Get Mystery Box with random crypto!

#ሕዳር_1_ጻድቁ_ንጉሥ_ነአኩቶ_ለአብ_የተሰወረበት_ዕለት_ነው:: ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በዛግዌ ሥር | ዝክረ ብሒለ አበው

#ሕዳር_1_ጻድቁ_ንጉሥ_ነአኩቶ_ለአብ_የተሰወረበት_ዕለት_ነው::

ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ በዛግዌ ሥርወ መንግስት ከነገሡ 11 ነገሥታት 10ኛው ንጉሥ ነው:: እርሱን በ12ኛው መቶ ክ/ዘመን የወለዱት ቅዱሱ ንጉሥ ሐርቤ (ገብረ ማርያም) እና መርኬዛ ናቸው::

ዘመኑ ቅድስና በላስታ ዙሪያ የመላበት በመሆኑ ቅዱስ ሐርቤ ከመመነኑ በፊት ነበር ነአኩቶ ለአብን የወለደው:: እናቱ መርኬዛ እርሱን ልትወልድ ምጥ ተይዛ ሳለ ጀሮዋ ቅዳሴን ይሰማ ነበር:: ቅዳሴው ሲጀመር የጀመራት ምጥ ድርገት ሲወርዱ (ሥጋ ወደሙ ሲሰጥ) ተፈታላትና ልጇን ተገላገለች:: ሕጻኑን አንስታ ስትታቀፈው ዲያቆኑ ማቁረቡን ፈጽሞ "ነአኩቶ" እያለ ሲዞር ሰማችው:: እዚያው ላይም "ነአኩቶ ለአብ" (አብን እናመስግነው) ስትል ስም አወጣችለት::

ወዲያው ግን አባቱ ቅዱስ ሐርቤ መንግስቱን ለቅዱስ ላሊበላ ሰጥቶ በርሃ በመግባቱ ቅዱሱ ሕጻን ወደ አጐቱ ላሊበላ ቤተ መንግስት ውስጥ ገባ::

የቅዱስ ላሊበላ ቤት ደግሞ በቅድስና ያጌጠ ነውና ከርሱና ከሚስቱ (ቅድስት መስቀል ክብራ) ሕጻኑ ነአኩቶ ለአብ ምናኔና ፍቅረ ክርስቶስን ተማረ:: በዘመኑ ብዙ ሊቃውንት ስለ ነበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትን በደንብ አጠና:: ክህነት ተቀብሎ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግልም እድሜው 30 ደረሰ:: በወቅቱ ቅዱስ ላሊበላና ባለቤቱ መስቀል ክብራ ልጃቸው ይትባረክ እያለ ንግሥናቸውን ለቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አወረሱ::

ቅዱሱ ነአኩቶ ለአብም ምን እንደሚሠራ ሲያስብ አንድ ነገር ተገለጠለት:: ቤተ መንግስቱን እንደሚገባ ካደራጀ በኋላ በቤት ውስጥ አንድ ጉድጓድን በቁመቱ ልክ አስቆፈረ:: በውስጡም በ4 አቅጣጫ ጦሮችን ተከለባቸው:: ድንግል ካህን ነበረና ቀን ቀን ሃገር ሲያስተዳድር: ቅዳሴ ሲቀድስ: በጾም ይውላል:: ሌሊት ደግሞ ወዳስቆፈረው ቦታ ገብቶ ያለማቋረጥ እየጸለየ ይሰግዳል:: ወደ ምድር ሲሰግድ በፊቱ ያለው ጦር ይወጋዋል:: ቀና ሲል ደግሞ የጀርባው ይቀበለዋል:: እንዲህ እያለ የፈጣሪውን ሕማማት ይካፈላል:: በተለይ ዐርብ ዐርብ ሲሆን ደሙ: እንባውና ላበቱ ተቀላቅሎ ይፈስ ነበር:: እርሱ መስቀሉን ተሸክሞ ጌታውን ይከተል ዘንድ መርጧልና::
ከተጋድሎው ጐን ለጐን ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ አብያተ ክርስቲያናትንም ያንጽ ነበር:: በተለይ በ1211 ዓ.ም አካባቢ ያነጻት አሸተን ማርያም ልዩ ናት:: እርሷን ካነጸ በኋላ ከቤተ መንግስቱ በደመና ሠረገላ ተጭኖ እየሔደ ያጥናት: ይቀድስባትም ነበር:: ታዲያ አንድ ቀን አጥኖ ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ብዙ ሥውራን ቅዱሳን መቅደሱን ከበው ተመለከተ:: እርሱም "ወገኖቼ! ከወዴት መጣችሁ?" ቢላቸው "መዐዛ እጣንህን አሽተን መጣን" ሲሉ መለሱለት:: በዚህ ምክንያትም እስከ ዛሬ ድረስ "አሽተን (አሸተን) ማርያም" ስትባል ትኖራለች:: ዛሬ ታቦቱ ያለበት ገዳሙም በእርሱ የታነጸ ሲሆን እጅግ ተአምረኛ ቦታ ነው::

ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ የነገሠ በ30 ዓመቱ ነው:: ለ40 ዓመታት በእንዲህ ያለ ቅድስና ኑሮ 70 ዓመት ሞላው:: በዚህ ጊዜም ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ እርሱ ዘንድ መጣ:: ሰላምታንም ሰጠው:: "ወዳጄ ነአኩቶ ለአብ! አንተ ስለ እኔ ፍቅር ለ40 ዓመታት መከራን ተቀብለሃልና ሞት አያገኝህም:: ክፍልህ ከነ ኤልያስ ጋር ነውና:: የሚያከብርህን አከብረዋለሁ:: ደጅህን የሳመውን: ይህ ቢያቅተው በሩቁ ሆኖ በአድናቆት የተመኘህን: መታሰቢያህን ያደረገውን ሁሉ እምርልሃለሁ" አለው:: ቀጥሎም "ይሕች ቤት አንተ ስትደማ እንደኖርክባት እርሷም እስከ ምጽዓት ድረስ ለመታሰቢያህ ስትደማ ትኑር" አለው:: እነሆ ዛሬም ድረስ ከመቅደሱ ጠበል ይንጠበጠባል:: ለዚህም ደግሞ እኛ ኃጥአን ምስክሮች ነን:: ሳይገባን የቅዱሱን ደጅ ተመልክተናልና:: ቅዱስ ነአኩቶ ለአብም የዚህን ዓለም ተጋድሎውን ፈጽሞ ወደ ብሔረ ሕያዋን መላእክት ወስደውታል:: የተሰወረበትን ዕለት ስንክሳር ሕዳር 1 ሲያደርገው አንዳንድ መዛግብት ደግሞ በ3 ነው ይላሉ:: በዙፋኑም ላይ የአጐቱ የላሊበላ ልጅ አፄ ይትባረክ ተተክቷል::

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጻድቁ ንጉሥ ጸሎት ይማረን!!! አሜን