Get Mystery Box with random crypto!

የአቡበክር አስ-ሲዲቅ (ረድየሏሁ ዐንሁ) ታሪክ   'የኡማው ኢማን በአንድ መዳፍ፤ የአቡበክር ኢማ | የአረብ ገንዳ መስጂድ ወጣቶች

የአቡበክር አስ-ሲዲቅ (ረድየሏሁ ዐንሁ) ታሪክ

  "የኡማው ኢማን በአንድ መዳፍ፤ የአቡበክር ኢማን ደግሞ በሌላ መዳፍ ሆኖ ቢመዘን የአቡበክር ኢማን ባመዘነ ነበር፡፡” ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ)
        
           ክፍል አንድ

   ምስጋና ለኃያሉ ጌታ አላህ (ሱ.ወ) የተገባ ነው፡፡ እናመሰግነዋለን፡፡ እገዛውንም እንሻለን፡፡ ምህረቱን እንጠይቃለን፡፡ ቀጥተኛውን ጎዳና እንዲመራንም እንማጸነዋለን፡፡ እርሱ ወደ ቀጥተኛው ጎዳና የመራውን የሚያጠመው እንደሌለ ሁሉ እርሱ ያጠመመውንም የሚያቀናው የለም፡፡

   ስለ ታላቁ ኸሊፋ አቡበክር አስ-ሲዲቅ (ረ.ዐ) ማራኪ ታሪክ ከማውጋታችን በፊት አንድ ጥያቄን ፡ዕናስቀድም ?ለመሆኑ የእስልምና ተዓምር ምንድን ነው? እንደሚታወቀው ሁሉ በምድራችን ላይ ተነስተው የነበሩ ነብያት ሁሉ ዳዕዋቸውን ሲያካሂዱ የነበረው በተዓምራት(ሙዕጂዛ) እየታገዙ ነበር፡፡

   ሁሉም ነብያት ይዘው የተነሱትን ዳዕዋ ያግዝ ዘንድ ያሳዩ የነበርው ተዓምር በዘመኑ በነበሩ ሕዝቦች አቅም በተግባር ሊውል የማይችልና ከሰብዓዊ ፍጡር ችሎታ በላይ የሆነ ነገር ነበር፡፡ በዓረብኛ “ኻሪቁን ሊልዓዳ” ይባላል።

የሞተ ሰው ነፍስ ዘርቶ እንዲነሳ ማድረግ ነብዩላህ ዒሳ (ዐ.ሰ) የተሰጣችው ተዓምር ነበር። ነብዩ ዒሳ (ዐ.ሰ) በመዳበስ ብቻ ዓይነ ስውርን ያበሩ፣ ለምጻምን ይፈውሱ ነበር፡፡ ግዙፉን ቀይ ባህር ለሁለት የሰነጠቀውና ወደ እባብነት ይቀይር የነበረው በትር ደግሞ ለነብዩሏህ ሙሳ (ዐ.ሰ) የተቸረ ተዓምር ነበር።

ለመሆኑ የእስልምና ተዓምርስ ምንድን ነው?

የእስልምና ሃይማኖት ዋነኛ ተዓምር ቁርኣን እንደሆነ ነው ከልጅነታችን ጀምሮ የምናውቀው፡፡ ኧረ ለመሆኑ የቁርኣን ተዓምር ምንድን ነው?

በእርግጥ እጅግ በጣም አስደማሚና መሳጭ የሥነጹሑፍና የአገላለጽ ውበት ቅዱስ ቁርኣን መላበሱ እውነት ነው፡፡ ቁርኣን ሌሉችም በርካታ ዘለዓለማዊ ተዓምራትን በውስጡ አጭቆ ይዟል፡፡ ይኸውም፣ አንድ ሰው ቁርኣንን ለመንገዱ ብርሃን፣ ለሕይወቱ መመሪያ አድርጎ መያዝ ከቻለ በዚህ ዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ ሰዎች ውስጥ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ከቅዱስ ቁርኣን ኅያው ተዓምራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ማንኛውም ተራ ሰው የሕይወት መንገዱን ቁርኣን ካደረገ ከዓለማችን ዕንቁ መሪዎች ውስጥ አንዱ ይሆናል፡፡ ይህ በታላቁ ቁርኣን ካዝና ከተከማቹ ምስጢራት ውስጥ አንዱ ነው... በየትኛውም ጊዜና ቦታ ያለ ሰው ቁርኣንን ለመንገዱ ብርሃን ካደረገ ከታላላቅ ስብዕናዎች አንዱ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

   ይህ ዘለዓለማዊ ተዓምር የተሰጠው የነብያት ሁሉ ማክተሚያና መደምደሚያ ለሆኑት ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ነው፡፡ የርሳቸው ተልዕኮ ደግሞ የትኛውንም ዘመንና ጊዜን የሚያጥለቀልቅ ብርሃን ነው፡፡ የቁርኣን ተዓምር በየትኛውም ዘመንና ቦታ ሕያው ሊሆን የሚችለውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

...እኛ የሰው ልጆች ይህንኑ ህያውና ዘለዓለማዊ ተዓምር መሠረት ከነበሩ ምርጥ መሪዎች ውስጥ አንዱ መሆን የማንችልበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም።

    ተራ ሰው የነበሩት ታላቁ ሶሓቢ ሰዕድ ቢን አቢወቃስ(ረ.ዐ) ከታላላቅ መሪዎች ተርታ ለመሰለፍ ጊዜ ያልወሰደባቸው ቁርኣንን ለሕይወታቸው መመሪያ፣ ለመንገዳቸው ብርሃን በማድረጋቸው ብቻ ነበር፡፡ ሌላ ምስጢር የለውም፡፡ ሶሓባው ተራ ሰው ነበሩ፡፡ የቁርኣንን ተዓምር በቀኝ እጃቸው ሲያነግቡ ግን ታሪክ በክብር መዝገቡ ያሰፈራቸው ታላቅ የጦር መሪ ለመሆን በቁ፡፡ በአል-ቃዲሲያ ዘመቻ ግዙፍ ጦር ሠራዊትን ከጀርባቸው በማስከተል ታላቂቱንና አይበገሬዋን ፋርስ ተቆጣጠሯት፡፡ የጣዖታት መናኸሪያ የነበረችውን ፋርስ ወደ ሰፊ የኢስላም ማሳነት ለወጧት። ተራ ሰው የነበሩት ሰዕድ ቢን አቢ ወቃስ!(ረድየሏሁ ዐንሁ)

   የእስልምና ተዓምር  እጅግ ተራና መሐይም የነበሩትን ሰዎች ከዚያ ከዘቀጠና ከጨለማ ህይወታቸው አውጥቶ ለሰማይና ለምድሩ የከበዱ ታላቅ ሰው እንዲሆኑ አድርጎ በአዲስ መልክ መፍጠር ችሏል፡፡ ከእነኚህ በቁርኣን ተዓምር
ከተራነት ወደ ታላቅ ሰውነት በአዲስ መልክ ከተለወጡት ግለሰቦች ውስጥ አንዱ ዑመር ኢብን አል-ኸጧብ ናቸው፡፡ እኚህን ታላቅ ሰው ታሪክ በክብር ማህደሩ የመጀመሪያ ገጽ አስፍሯቸዋል፡፡ አል-ኸጧብ በቁርኣን ተዓምር አማካኝነት ድንቅ የፖለቲካ ሰው፣ ምርጥ ሃሳቦችን አፍላቂ ጀግና ለመሆን ችለዋል። ሰይዱና ዑመር(ረ.ዐ) በቁርኣን ምስጢር አማካኝነት የኢኮኖሚ ሊቅ፣ ጥበቡ የላቀ የጦር
መሐንዲስ ለመሆን በቅተዋል፡፡

      ዑመር ኢብን አል-ኸጧብ (ረ.ዐ) ከትቢያ መሬት ተነስተው የዐረብ ፔንሱላ (የጀዚረተል ዓርብ) ፣ የግብዕ፣ የሻም፣ የኢራቅና የተቀረውን የሙስሊሙ ዓለም ጠቅልለው ሊገዙና ሊያስተዳድሩ የቻሉት የቁርኣንን ተዓምር መሠረታቸው በማድረጋቸውና የቁርኣንን ተልዕኮ ሊደርሱበት በመቻላቸው ነበር፡፡

     ራስን አሳልፎ የመስጠት፣ የለጋስነት የጽኑ እውነተኝነት አብይ ተምሳሌት ለመሆን የበቁት አቡበከር አስ-ሲዲቅ (ረ.ዐ) ተራ ነጋዴ ነበሩ፡፡ ተራ ነጋዴ፡፡ ከተራነት ወጥተው ለዓለም ሙስሊሞች አብይ ተምሳሌት ለመሆን የቻሉት ታዲያ ቁርኣንን ምርኩዝ በማድረጋቸው እንጂ በሌላ አልነበረም፡፡ረዲየሏሁ ዐንሁ!

    ተዓምረ-ቁርኣን ሰዎችን ለዘለዓለሙ እንዲህ እየለወጠ ይኖራል፡፡ተራና ከቁጥር የማይገቡ ሰዎችን ነጥሎ እያወጣ ፍትሃዊ፣ አዛኝ፣
ስብዓዊነትን የተላበሱ የዓለማችን ድንቅ መሪዎችና ገዢዎች ያደርጋቸዋል። የፍትህ መጓደልን የሚያስወግዱ፣ የሰብዓዊ መብት
ጥሰትን የሚያስቀሩ መሪዎች እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡

   በእርግጥ ስለ አቡበክር አስ-ሲዲቅ ማንነት ሙሉ በሙሉ መግለፅ ይከብዳል፡፡ የትኛው ቃል ይሆን የርሳቸውን ታላቅነት ቁልጭ አድርጎ ሊያስቀምጥ የሚችል? በጣም ይከብዳል...
አቡበክር አስ-ሲዲቅ ተቆጥሮ የማይዘለቅ የሰናይ ምግባር፣ የጀግንነትና ታላቅነት ባለቤት ነበሩ፡፡ የትኛውም ቃል እርሳቸውን የሚገልፅ አይደለም...

           አቡበክር አስ-ሲዲቅ ማን ናቸው?

    ትክክለኛ ስማቸው ዐብደላህ ሊሆን ይበልጥ የሚታወቁት ግን አቡበክር በሚለው ቅጽል ስም ነው፡፡ ወላጅ አባታቸው ደግሞ አቡ ቁሀፋ ይባላሉ፡፡ አቡበክር(ረ.ዐ) አል ዐቲቅ የሚል የማዕረግ ስምም አላቸው በዚህ የማዕረግ ስም የሰየሟቸው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ናቸው፡፡ ነፃ የወጣ ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ በአንድ ወቅት ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ማለታቸው ተነግሯል፡፡ “አላህ ከእሳት ነፃ ያወጣውን ሰው ማየት የፈለገ አቡበክርን ይመልከት፡፡"
በሌላ ዘገባ ደግሞ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ለአቡበክር (ረ.ዐ) እንዲህ ብለዋቸዋል "አንተ አቡበክር ሆይ! አንተ አላህ ከእሳት ነፃ ካወጣቸው ሰዎች ነህ"

   'አል ዓቲቅ' በሚል ይጠሩ የነበረው ከእስልምና በፊት ነው ተብሎ ተነግሯል፡፡ መልካቸውም ሆነ ምግባራቸው ውብ ስለ ነበር በዚህ የማዕረግ ስም ይጠሩ ነበር ተብሎ ይነገራል፡፡ በዓረብኛ ቋንቋ አንድ መጥፎ ምነ-ምግባር ያለው ግለሰብ "ሙዓቲቅ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ያለው ደግሞ “ዓቲቅ” ይባላል፡፡ የአቡበክር (ረ.ዐ) ሥነ-ምግባር ግን ምን ጊዜም ቢሆን “ዓቲቅ" ነበር፡፡ ዕጹብ ድንቅ!

      ➢➢➢➢ይቀጥላል

  ኢንሻ አላህ


http://t.me//@arebgendamesjid
የአረብገንዳ መስጂድ ወጣቶች የመረጃ ዘርፍ