Get Mystery Box with random crypto!

   የአቡበክር አስ-ሲዲቅ (ረድየሏሁ ዐንሁ) ታሪክ   'ከአቡበክር በስተቀር ማንኛውንም ሰው ወ | የአረብ ገንዳ መስጂድ ወጣቶች

   የአቡበክር አስ-ሲዲቅ (ረድየሏሁ ዐንሁ) ታሪክ

  "ከአቡበክር በስተቀር ማንኛውንም ሰው ወደ እስልምና ስጋብዘው ያላመነታና ያላንገራገረ የለም።..." ረሱል ﷺ
   
                    ክፍል ስድስት

    ለዚህ ነበር በወቅቱ ወደ እስልምና ገብተው የነበሩ አዳዲስ ሰዎች ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ያደረጉትን ይህንን ጉዞ አምኖ ለመቀበል የተሳናቸዉ፡፡ የቁረይሽ ሙሽሪኮችና ባላባቶች ይህንኑ ዜና በሰሙ ጊዜ ረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) ለማሳጣትና ለማዋረድ የማይገኝ እድል ያገኙ ስለመሰላቸው ጮቤ ረገጡ፡፡ ክፍተትን ለስህተት ለመጠቀም ያላቸው አቋም ይገርማል፡፡

    በነገሩ ለመሳለቅና ለማሾፍም ወደ አቡበከር (ረ.ዐ) ዘንድ ሄዱ፡፡
እንደደረሱም ለአል ሲዲቅ እንዲህ አሏቸው፡- "አቡበክር ሆይ! ጓደኛህ የሚዘላብደውን ሰምተሀልን?” ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በኢስራእና ሚዕራጅ ስላደረጉት ጉዞ የተናገሩትን ነገሯቸው፡፡ አቡበከርም(ረ.ዐ) "በእርግጥ እንዲህ ብሏል? አሉ፡፡“አዎ! ብሏል፡፡” አሏቸው፡፡ አቡበከርም (ረ.ዐ) "በእዉነት ይህንን ብሎ ከሆነ እውነትን ተናግሯል።” አሉ፡፡

   ቁረይሾቹም "ይህንን አምነህ ትቀበላለህ?” ሲሉ ደግመው
ጠየቋቸው፡፡ “ከዚህ የበለጠ ነገር ቢናገሩም አምናቸዋለሁ፡፡” ሲሉ
መለሱ..." ወደ እርሳቸው እንሂድ አሉ። ወደ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ
እንደደረሱም ስለ ኢስራእና ሚዕራጅ የተከተለውን ሁሉ በዝርዝር
ነገሯቸው፡፡ አቡበከርም እንዲህ አሉ፡- "እውነት ተናግረዋል! እውነት
ተናግረዋል! እርሶ የአላህ መልክተኛ መሆንዎን እመሰክራለው፡፡”
ረሱልም (ሰ.ዐ.ወ) "አቡበከር ሆይ! አንተ እውነተኛ ነህ፡፡” አሏቸው፡፡

       ከማንም የተሻለ ጉርብትና

  የመካ ከሓዲያን በረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እና በተከታዮቻቸው ላይ
የሚያደርሱት ስቃይና ግፍ በጣም እየበረታ ሲመጣ! ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለአቡበከር ወደ ሐበሻ ይሰደዱ ዘንድ ፈቀዱላቸው፡፡ ከቁረይሽ ጎሳዎች ዉስጥ በጣም የተከበረ ሰው የነበረው ኢብኑ ዱግና ይህንን ይሰማና፤ የሚሻለው የርሱ ጎረቤት ሆነው መኖር ከቻሉ ማንም ሊነካቸዉ እንደማይችል ለአቡበክር ይመክራቸዋል፡፡

    ሰይድ አቡበክር በኢብን ዱግና ምክር ይስማማሉ፡፡ አቡበክር (ረ.ዐ) የዚህ ሰውዬ ጎረቤት ሆነው በመኖር ብዙ ጊዜ ቁርኣን እየቀሩ ያለቅሱ ነበር። እንዲህ ሲያደርጉ ሴቶችና ህፃናት ከበዋቸው ያዳምጡ ስለነበር በጣም ይማረኩና ተፅዕኖ ያድርባቸው ነበር፡፡

     ቁረይሾች በዚህ ሁኔታ ብዙም ስላልተደሰቱ፤ ከዚህ ተግባር
እንዲታቀቡ ይነግሯቸው ዘንድ ኢብን ዱግናን ይልኳቸዋል፡፡ ኢብን
ዱግናም በተላኩት መሰረት አቡበክር በቤታቸው ሆነው እንዲቀሩ
ይነግሯቸዋል። አቡበክርም በመንገድ የሚያልፉ ሰዎች እንዲሰሟቸው በሚል በቤታቸው መስኮት አቅጣጫ ሆነው መቅራት ይጀምራሉ፡፡

     የመካ ቁረይሾች ይኸኛው ሁኔታም ቢሆን ስላልተስማማቸው ጎረቤታቸው ወደሆኑት ሰው (ኢብን ዱግና) ስሞታ ያቀርባሉ፡፡ ኢብን ዱዓናም ቁርአኑን መቅራት እንዲያቆሙ ለአቡበክር ይነግሯቸዋል።
አቡበክር ግን ቁርኣን መቅረቱን ማቆሙ በጭራሽ እንደማይችሉ
ይነግሯቸውና እንዲህ ይላሉ፡- "ወላሂ ሰዎች ቁርኣን እንዲሰሙ
ማድረጌን አላቆምም፡፡ ከፈለክ ጉርብትናህ ይቅርብኝ፡፡ ካንተ የተሻለና የበለጠ ጎረቤት አግኝቻለሁ፡፡” (ቁርኣንን ማለታቸው ነው፡፡)

                    ለቅሶ
      አቡበክር አስ-ሲዲቅ ቁርኣን በሰሙ ቁጥር እንባቸውን
አይቆጣጠሩም ነበር፡፡ በጣም ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ፡፡ በተለይ ሱረቱል ዘልዘላን በቀሩ ቁጥር ማልቀስ የዘውትር ልማዳቸው ነበር፡፡

     ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) በመሞቻቸው ዕለት ታመው ነበርና ሶላት
እንዲያሰግዱ አቡበክርን ያዟቸዋል፡፡ ይሄኔ እሜቴ ዓኢሻ (ረ.ዐ) እንዲህ ይላሉ፡- “አንቱ የአላህ መልእክተኛ! አቡበክር እኮ ለስላሳ ስው ነው። ቁርኣን ሲቀራ እምባውን መቆጣጠር ስለማይችል ሰፉዋን ምን እንደሚል መስማት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ዑመርን ይዘዟቸው...”

    በአንድ ወቅት ከየመን የመጣ ልዑክ ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘንድ
ይመጣና ለእስልምና ቃል ኪዳን (ሙባየዓ) ይገባል፡፡ ልዑኩ ቁርኣን
ኢስማም ያለቅሳል፡፡ ይሄኔ አቡበክር እንዲህ ይላሉ..“ቀልቦቻችን
ሳይደርቁ በፊት እኛም እንዲህ ነበርን፡፡” ወዲያዉም ማልቀስ ይጀምራሉ፡፡

       እስኪ የታላቁን አቡበክር (ረ.ዐ) ሁኔታ ከራሳችን ሁኔታ ጋር
እናነፃፅረው፡፡ ለመሆኑ እኛ አላህን ፈርተን፣ ቁርኣን ሰምተን
ያለቀስነበትን ጊዜ እናስታውሳለን? ለምን ይሆን ቀልባችን እንዲህ
የደረቀው? ለምንስ ይሆን ከዓይናችን እንባ የጠፋው? መጠያየቅ አለብን!

      ስባት ባህሮችን የፈጠረው ኃያሉ አላህ (ሱ.ወ) እርሱን በመፍራት የሚወርድ እንባን ከእኛ መመልከት ይወዳል፡፡ ነገር ግን የእኛ ዐይን ይህን ከማድረግ ሰስቷል፡፡

          በአላህ ቃል ኪዳን ላይ የነበራቸው ፍጹም እምነት

ፋርሶች ሮሞችን በጦርነት ባሸነፉ ጊዜ፤ አላህ(ሱ.ወ)
የሚከተሉትን የቁርኣን አንቀጾች አወረደ....

{ الۤمۤ (1) غُلِبَتِ ٱلرُّومُ (2) فِیۤ أَدۡنَى ٱلۡأَرۡضِ وَهُم مِّنۢ بَعۡدِ غَلَبِهِمۡ سَیَغۡلِبُونَ (3) فِی بِضۡعِ سِنِینَۗ لِلَّهِ ٱلۡأَمۡرُ مِن قَبۡلُ وَمِنۢ بَعۡدُۚ وَیَوۡمَىِٕذࣲ یَفۡرَحُ ٱلۡمُؤۡمِنُونَ (4) بِنَصۡرِ ٱللَّهِۚ یَنصُرُ مَن یَشَاۤءُۖ وَهُوَ ٱلۡعَزِیزُ ٱلرَّحِیمُ (5) }    الروم: ١-٥

አሊፍ ላም፣ ሚም፡፡ ሩም ተሸነፈች። በጣም ቅርብ በኾነችው ምድር፡፡ እነርሱም ከመሸነፋቸው በኋላ በእርግጥ ያሸንፋሉ። በጥቂት ዐመታት ዉስጥ (ያሽንፋሉ) ትእዛዙም በፊትም በኃላም የአላህ ነዉ። በዚያ ቀንም ምእመናን ይደሰታሉ፡፡ በአላህ እርዳታ (ይደሰታሉ) የሚሻውን ሰው ይረዳል እርሱም አሸናፊው አዛኙ ነው፡፡ (አል-ሩም 1-5)

     እነዚህ አናቅጽ ከወረዱ በኋላ አቡበክር አስ-ሲዲቅ በቁረይሽ
ወደ ሙሽሪኮች መሰብሠቢያ እየሄዱ "ሮሞች እንደሚያሸንፏቸው አርግጠኛ ነኝ፡፡” ማለት ጀመሩ፡፡ አቡበክር እንዲህ እርግጠኛ የሆኑት ከላይ የተገለጸዉን የአላህ (ሱ.ወ) ቃል ኪዳን መሠረት አድርገው ነዉ። ኡመያ ኢብን ኸለፍ ይህንን ሲሰማ “እስኪ እዉነተኛ ከሆንክ እንወራረድ” አላቸው፡፡ አቡበክርም ተስማሙ። ኡመያም “መቼ ነው ድል የሚያደርጉት” ሲል አቡበክርን ጠየቃቸው፡፡ እርሳቸውም “ከሶስት ዓመታት በኋላ” አሉት።

   ▻▻ኢንሻአላህ ይቀጥላል◅◅
http://t.me//@arebgendamesjid

  
የአረብገንዳ መስጂድ ወጣቶች የመረጃ ዘርፍ