Get Mystery Box with random crypto!

#መልአኩ_ገብርኤል_እና_ወንጌላዊው_ዮሐንስ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በፍጥሞ ደሴት ያለበደሉ ወንጌ | ዝክረ ብሒለ አበው

#መልአኩ_ገብርኤል_እና_ወንጌላዊው_ዮሐንስ

መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በፍጥሞ ደሴት ያለበደሉ ወንጌልን በመስበኩ ብቻ ለታሰረው ለወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በታላቅ ግርማ ተገለጠለት።

የመላእኩን ክብር የሚያውቅ ቅዱስ ዮሐንስም በእግሩ ስር ወድቆ የጸጋ ስግደት ሰገደለት የዚህን ጊዜ የትህትና ባለቤት የሆነው ቅዱስ ገብርኤል ግን <<እኔም አንተም የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነንና አትስገድልኝ>>አለው።

አንዳንድ ተጠራጣሪዎች ታዲያ ለመላእክት ሲገለጡም ሆነ ሳይገለጡ ምንም ዓይነት ስግደት አይገባቸውም በማለት ራእ. 19፥10 ላይ ያለውን (‹‹አትስገድልኝ››) የሚለውን ጥቅስ ይጠቅሳሉ፡፡

በመሠረቱ ይህ ጥቅስ ለመላእክት የጸጋ ስግደት መስግድ እንደሚገባን እንጂ መስገድ እንደማይገባን የሚገልጽ አይደለም፡፡ ወንጌላዊውና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ለመልአኩ ገብርኤል መስገዱ ሳያውቀው ሳይረዳው ያደረገው ድርጊት እንዳልሆነ እንድናምን ማንነቱና ሕይወቱ ያስገነዝበናል፡፡ ምክንያቱም የጥበብ፣ የማስተዋል፣ የዕውቀት ጸጋን የሚያድል መንፈስ ቅዱስ አድሮበት እያለ ሳያውቀው አደረገው ብሎ መናገርና ማመን መንፈስ ቅዱስን እንደ መጽረፍ /መስደብ/ ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ የተቃኘ ሰው የሚያመልከውንና የሚሠራውን ሁሉ የሚያውቅ ነው፡፡ በተለይ ቅዱስ ዮሐንስ አካል ከሕልውና ተገልጾለት ምሥጢረ መለኮትን የተናገረ ታላቅ ሰው ሆኖ ሳለ ትንሿ ጉዳይ ተሰውራው ለመልአኩ ገብርኤል ሳያውቅ ሰግዶ ተግሳጽ ደረሰበት ብሎ ማመን ሞኝነት ብቻ ሳይሆን ክህደትም ጭምር ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ሰላም ማቃለል ነው፡፡ «መንፈስ ቅዱስ የሰደበ ደግሞ ኃጢአቱ አይሠረይለትም፡፡» (ማቴ. 12፥31-32)፡፡

#የመልአኩ_ገብርኤል_አነጋገር_ታዲያ_እንዴት_ይተረጎማል?

መልአኩ ቅዱስ ዮሐንስን አትስገድልኝ ማለቱ ስለ ሁለት ነገር ነው፡፡

#1ኛ_ስለ_ትኀትና
ዲያብሎስ ከሥልጣኑ የተሻረው ከክብሩ የተዋረደው በትዕቢቱ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት ግን ትሕትናን ገንዘብ ያደረጉ በመሆናቸው እንደ ሰይጣን ስገዱልን የሚሉ አይደሉም፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ይከበሩ ዘንድ ፈቃዱ በመሆኑ የእግዚአብሔር ሰዎች እንዲወዷቸውና እንዲያከብሯቸው አድርጓል፡፡ ለዮሐንስ በሰገደለት ጊዜ «አትስገድልኝ» ማለቱ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ከአምልኮተ እግዚአብሔር የሚያወጣ ለጣኦት እንደመስገድ የሚያስቆጥር ሆኖ ሳይሆን መልአኩ ራሱን በዮሐንስ ፊት ዝቅ ከማድረጉ የተነሣ ስለ ትሕትና የተናገረው ነው፡፡ አንድ ሰው ሌላውን ሰው አክብሮ እጅ ቢነሣው /ከመቀመጫው ሲነሳና ሲቀበለው/ éረ አይገባም እንደሚለው ሁሉ ማለት ነው፡፡ ለዚሁም ማረጋገጫ የሚሆነን (ለትሕትና የተናገረ መሆኑን) በምዕራፍ 19 የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በምዕራፍ 21 ላይ መድገሙ ነው፡፡ ለትሕትና የተናገረው መሆኑን ያወቀው ዮሐንስ ለመልአኩ ክብር መስጠት እንዳለበትና መስገድ እንደሚገባው ዐውቆ ድጋሚ ሲገለጥለት በድጋሚ ሰግዶለታል፡፡

#2ኛ_ስለ_ሥልጣነ_ክህነት_ክብር_ሲል

የቤተ ክርስቲያን የአጥቢያ ኮከብ ቅዱስ ጳውሎስ የካህናትን ሥልጣን አስመልክቶ ሲያስተምር #ካህናት ሰውን ሁሉ እንደሚዳኙ አታውቁምን? እናንተ ሰውን ሁሉ የምትዳኙ ከሆናችሁ ይህን ትንሹን ነገር ልትፈርዱ አይገባችሁምን? የዚህንስ ዓለም ዳኝነት ተውትና መላእክትን ስንኳ እንድንገዛ አታውቁምን$ (1ቆሮ 6፥2-3) ብሏል፡፡ ከዚህ ትምህርቱ የምገነዘበው ካህናት በሥልጣናቸው መላእክትን ስንኳ ሳይቀር እንደሚያዙ ነው፡፡

ይህንንም ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት እንረዳለን፡፡ በ344 ዓ.ም. በአንጾኪያ ከተማ የተወለደው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እምነትንና ፍቅርን፣ ትዕግሥትንና ትሕትናን፣ በአንድነት ገመድ አስሮ ሕዝቡን ለ7 ዓመት ወንጌልን ሰብኳል፡፡ በ387 ዓ.ም. በአንጾኪያ ከተማ ፖትርያርክነት ተሾሞ ሳለ አንድ ጉዳይ ይገጥመዋል፡፡ ንጉሡ አርቃድዮስና ንግሥቲቱ አውዶክያስ ልጅ እየወለዱ እየሞተባቸው አላድግ ስላላቸው የዚህን ምክንያት ቢጠይቁ ደግ ሰው ክርስትና ባያነሣላችሁ ይሆናል ስላሏቸው ከዮሐንስ አፈወርቅ የበለጠ ደግ ሰው በዘመናችን አለን? በማለት ሴት ልጅ በወለዱ ጊዜ መጥተህ ክርስትና አንሣልን ብለው ላኩበት እርሱም ጥሪውን አክብሮ ሲሆድ በመንገድ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከተላከ መልአክ ጋር ይገናኛል፡፡ የበቃ ነውና ረቂቁን መልአክ ሊያየው ችሏል፡፡ ዮሐንስም መልአኩን ‹‹ወዴት ትሄዳለህ?›› ብሎ ጠየቀው መልአኩም ሲመልስለት ‹‹አሁን አንተ የምትሄድባትን ብላቴና ነፍሷን ከሥጋዋ ለይተህ አምጣ ብሎኝ የታዘዝኩትን ለመፈጸም ወደዚያ መሄዴ ነው›› ይለዋል፡፡ ዮሐንስም ‹‹ቆየኝ በጥምቀት ሀብተ ውልድና፣ ስመ ክርስትና ከተሰጣት በኋላ የታዘዝከውን ትፈጽማለህ፡፡ እስከዚያው ግን ከዚሁ አትንቀሳቀስ›› ብሎት በሥልጣነ ክህነቱ ገዝቶት ሄደ፡፡ መልአኩም የዮሐንስን ግዝት ጠብቆ ባለበት ቆመ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ልጅቷን ካጠመቃት በኋላ ንግቶት በሌላ መንገድ ተመለሰ፡፡

 የካህናት ሥልጣናቸው የማይናቅ፣ ትእዛዛቸውም ክብር የሚገባው መሆኑን ስለሚያውቅ ያ መልአክ ወደ ላይም ወደታችም ሳይል አሥር ዓመት ከዚያው ሥፍራ ቆሞ ኖረ፡፡ አሥር ዓመት ሲሆናት ለባል ታጨች ያጠመቅካት ብላቴና እነሆ ለአቅመ ሔዋን፣ ባል ልታገባ ነውና መጥተህ ባርከህ ስደዳት ብለው ለዮሐንስ አፈወርቅ ላኩበት፡፡ እርሱም በጥሪው መሠረት ከዛሬ አሥር ዓመት ልጅቱን ሊያጠምቅ ሲሔድ በሄደበት መንገድ መልአኩን ቆሞ አገኘው፡፡ «ምነው ከዚህ ቆመሃል?» አለው፡፡ መልአኩም ሲመልስለት «የካህናት ማዕረጋቸው የከበረ ነውና መች ወዲያ ወዲህ ያሰኛል፡፡ ቃልህን አክብሬ አንተ ቆይ ካልከኝ ወዲያና ወዲህ ብዬ አላውቅም» አለው ቅዱስ ዮሐንስም በዝንጉዕነቱ ራሱን ወቅሶ መልአኩን የታዘዘውን ያደርግ ዘንድ አሰናብቶታል፡፡ ከላይ በተገለጸው ታሪክ ብናይ በፍጥሞ ደሴት መልአኩ ለዮሐንስ ወንጌላዊ አትስገድልኝ ማለቱ ዮሐንስ ካህንም ነውና ሥልጣኑ ሊያከብር እንደሚገባው ለመግለጽ ሽቶ ነው፡፡ በክብር ዮሐንስ ከመልአኩ ይበልጣልና፡፡

ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን የመላኩ ጥበቃው አይለየን!!! አሜን