይቃለሁ" ብሎ የዐፄ ገብረ ማርያም ጫማ ስሞ በፍቅር ተሰናብቶ ወጣ። በዚህ ጊዜ ሕዝቡና "መንግሥትን ያህል ነገር እንደ ቀላል ነገር ቆጥሮ አልነግሥም ብሎ በመሄዱ እንዴት የእግዚአብሔር መንፈስ ቢያድርበት ነው?" በማለት በችሎት ተቀምጦ ሁኔታውን በግብር ሲከታተል የነበረው ሁሉ እያለቀሱ ቅዱስ ላሊበላን ተከትሎ ወጣ። ቅዱስ ላሊበላ ግን በአላማው ፀንቶ በሰዎቹ ፍቅር ሳይታለል እግዚአብሔር የሰጠውን ረዳቱን ቅድስት መስቀል ክብራን ይዞ ወደ አክሱም ሄደ።

በአክሱም አካባቢ በአባ ጰንጠሌዎን ገዳም በጾምና በጸሎት ተወስነው ፈጣሪያቸውን እየተማፀኑ ሳለ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ "ሰማያዊ ኢየሩሳሌምን እንዳየህ ምድራዊት ኢየሩሳሌምንም አይቶ ህንፃ ቤተ መቅደሱን በሰማያዊትና በምድራዊት ኢየሩሳሌም አምሳል ያንፅ ዘንድ ኢየሩሳሌም ሔዶ የተወለደበት ቤተልሔም፣ የተጠመቀበትን ዮርዳኖስ፣ የተሰቀለበትን ቀራንዮ፣ የተቀበረበትን ጎልጎታን፣ ደብረ ታቦርን ምስጢረ መለኮቱን የገለጸበትን አጠቃላይ ብዙ ተአምራት ያደረገበትን ሁሉ እንዲያይና እንዲሳለም መልአኩም እንደሚመራው መስቀል ክብራ ግን በዚሁ ከደናግሎች ጋር እንደምትቀመጥና ቅዱስ ሚካኤል እንደሚያጽናናት እንደሚጠብቃት መታዘዙን ነገረው።

በዚህም መሠረት ቅዱስ ላሊበላ ወደ ኢየሩሳሌም በፈቃደ አምላክ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ጠባቂነት በሱዳንና በግብጽ አድርጎ ኢየሩሳሌም ገባ። በዚያም ከላይ የተጠቀሱትን ቅዱሳን መካናትንና ሌሎችንም ቅዱሳት ስፍራዎች ለዐሥራ ሦስት ዓመታት በመዘዋወር ተመለከተ። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ላሊበላ የጉብኝቱንና የተፈቀደለትን ጊዜ ሲፈጸም አሁንም መልአኩ ተገልጾ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሄደ መንግሥትን ከዐፄ ገብረ ማርያም ተረክቦ የታዘዘውን እንዲሰራና በመንገድ በግብጽ ምድር የተበተኑትን ወገኖችን ወደ ኢትዮጵያ ይዞ እንዲሄድ የታዘዘ መሆኑን ገለጸለት። ቅዱስ ላሊበላም በፈቃደ አምላክ በግብጽ ያሉትን ክርስቲያኖች ሰብስቦ በጊዜው የነበረው የግብጽ መንግሥት የእስላም ሃይማኖት ተከታይ በመሆኑ እንዴት አድርጎ እንደሚያስተዳድራቸው ጠየቃቸው። ክርስቲያኖቹም እግዚአብሔርን ማምለክ እንደተከለከሉና በሀዘን በሰቀቀን የሚኖሩ መሆናቸውን ገለጹለት። በዚህ ዘመንም በመካከለኛው ምሥራቅ 3ኛው የመስቀል ጦርነት በመኖኑ ግብጻውያን ፊታቸውን ወደዚያ አዙረው ስለነበር ቅዱስ ላሊበላ በፈቃደ አምላክ በርካታ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ መጣ።

ዐፄ ገብረ ማርያም ወንድሙ ቅዱስ ላሊበላ ሕዝበ ክርስቲያንን ይዞ የኢትዮጵያ ምድር እንደረገጠ በሰማ ጊዜ በክብር የሚቀበሉት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰራዊት አሰልፎ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንዲመጣ ላከበት። ቅዱስ ላሊበላም ከባለቤቱ ጋር እና ከሕዝቡ ጋር በአክሱም ስለነበር የእግዚአብሔር ፍቃድ እንደሆነና ጊዜም እንደደረሰ በማወቁ ልዋል ልደር ሳይል ወደ ቤተ መንግሥቱ መጥተ ከዐፄ ገበረ ማርያም ጋር ተገናኘ። ንጉሡ ዐፄ ገብረ ማርያም ቅዱስ ላሊበላ ወደ እርሱ መምጣቱን በሰማ ጊዜ በፍቅር እንባ ተቀበለውና ሕዝቡን ሰብስቦ አዋጅ ነግሮ "እንሆ የአምላክ ፈቃድ ደርሷል መንግሥት ለዚህ ቅዱስ ሰው ይገባል ብሎ ዙፋኑን ለቅዱስ ላሊበላ አስረክቦ ተሰናብቶ ዛሬ ቅዱስ ሐርቤ እየተባለ ወደሚጠራው ገዳም ዘግቶ በጾም፣ በጸሎት፣ በቀኖናና በንስሐ ሰውነቱን ለፈጣሪው አስገዝቶ በክብር የካቲት 16 ቀን ዐርፎአል።

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ላሊበላ ንጉሥ ነኝ ብሎ ሳመካ ስልጣኑን ለሕዝቡ በመስጠት ሕዝቡን ይመራ ነበር። ሕዝቡም የቅዱስ ላሊበላን የሃይማኖት ጽናትና ደግነት እያየ "ይህን ጻድቅ ንጉሥ ዕድሜውን አርዝምልን" እያሉ ይጸልዩለት ነበር። የቅዱስ ላሊበላን ደግነት በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆኑ በውጭም ያሉ ነገሥታትና ሕዝብ ጭምር ያውቁ ነበር በዚህም መሰረት እስላሙም ክርስቲያኑም ቅዱስ ላሊበላን አንስተው አይጠግቡም ነበር። በቅዱስ ላሊበላም ዘመነ መንግሥት ጊዜ ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ያላት ግንኙነት የሰላም፣ የፍቅር፣ የክብርና የደስታ ግንኙነት ነበራት ለዚህም ነበር 1189 ዓ.ም አካባቢ ሳላህ አዲን የተባለው የእስላም ንጉሥ በሦስተኛው የመስቀል ጦርነት ኢየሩሳሌምን በያዘ ጊዜ ከክርስቲያን ቅርሶች ዋና ዋናዎቹን በጎልጎታ በሚገኘው በጌታችን መቃብር አጠገብ ያለውን ዕሌኒ ንግሥት ቅዱስ መስቀሉን ያስወጣችበት ዋሻና በቤተልሔም ጌታ የተወለደበትን ጎል (በረት) ለቅዱስ ላሊበላ በስጦታ ያበረከተው።

የቅዱስ ላሊበላ ቤተ መቅደሶች አሰራርና ፍጻሜ፦ ቅዱስ ላሊበላ በዘመኑ ይህን ድንቅ ሥራ የሰራው ጮማ በመቆራረጥ ጠጅ በማማረጥ ልብስ መንግሥትን ለብሶ በመሽሞንሞን አልነበረም። ለአንዲት ደቂቃ መንፈስ እግዚአብሔር ያልተለየው ቅዱስ አባት ነበር። ፈጣሪው የሚመሰገንበትን የእርሱም ስም ለዘላለም የሚጠራበትን ቤተ መቅደስ ለማነፅም ሱባኤ ገብቶ ቦታው የት እንደሆነ ተረዳ። ነገር ግን የተገለጸለት ቦታ ቀይት የምትባል ባላባት ትኖርበት ነበር። ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሌላ ቦታ ሰጥቶ መጠቀም ይችል ነበር። ግን የትሕትና አባት ነውና መብቷን ሳይነካ እራሱን ዝቅ አድርጐ "ቦታውን ለሥራ ፈልጌዋለሁና በገንዘብ ሽጭልኝ" አላት። እርሷም እጅግ ከፍ ያለ ገንዘብ ጠየቀችው። ይኸውም አርባ ጊደር ላም መግዛት የሚችል ገንዘብ ነበር የጠየቀችው እርሱም ምንም ምን ሳይል ወርቁን ከፈላት። ቀይትም ገንዘቧን ተቀብላ ሔደችና እንደገና ተመልሳ "የምኖርበት ቦታ ስጠኝ" አለችው። እርሱም "ወደፊት ሌላ ቦታ እስክሰጥሽ በዚህ ቆይ" ብሎ ዛሬ ቆይታ የምትባለውን ቦታ ሰጣት ከዚህም የተነሳ ከግዜ ብዛት የቦታው መጠራያ ስም ቆይታ ተባለች። ይህች ቦታ የምትገኘው ከላሊበላ ከተማ በስተ ምሥራቅ በግምት ሁለት ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው። ለዚህ ነበር አባቶቻችን ንጉሥ ላሊበላ በአንጡራ ገንዘቡ የገዛውን ቦታ ስለሆነ በቦታው የሃይማኖት ሸቃጮች የሃይማኖት ሸቀጥ አያካሂዱበትም በማለት ለመስዋዕትነት የተዘጋጁት አሁንም ቢሆን ወደፊትም በዚህ ዙሪያ ላይ መናፍቅ ቦታ እንደሌለው ሊያውቅ ይገባል።