Get Mystery Box with random crypto!

#ኅዳር_11_ለእግዚአብሔር_በሥጋ_አያቱ_ለእመቤታችን_እናቷ_የሆነችው_የብጽዕት_ሐና_ዕረፍቷ_ነው:: | ዝክረ ብሒለ አበው

#ኅዳር_11_ለእግዚአብሔር_በሥጋ_አያቱ_ለእመቤታችን_እናቷ_የሆነችው_የብጽዕት_ሐና_ዕረፍቷ_ነው::

"ሐና" ማለት በእብራይስጥኛው "የእግዚአብሔር ስጦታ" እንደ ማለት ነው:: "ሐና: ዮሐና: ሐናንያ" የሚሉ የዕብራይስጥ ስሞች ትርጉማቸው ተወራራሽ ነው::

ቅድስት ሐና ትውልዷ: ነገዷ ከላይ ከቅዱስ አብርሃም: ከታች ደግሞ ከነገደ ካህናት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- *አብርሃም ይስሐቅን: ይስሐቅ ያዕቆብን: ያዕቆብ ደግሞ ሌዊንና 11 ወንድሞቹን ይወልዳል:: *ሌዊ ቀዓትን: ቀዓት እንበረምን: እንበረም አሮን ካህኑን ይወልዳሉ:: *ቅዱስ አሮን አልዓዛርን: አልዓዛር ፊንሐስን እያለ ትውልዱ እስከ ቴክታና ጰጥሪቃ ይወርዳል:: ቴክታና ጰጥሪቃም ልጅ በማጣት ኖረው: የእንቦሳዎችን: የጨረቃንና: የፀሐይን ምስጢር በሕልም ተመልክተው ሄኤሜንን ይወልዳሉ::

*ሄኤሜን ዴርዴን: ዴርዴ ቶናሕን: ቶናሕ ሲካርን: ሲካርም ሔርሜላን ይወልዳሉ:: *ሔርሜላም ከክርስቶስ ልደት 90 ዓመታት በፊት ማጣት ("ጣ" ጠብቆ ይነበብ) የሚባል ደግ ሰው ከካህናት ወገን አግብታ በስርዓተ ኦሪት ትኖር ነበር:: እግዚአብሔር ለዚህች ደግ ሴት የተባረኩ 3 ሴቶች ልጆችን ሰጣት:: የመጀመሪያዋን "ማርያም" አለቻት:: ይህቺውም የአረጋዊው ዮሴፍ ሚስትና የቅድስት ሰሎሜ ቡርክት እናት ናት:: ሁለተኛዋን "ሶፍያ" አለቻት:: እርሷም ቅድስት ኤልሳቤጥን (የመጥምቁን እናት) ወልዳለች:: በመጨረሻ የወለዷትን ግን "ሐና" አሏት:: ይህቺውም የፈጣሪ የሥጋ አያቱ: የድንግል ማርያምም እናቷ ትሆን ዘንድ የተመረጠችውና ስም አጠራሯ የከበረው እናት ናት::

ኢያቄምና ሃና ለእግዚአብሔር የታዘዘ በተቀደሰ ጋብቻ ውስጥ በብዙ ዘመናት አብረው ቢኖሩም በነዚያ ጊዜያት ወስጥ አንድ ልጅ እንኳ ስላልነበራቸው እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ እግዚአብሔር ልጅ ይሰጣቸው ዘንድ አጥብቀው ይለምኑት ነበር፡፡

ከእለታት አንድ ቀን ኢያቄምና ሃና እርግቦች ጫጩቶቻቸውን ሲያጫውቱ ተመልክተው “ለነዚኽ ወፎች እንኳ ልጆችን የሰጠህ አምላክ ለእኛስ መች ይሆን ልጅ የምትሰጠን?” ብለው እጅግ አምርረው አለቀሱ፡፡ ከሐዘናቸውም ጽናት የተነሳ እንቅልፍ ያዛቸውና ተኙ፡፡ በተኙ ግዜም ለሁለቱም እግዚአብሔር መልካም ፈቃዱን በህልም ገለጠላቸው፡፡ ኢያቄም በህልሙ ሃና በእቅፍ ውስጥ ከፍሬዎች ሁሉ የምትበልጥ መልካም ጣፋጭ ፍሬ ይዛ ተመለከተ፡፡ ሃና የኢያቄም በትር ለምልማ፣ አብባና አፍርታ ተመለከተች፡፡ ከእንቅልፋቸውም ነቅተው ስለ ህልማቸው ተነጋገሩ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆንላቸው በጸሎት ጠየቁ፡፡ እግዚአብሔር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ ቢሰጣቸው አድጎ እኛን ያገልግለን ይታዘዘን ሳይሉ ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ እንዲሆን እንደሚሰጡት ቃል ገቡ፡፡

ከዚህ በኋላ ነሐሴ 7 ቀን ሃና ፀነሰች፡፡ ሃና በእርጅናዋ ጊዜ መፅነሷ የተመለከቱ ዘመዶቿና ያገሯ ሰዎች ተገርመው እየመጡ ይጠይቋት ነበር፡፡ ከነዚህም ሰዎች መካከል አንዱ ዐይነ ስውር የነበረችው የአርሳባን ልጅ ናት፡፡ የአርሳባን ልጅ ወደ ሃና መጥታ እውነትም ሃና መጽነሷን ለማረጋገጥ ሆዷን ዳሰሰቻት፡፡ በአድናቆትም ሳታስበው ዐይኗን ስትነካ ዐይኗ በራላት፡፡ በሌላ ግዜም የአጎቷ ልጅ በህመም ምክንያት ይሞትና ሃና ትወደው ስለነበር ልታለቅስ ወደአረፈበት ቤት ትሔዳለች፡፡ እንደደረሰችም አስክሬኑ በተቀመጠበት መካከል አልጋ ዙሪያ ስታለቅስ ሳለ ድንገት ጥላዋ ቢያርፍበት የሞተው ሰው ተነስቶ ሃና የአምላክ እናት የምትሆን እመቤታችንን እንደምልድና በዚህም ሃና እጅግ የከበረችና ምስጋና የሚገባት መሆኗን መሰከረ፡፡ ሃና በፀነሰች ግዜ የተደረጉ ብዙ ተአምራትን አይሁድ አይተው ገና በፅንስ ግዜ ይህን ያክል ተአምራት ያደረገ ሲወለድማ ብዙ ነገር ያደርጋል ብለው በምቀኝነት ተነሳስተው ኢያቅምና ሃናን ሊገድሏቸው ተነሱ፡፡ እግዚአብሔር ግን መልአኩን ልኮ ኢያቄምና ሃና ወደ ሊባኖስ ተራራ እንዲሸሹ አደረጋቸው፡፡ በዚያም ሆነው ግንቦት 1 ቀን ከንጋት ኮከብ ይልቅ የምታበራ እጅግ ያማረች የተቀደሰች የምትሆን ልጅን ወለዱ፡፡

ስሟን "ማርያም-የአምላክ ስጦታ" ብለው ሰይመው ለ3 ዓመታት አሳድገዋታል:: የሚገርመው በ3ቱ ዓመታት ውስጥ ቅድስት ሐና ድንግል ማርያምን ከክንዷ አውርዳት አታውቅም ነበር:: አንድ ጊዜም መላእክት ወስደውባት ፍጹም አልቅሳለች:: ሁዋላ ግን መልሰውላታል:: ሌላኛው የሚደንቀው እግዚአብሔር የዓለም ውዱን ስጦታ እመ ብርሃንን ሰጣቸው:: እነርሱም ይሕችን ውድ ስጦታ ሳይሰስቱ ለፈጣሪ መለሱለት:: ቅድስት ሐና ድንግል ወደ ቤተ መቅደስ ከገባች በሁዋላ የእናትነት ፍቅሯ እያገበራት ለ5 ዓመታት እየተመላለሰች ትጐበኛት: ትስማት ነበር:: እመቤታችን 8 ዓመት በሞላት ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ጥሪ ወደ ቅድስት ሐና ደረሰ:: ከክርስቶስ ልደት 8 ዓመታት አስቀድማ ብጽዕት እናት ሐና ኅዳር 11 ቀን ዐረፈች:: ትንሽ ቆይቶም ባለቤቷ ቅዱስ ኢያቄም ተከተላት እኛም ልጆቿ "ብጽዕት ሐና ክብር ይገባሻል!" እያልን እናመስግናት::

አምላከ ብጽዕት ሐና በምልጃዋ ከዘለዓለም እሳት ያድነን!!! አሜን