Get Mystery Box with random crypto!

የአቡበክር አስ-ሲዲቅ (ረድየሏሁ ዐንሁ) ታሪክ                     ክፍል ሰባት | የአረብ ገንዳ መስጂድ ወጣቶች

የአቡበክር አስ-ሲዲቅ (ረድየሏሁ ዐንሁ) ታሪክ


                    ክፍል ሰባት

      ከዚያም አቡበክር(ረ.ዐ) ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ሄዱና ይህንኑ ነገሯቸው፡፡ ነብዩም (ሰዐ.ወ) "ጊዜው ሊሆን የሚችለው ከሶስት እስከ ዘጠኝ ዐመት ነው፡፡” በማለት ነገራቸው፡፡ አቡበክርም ወደ ኡመያ ዘንድ ተመለሱ፡፡ ኡመያም እንዲህ አለ “ምነው ተጸጸትክ እንዴ?” አቡበክርም “የለም እኔ የመጣሁት ተጸጽቼ ሳይሆን የተናገርኩትን የጊዜ ገደብ ከፍ ለማድረግ ነው።” አሉት፡፡
ዓመታቶች እየተከታተሉ አለፉ፡፡ ልክ በዘጠነኛው ዓመት እንቅጩ
ላይ ሮሞች ፋርሶችን አሸነፉ፡፡ አቡበክርም ዉርርዳቸውን አሸነፉ፡፡
ከዉርርድ ያገኙትን ገንዘብ ሶደቃ እንዲያወጡት ረሱል (ሰ.ዐ.ወ)
ነገሯቸዉ፡፡

     ከዚህ ታሪክ ሁሉም ሙስሊም ሊማር የሚገባው ነገር አለ፡፡
በተለይ ሴትና ወንድ ወጣቶች ከዚህ መማር ያለባቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከማፈርና ወደ ኃላ ከማለት ይልቅ በሙሉ ልብ ሃይማኖታቸውን ማንጸባረቅ አለባቸው፡፡ እውነትን ከመግለጽ ማፈር የለባቸውም፡፡ መጥፎን ነገር በአግባቡ ከመቃወም ማፈግፈግ አይኖርባቸውም፡፡ አንዳንድ ወጣቶች የአቡበከርን (ረ.ዐ) ሙሉነት ተምሳሌት አድርገው በየኮሌጃቸው ቁርኣን ይዘዉ ከመግባት፤ ሒጃቦቻቸውን ዘውትር ከመልበስ መታቀብ የለባቸውም፡፡

              ስደት ወደ መዲና

     ጊዜው ሙስሊሞች ከመካ ወደ መዲና የሚሰደዱበት ወቅት ነው። አስ-ሲዲቅ ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ ሔዱና እንዲህ አሏቸው...“አንቱ የአላህ መልዕክተኛ! እንድሰደድ ይፍቀዱልኝ፡፡” ረሱልም (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ሲሉ መለሱ፡- “አቡበክር ሆይ! ትንሽ ታገስ፡፡ አላህ አብሮህ የሚሰደድ ጓደኛ ይሰጥሀል፡፡”

  አቡበክርም (ረ.ዐ) በስደት ወቅት የነብዩ ጓደኛ መሆንን አጥብቀዉ ተመኙ፡፡ ሁለት ለመጓጓዣ የሚሆኑ ፈረሶችን ገዙና የመሰደጃቸዉ ቀን እስኪደርስ እየተንከባከቧቸው ጠበቁ። አንድ ቀን ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ አቡበከር ቤት መጡ፡፡ “አቡበክር! አላህ እንድሰደድ ፈቅዶልኛል አሏቸው።”

  አቡበክርም «የአላህ መልዕክተኛ እባክዎን ከርሶ ጋር ሆኜ ልሰደድ» አሏቸው፡፡ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) ፍቃደኛ መሆናቸውን ነገሯቸዉ፡፡ ነብዩም (ሰ.ዐ.ወ) ፍቃደኝነታቸውን ከገለጹላቸው በኋላ አቡበክር (ረ.ዐ) የነበሩበትን ሁኔታ እሜቴ አዒሻ (ረ.ዐ) ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ...“አቡበክርም ያለቀሱትን ያህል ማንም ሰው ደስታ ሲያስለቅሰው አይቼ አላዉቅም፡፡ ጉዞው በጣም አስቸጋሪና የሞት ጉዞ ነዉ፡፡ እንደዚያም ሆኖ የሚጓዙት ከረሱል ጋር መሆኑን ስላወቁ በደስታ ሲቃ ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ ዋሉ።” አቡበክር ለነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) የነበራቸው ፍቅር በእጅጉ የሚያስገርም ነበር፡፡

     ሰይድ አቡበክር (ረ.ዐ) ገንዘባቸዉን ሁሉ ለዚህ ጉዞ አዋሉት፡፡
ለቤተሰባቸው ከአላህና ከረሱሉ (ሰ.ዐ.ወ) በስተቀር የተዉላቸው አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡ ይህ እንግዲህ ለዲን የሚከፈል ጣሪያ የነካ መስዋዕትነት ነበር፡፡ የአቡበክር መስዋትነት ይህን ያህል ነበር፡፡
     በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱን መስዋትነት በአሁኑ ሰዓት በፍልስጤም ምድር እያየነዉ ነዉ፡፡ ወጣቶች በሰልፍ ለክብራቸው መስዋዕትነትን እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡ ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር አያዉቁም፡፡ ፍልስጤማዉያን መስዋትነትን የሚከፍሉት እጅግ ደስተኛ ሆነው ነዉ፡፡ እንዲያውም ሰማዕት የሌለበት ቤት ከተገኘ ቤተሠቦቹ በሁኔታዉ እስከማፈር ይደርሳሉ፡፡

    አስ-ሲዲቅና ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ስደት ወጥተዋል፡፡
“ጋሩ ሠዉር” (የሠዉር ዋሻ) ደርሰዋል፡፡ እንደሚታቀዉ ስደቱ
የሚካሄደዉ በድብቅ ነዉ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ዋሻዉ ለመግባት ሲፈልጉ አቡበክር አስ-ሲዲቅ በቅድሚያ የዋሻዉን ደህንነት ማጣራት ይኖርብኛል ብለዉ ቀድመዉ ገቡና ሁሉንም ነገር አጣሩ፡፡ ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ) ሊጎዳ የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ካጣሩ በኃላ ተመልሰዉ ከመዉጣታቸው በፊት በላያቸዉ ላይ ጣል ያደረጉትን ኩታ እየቀደዱ የዋሻዉን ሽንቁሮች ሸፈኑበት፡፡ ከዚህ በኋላ ነዉ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ወደ ዋሻው ዘልቀዉ የገቡት፡፡ የአቡበክር ኩታ መቀደድን ሲመለከቱ ለምን እንዲህ እንዳደረጉ ጠየቋቸው፡፡ አስ-ሲዲቅም “እርሶን አንዳች ነገር እንዳይጎዳብኝ ፈርቼ ነው፡፡” አሏቸው፡፡ ትንሽ እንደቆዩ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በአቡበክር እግር ላይ ጋደም ብለው እንቅልፍ ይዟቸው ሄደ፡፡ አቡበክር ትንሽ ሽንቁር ተመለከቱና ረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) የሚጎዳ ነገር ከዚያ ውስጥ እንዳይወጣ ፈርተው በእግርቸው መዳፍ ሸፈነት፡፡ ሽንቁሩ ውስጥ ጊንጥ ነበርና
እግራቸው ተነደፈ፡፡

    አቡበክር እግራቸውን የቱንም ያህል ቢያሳርራቸውም ረሱልን
(ሰ.ዐ.ወ) ላለመቀስቀስ ሲሉ ስቃያቸውን ዋጥ አድርገው ዝም አሉ:: ምንም ድድምፅ ላለማሠማት ጥረት አደረጉ እንባቸው ብቻ ፀጥ ብሎ ቁልቁል ይፈስ ጀምር፡፡ ይሄኔ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ከእንቅልፋቸው ተነሱና የነገሩን ምንነት ጠየቁ፡፡ አቡበክር እንዲህ አሏቸው፡፡ እናትና አባቴ መስዋእት ይሁንልዎ! ጊንጥ ነደፈኝ፡፡ ረሱልም (ሰ.ዐ.ወ) ፈጠን ብለው ሲዳብሷዋቸው ወዲያው በአላህ (ሱ.ወ) ፍቃድ ተፈወሱ፡፡

             የሁለቱ ሁለተኛ

    ብዙዎቻችን የቻልነውን ያህል አቡበክርን (ረ.ዐ) እናወድሳለን፡፡
አላህ (ሱ.ወ) በሱረቱ ተውባ በአንቀጽ 40 ላይ ያወደሳቸውን ያህል ግን ማንም አላወደሳቸውም፡፡

  አቡበክር እንዴት ታድለዋል! አላህ “የሁለት ሁለተኛ” ሲል
አሞግሷቸዋል። አስ-ሲዲቅ በጣም የታደሉ ሰው ነዎት! ኃያሉ ጌታችን በዚያች ቀውጢ ጊዜ የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጓደኛ ሆነው በመጓዝዎ አወድሶዎታል፡፡ በጣም ታድለዋል! አላህ (ሱ.ወ) መረጋጋትን ለርሶ በማድረጉ እንዴት የታደሉ ነዎት!

  ሰይድ ዑመር ቢን አል-ኸጣብ(ረ.ዐ) ይህን አስመልክተው እንዲህ ይላሉ፡-

  "አቡበክር የተሰደዱባት ያቺ ሌሊት ምድር ከሞላችው በረከት ሁሉ
የበለጠች ናት።” እንዲህም ብለዋል፡- “ምነው ያኔ አቡበክር ደረት ላይ ከነበሩት ፀጉሮች አንዲቷን አድርጎኝ በነበረና አብሬያቸው በሆንኩ!”

   የተከበራችሁ ሙስሊሞች! ዓለምን በዲን ቀጥ ያደረጓት እነዚህን
ዕንቁዎች ለመገናኘት በእጅጉ አንጓጓምን? የአቡበክር አስ-ሲዲቅ(ረ.ዐ) ታላቅነት እኮ በዲን ብቻ የሚገታ አይደለም፡፡ ታላቅነታቸው ሰብአዊ የሆነ ታላቅነትም ጭምር ነው።
http://t.me//@arebgendamesjid
        ▻▻ኢንሻአላህ ይቀጥላል◅◅

የአረብገንዳ መስጂድ ወጣቶች የመረጃ ዘርፍ