2022-05-28 10:24:04
የሰው ልጅ ሲያገኘው የሚችለውን ትልቁን ፀጋ ሌሎችን አለመከተል ነው።
ምንጭ ፦ ንቃተ ህሊና ( ኦሾ)
ተርጓሚ ፦ አና ፍራንክ
እኔ «ኑ ተከተሉኝ» ልላችሁ አልችልም። መጀመሪያ ይህንን የተናገሩት የሰው ልጅን ረዳት አልባ አድርገውታል። የሚፈልጉትን ነገር አሟልተውበታል። ሰዎች በራሳቸው ብቻቸውን መሆንን (ለብቻ መቆምን) አይፈልጉም። የራሳቸውን መንገድ የመፍጠር፣ በፈጠሩትም መንገድ
የመጓዝ ወኔ የላቸውም። መመራት ይፈልጋሉ።
የምትመሩ ከሆነ አይኖች እንኳን ቢኖራችሁ ቀስ በቀስ እንደምታጧቸው አታውቁም። በክሪሽና፣ በቡድሀ ወይም በሌላው አያኖች መመልከት ትጀምራላችሁ። የእናንተ አይኖች አስፈላጊነት ያበቃል። እንደውም አይኖቻችሁ ችግር ይፈጥሩባችኋል። አንድ መሪ የሚፈልገው በራሳችሁ አይን መመልከት አቁማችሁ በእሱ አይኖች እንድትመለከቱ ነው፤ የራሳችሁን እግር ትታችሁ በእሱ እግሮች እንድትጓዙ ነው። በራሳችሁ ማመን ትታችሁ በእሱ እንድታምኑ ነው። ይህ ለእኔ ወንጀል ነው። እንደዚያ ካደረግኩ እናንተን አካለ-ጉደሎ፣ ሽባ እያደረግኳችሁና እያጠፋኋችሁ ነው። ይህንንም በመላው አለም ሲደረግ ማስተዋል ትችላላችሁ። መላው የሰው ልጅ በእንደዚህ አይነት ንግግሮችና ይህን በሚናገሩ ሰዎች ጠፍተዋል። እናንተም ለዘላለም መጥፋት ካልፈለጋችሁ በስተቀር እኔን ፈፅሞ ልትከተሉ አይገባም! እኔን ከተከተላችሁ በርግጠኝነት ትጠፋላችሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ‹ኑ እና ከእኔ ተጋሩ> እንጂ <ኑ ተከተሉኝ> ልላችሁ አልችልም፡፡ ደግሞስ እኔን የምትከተሉት እኔ ማን ሆኜ ነው?!
እያንዳንዱ ሰው በራሱ ልዩ ፍጡር በመሆኑ አንድን ሰው መከተል ከጀመራችሁ ወዲያውኑ ማስመሰል እንደምትጀምሩ አስተውሉ። የራሳችሁን ማንነት ታጣላችሁ፤ አስመሳይና ግብዝ ትሆናላችሁ፤ ራሳችሁን መሆን ትታችሁ ሌላ ሰውን ትሆናላችሁ፤ ትከፋፈላላችሁ። ሂንዱ፣ አይሁድ፣ ቡዲስት የሚል ጭምብል ይኖራችኋል። ይህም እናንተና ያ የምትከተሉት ሰው የፈጠራችሁት ጭምብል እንጂ የእናንተ እውነተኛ መልክ አይደለም። የምትጓዙት ከማንነታችሁ በተቃራኒ ስለሆነ ትሰቃያላችሁ። መላው የሰው ልጅም ስቃይ ላይ ነው። ምክንያቱም ሁሉም ልጅ ወላጆቹን፣ ጎረቤቶቹን፣ የትምህርት ቤት ጓደኞቹን፣ አስተማሪዎቹን . . . ለመምሰል ይሞክራል። እነሱም ሊያስገድዱት ይሞክራሉ።
እኔ በልጅነቴ የነበረውን ሁኔታ አስታውሳለሁ። የጄይና እምነት ከሚከተል ቤተሰብ መወለዴ ድንገተኛ አጋጣሚ ነበር። አባቴም እንደ ማንኛውም ሰው ወደ ቤተ-መቅደስ ቢወስደኝም፣ እሱን መምሰል እንደሌለብኝ ዘወትር ይነግረኝ ነበር። እሱ የአያት የቅድመ አያቶቹን መንገድ ተከትሎ ያገኘው ነገር አልነበረም። «የእኔን መንገድ እንድትከተል አልፈልግም። እኔ የተከተልኩት መንገድ ይህ ነው ፤ እኔ ስሰግድ የኖርኩት ለእነኚህ አማልክት ነው ፤ እነኚህን ፀሎቶች ስጸልይ ኖሬአለሁ እያልኩ ላሳይህ እችላለሁ። ለእኔ ግን ምንም የፈየደልኝ ነገር የለም። አንተም እንድታደርገው ላስገድድህ አልችልም። በተቃራኒው አንድ ነገር በውል ካልተሰማህ በስተቀር እንዳታደርገው እመክርሀለሁ።››
እኔም በህይወቴ ማንንም አልተከተልኩም። ይህ እጅግ በጣም ከፍተኛ ጠቀሜታ ሰጥቶኛል። የሰው ልጅ ሊያገኘው የሚችለውን ትልቁን ፀጋ አግኝቻለሁ። ይህም ሌሎችን አለመከተል ነው።
ራሴን ሆኜ ለመኖር ሞክሬአለሁ።
ይህንን ለማድረግ ታድያ ድፍረት ያስፈልጋችኋል፤ ጥሩ እውቀት ያሻችኋል፤ እውነትን በራስ መፈለግ መቻልን ይጠይቃችኋል፤ ትክክለኛ የሆነ ፍለጋ ማካሄድ ይኖርባችኋል።
ያኔ ነው አደጋን መጋፈጥ የሚቻለው። አለበለዚያ በዙሪያችሁ ወደ እነሱ ሊወስዷችሁ ያሰፈሰፉ ብዙዎች አሉ።
የትኛውም ቡዲዝምም ሆነ ሂንዱይዝም ወይም ሌላውም እንድትከተሉት በጥብቅ ስለሚያዝ የእናንተን መመሪያዎች፣ የትክክለኛ መንገድ ፍለጋችሁን ወስዶባችኋል። በመሰረታዊ ደረጃ ህይወታችሁ እንዲኖረው የምትፈልጉትን ትርጉም አሳጥቷችኋል። «እኔ ይህንን ልስጣችሁ ዝግጁ ነኝ። እናንተ ማድረግ ያለባችሁ ያለምንም ጥያቄና መጠራጠር እኔን ማመን ነው። የሚያስፈልገው ነገር በእናንተ በኩል ፍጹም አመኔታ ማሳደር ብቻ ነው» ብሎ ቃል ገብቶላችኋል። አንድ ሰው በራሱ መርምሮ ያላገኘውን ነገር እንዲያምን መጠየቅ ደግሞ የመረዳት ችሎታውን ማሰናከል፣ ተራ አዕምሮ እንዲኖረው ማድረግና ለዘላለም ደደብ ሆኖ እንዲኖር መፍረድ ነው።
297 viewsŻel@lem Ãdineŵ, 07:24