Get Mystery Box with random crypto!

  ሰይድ አቡበክር ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሄዱና እንዲህ አሏቸው «ዑመርን ይቅርታ አድርግልኝ፣ ታረ | የአረብ ገንዳ መስጂድ ወጣቶች

  ሰይድ አቡበክር ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሄዱና እንዲህ አሏቸው
«ዑመርን ይቅርታ አድርግልኝ፣ ታረቀኝ ብለው እንቢ አለኝ ከዚያም
ዑመር ትንሽ ቆይተው ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መስጂድ ሲገቡ አቡበክር አጠገባቸው እንደተቀመጡ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በጣም ተቆጥተው ፊታቸው ቀልቶ አዩዋቸው።

   አቡበክርም ይህንኑ የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ሁኔታ ሲመለከቱ
ያበርዷቸውና ያረጋጓቸው ጀመር፡፡ «ረሱል ሆይ! እባክዎን ይረጋጉ እኔ ነኝ ጥፋተኛ አሉ። ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ “ምን ሆነህ ነው ዑመር እንዴት ለአቡበክር ፊት ትነሳዋለህ?..»

   "ሰዎች ሆይ! ይህን ዲን ዤ ስመጣ ሰው ሁሉ ፊት ሲነሳኝ
የተቀበለኝ አቡበክር ነው፡፡ እውነተኛ ነህ ያለኝ አቡበክር ነው፡፡ ገንዘቡን፣ ነፍሱንና ቤተሰቡን አሳልፎ የሰጠኝ አቡበክር ነው፡፡ እባካችሁ ጓደኛዬን እንዳትነኩት፡፡" ከዚህ ጊዜ ጀምሮ አቡበክርን(ረ.ዐ) ቀና ብሎ ያያቸው ኣልነበረም፡፡

           የመዋደድ ውበት

  በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)ና በአቡበክር(ረ.ዐ) መካከል የነበረው መዋደድ መለኪያ አልነበረውም። አንድ ቀን በነብዩና (ሰ.ዐ.ወ) በእሜቴ ዓኢሻ መካከል የፍቅር ጭቅጭቅ ይጀመራል፡፡ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ «በመካከላችን ማን እንዲፈርድ ትፈልጊያለሽ፡፡ አቡ ኡበይዳ ይፍረድ?›› ዓኢሻም “አቡኡበይዳ መልካም ሰው ቢሆንም ከመጣ እርሶን ነው የሚደግፈው” ይላሉ ‹‹እሺ አባትሽ ይሁን?› እሜቴ ዓኢሻ ይስማማሉ፡፡

  ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አስ-ሲዲቅን አስጠሯቸው። አቡበክር እንደመጡ እሜቴ እንዲህ ይላሉ «አንቱ የአላህ መልዕክተኛ እውነቱን ብቻ
ይንገሩት›› አቡበክርም ተቆጥተው ‹‹እርሳቸው ያለእውነት መች ይናገራሉ” ብለው ዓኢሻን ሊመቷት ተጠጉ፡፡ ረሱልም (ስ.ዐ.ወ)
በመሃላቸው ይገቡና ‹‹አቡበክር ይህን እንድታደርግ አላስጠራንህም፡፡ በቃ ተወው›› ይሏቸዋል፡፡

  አቡበክር ከወጡ በኋላ ለእሜት ዓኢሻ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ
ይሏቸዋል «በእርሱና በአንቺ መካከል እንዴት ገላጋይ እንደሆነኩ አየሽ አይደል» አቡበክር(ረ.ዐ) ቆየት ብለው ተመልሰው ሲገቡ ሁለቱም ሲሳሳቁ አገኙዋቸውና ‹‹ስትፋለሙ እንደጠራችሁኝ በተስማማችሁ ጊዜም አሳትፉኝ» በማለት ቀለዷቸው፡፡ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) «አቡበክር ና ተሳተፍ› አሏቸው፡፡

  ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) መውደድ ከአላህ (ሱ.ወ) የሚገኝ በረከትና ጸጋ
ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ) ባሪያውን ሲወድ ይህን በረከትና ጸጋ ያጎናጽፈዋል፡፡ ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ወደድክ ማለት የአላህን (ሱ.ወ) ሪዝቅና ችሮታ አገኘህ ማለት ነው፡፡ ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ወዳጆች ከሆኑ ሙስሊሞች ጎን መሰለፍም ይጠበቅብናል፡፡

ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በሌሊት ጉዞ ባደረጉበትና ወደሰማይ በመጠቁበት ወቅት የአፍታ ማረፊያ የነበራቸው ቁዱስን ከጥቃት ካልተከላከልን
እንዴት ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) እንወዳለን እንላለን፡፡ ታላቁ አቡበክር ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከእንቅልፋቸው እንዳይነቁ ብለው እባብን የሚያክል ነገር
ሲነድፋቸው ድምጻቸውን ዋጥ ማድረጋቸዉን አይተናል፡፡ እኛ ግን የተቀደሰ የመሰሊም ግዛቶች በጠላት እጅ ሲቆሽሹ ዐይተን እንዳላየ
መስለን እናንቀላፋልን፡፡

  አንድ ቀን አቡበክር(ረ.ዐ) ለረቢዓ ቢን ካዕብ ትንሽ የሚያስከፋ ንግግር ይናገሩትና በመካከላቸው አለመግባባት ይፈጠራል፡፡ አቡበክርም(ረ.ዐ) በሁኔታው ያዝኑና «ረቢዓ ግድ የለም የተናገርኩህን መልሰህ ተናገረኝ” ይሉታል፡፡ ‹‹ረቢዓም መልስማ አልሰጦትም» ይላል፡፡ አቡበክርም «ረቢዓ በዚህ ንግግሬ አላህ ፊት እንድከሰስ ትፈልጋለህ?›› ይሉታል፡፡ ሳይናገር ዝም ይላቸዋል፡፡ አቡበክርም ቆጣ ብለው «ከዚህ ቃሌ ጋር አላህ ፊት እንድቀርብ ትወዳለህ ማለት ነው ወላሂ ለረሱል ሄጄ እነግራቸዋለሁ» ይላሉ፡፡

  የረቢዓ(ረ.ዐ) ወገኖችም ተገርመው «ራሱ የሚያስከፋ ንግግር ተናግሮህ ሲያበቃ እንደገና ለረሱል(ሰ.ዐ.ወ) እናገራለሁ ይላል እንዴ?›› ይላሉ። ሪቢዓም «ለመሆኑ የሰውየውን ማንነት አውቃችኋል? ዝም በሉ አስ-ሲዲቅ እኮ ነው! አሁን ለኔ ወግናችሁ እንዲህ ስትናገሩ እንዳይሰማንና እንዳይቆጣን ደግሞ! ከተቆጣ ለረሱል ሄዶ ይናገራላ ረሱልም እርሱን በማስቆጣታችን ይቆጡናል እርሳቸው ከተቆጡ ደግሞ ለእርሳቸው እና ለአቡበክር ቁጣ ሲል አላህም ስለሚቆጣ ረቢዓን ታስጠፋላችሁ፡፡ አሁን ዝም በሉ፡፡››ይላቸዋል ረቢዓ(ረ.ዐ) በስጋት ከአስ-ሲዲቅ(ረ.ዐ) ኋላ እየተከተለ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ሲደርሱ ነብዩ(ሰ.ዐ.ወ) ፈገግ ብለው "አል ሲዲቅና አንተ ምን ሆናችሁ?" ይላሉ አንድ የሚያስከፋኝን ቃል ተናገሩኝና እርሱን መልሰህ ተናገረኝ ሲሉኝ እኔ ደግሞ አይሆንም አልኳቸው›› አለ ረቢዓ፡፡ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) «ረቢዓ አዎን ልክ ነህ፡፡ ከአቡበክር ጋር መመላለስ የለብህም ይልቁንም አቡበክር ሆይ! አላህ ይማርህ» ብለው» አሉት፡፡

              በስንብቱ ዋዜማ

   ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ስልሣ ሶስተኛ ዓመታቸው ላይ ደርሰዋል፡፡
ሠውነታቸው ላይ የድካም ሁኔታ ይተይባቸው ጀምሯል። አንዲት ሴት ወደ ርሳቸው ዘንድ መጥታ የሆነ ነገር እንዲሰጥዋት ጠይቃቸዋለች፡፡ ከዓመት በኋላ እንድትጠይቃቸው ይነግሯታል፡፡ እርሷም «እኔ ስመለስ ባላገኞትስ?›› ትላለች፡፡ ከመድከማቸው የተነሳ እስከ ቀጣዩ ዓመት ሊቆዩ እንደማይችሉ ገምታለች። «እኔን ካላገኘሽኝ አቡበክር ጋር ሄደሽ ትጠይቂዋለሽ ይሏታል። ይህ የመልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) አባባል ከርሳቸው በኋላ አቡበክር እንደሚተካቸው (ሊተኳቸው እንደሚገባ) አመላካች ነው፡፡

  ከዚህ ክስተት በኋላ ነበር ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የመሰናበቻውን ሐጅ
ያደረጉትና ተከታዩ የቁርዓን አንቀጽ የወረደው

الْيَوْمَ أَكْمَلْتُ لَكُمْ دِينَكُمْ وَأَتْمَمْتُ عَلَيْكُمْ نِعْمَتِي وَرَضِيتُ لَكُمُ الْإِسْلَامَ دِينًا ۚ

"ዛሬ ሃይማኖታችሁን ለናንተ ሞላሁላችሁ፡፡ ጸጋዬንም በናንተ ላይ ፈጸምኩ፡፡ ለእናንተም ኢስላምን ከሃይማኖት በኩል ወደድኩ፡፡"  (ሱረቱል ማኢዳህ- 3)

  ይህ አንቀጽ ሲወርድ ሶሃቦች ሁሉ በደስታ ሲስቁ አስ-ሲዲቅ ብቻ በአንቀጹ ስለ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መሰናበት የሚጠቁም ነገር እንዳለ ስለገባቸው ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡

  በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ላይ ሕመም ይጠናባቸው ጀመር፡፡ ዓኢሻ ቤት ሆነው ታስታምማቸው ዘንድ እንዲፈቅዱላቸው ሚስቶቻቸውን ሁሉ
አስፈቀዱ፡፡ ፈቀዱላቸው፡፡ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት ሲደርሱ ሶሃቦች ሁሉ በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መስጂድ ተሰባስበው ከፍ ባለ ድምፅ ያዝመትሙ ጀመር። ረሱል (ስ.ዐ.ወ) ድምጻቸውን ሰምተው ምን እንደሆኑ ሲጠይቁ በርሳቸውስጋት ገብቷቸው እንደሆነ ተነገራቸው!! ረሱልም (ሰ.ዐ.ወ) "ያሉበት ተሽክማችሁ ውሰዱኝ» አሉ፡፡

  እንደደረሱም ሶሃቦችን እንዲህ አሏቸው «እናንተ ሰዎች ሆይ! የኔ ሁኔታ አስፈርቷችኋልን?» ሶሃቦችም "አዎን አንቱ የአላህ መል
ዕክተኛ» በማለት መለሱላቸው እርሳቸውም እንሚከተለው አሏቸው... «እናንተ ሰዎች ሆይ! የእኔና የእናንተ የቀጠሮ ቦታ ዱኒያ
አይደለችም፡፡ ቀጠሮዋችን ሐውድ ዘንድ ነው፡፡ ከዚሁ ሆኜ እያየሁት ይመስለኛል...

----------ኢንሻአላህ ይቀጥላል-----
የአረብገንዳ መስጂድ ወጣቶች የመረጃ ዘርፍ

http://t.me//@arebgendamesjid