Get Mystery Box with random crypto!

'ናፊባ' ክፍል ~ ዘጠና ~ በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888 'ይሄን ሁሉ ድራማ የፃፉት ግን እነ | የዮቶር ልጅ - አምባዬ ጌታነህ

"ናፊባ"
ክፍል ~ ዘጠና ~
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
"ይሄን ሁሉ ድራማ የፃፉት ግን እነማን ናቸው?"ስትል ራሷን ብትጠይቅም ዳሩ ግን ለእሷ ትልቅ እፎይታን ፈጥሮላታል።ከሁሉም ነገር ገሸሽ ያደረጋት በመሆኑ ትልቅ ደስታን አጎናፅፏታል። ያለውን ነገር ለማጣራት ለወንድሟ በተደጋጋሚ ብትደውልለትም ስልክ ሊያነሳላት ባለመቻሉ በፈገግታ ውስጥ ሆና "ምነው አንተ እንደዚህ ጠፋህ የመጨረሻሽ ነው ተደርሶብሻል ምናምን እያልክ ስታቅራራ አልነበረም እንዴ ምነው ዝም አልክ?"የሚል ስላቅ የበዛበት መልዕክት ብትልክለትም አንድም ምላሽ ባለማግኘቷ የሆነ ሀሳብ ነገር ገብቷታል። ምን አልባት ተንኮል እየሸረበ ይሆን? ወይንም እዚህ ሁሉ ግብግብ እጁ ይኖርበት ይሆን? አዎ ሊኖርበት ይችላል።ያው የኢንስፔክተሩ ደጋፊ አይደል። እኔ ላስገድለው እንደሆነ ገብቶታል ማለት ነው!።ነገር ግን ያልገባኝ የመንግስት ሀይሎች ለምን ባልተጠበቀ መንገድ እንደዛ ሊጠብቁት በድንገት ፈለጉ? ትንሽ ጥያቄ የሚያጭረው እሱ ነው!" አለችና ስልኳን አንስታ ለአንድ ታማኝ የመረጃ ምንጯ ደውላ ስትጠይቅ ሁሉንም ነገር አጫወታት።ራሷን በፈገግታ እየነቀነቀች "በቃ አንድ አረም ነቀልኩ።ከዚህ በኋላ መንግስት ለራሱ ሲል ይከታተለዋል።እናም ወደተቀዛቀዘው ስራዬ ሙሉ ለሙሉ በመዞር አቅሜን ና ሀብቴን በመጠቀም ያለምንም ሰቀቀን መስራት እችላለሁ" በማለት ተንጠራራችና ስልኳን ከፍታ ስትመለከት ሶሻል ሚዲያው በሸዋንግዛው ፎቶ ተጥለቅልቋል። የተፃፈውን የመንግስትን አፈናም ስትመለከት ድንግጥ አለች።በፍፁም መንግስት ራሱ ያስረዋል የሚል ግምት አልነበረባትም። ሁሉም ሰው በስአት በሚባል ደረጃ አጥለቅልቆታል።
**********
"በጣም የሚገርም ነው። ሶሻል ሚዲያ ለካ መሳሪያ ያልታጠቀ ወታደር የሚኖርበት ቦታ ነው። በዚህ ስአት ብቻ ከሁለትመቶ ሺህ ሰው በላይ ተደራሽ ሆኗል። ኢንስፔክተሩን ፕሮፋይል በማድረግ ከወዲሁ "እኔ ከሸዋንግዛው ጎን ነኝ!" የሚል ሀሽታግ እየተጠቀሙ ከጠበቅነው በላይ ነገሩን አግለውታል። በራሪ ወረቀቱም በሚገባ ነው ስራውን የሰራው።አሁን ህዝቡ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሰ ይመስላል። ወትሮም ይሄን መንግስት የታገሱት በኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ከመጠን ያለፈ እምነት ስላላቸው ነው እንጅ መንግስቱ ቋቅ ብሏቸዋል።" "በጣም አሪፍ ታዲያ እኛስ የምንፈልገው ይሄን ስርአት መቀየር አይደል?!"አለና በፈገግታ። " አየህ ወዳጄ ሀገር ዝም ብላ አትመራም በህዝብ ይሁንታና እሺታ እንጅ። ህዝብ የወደደው መሪ ምንም አይሆንም ከማንም እና ከምንም ነፃ ይሆናል። ሸዋንግዛውን ተመልከት ሀብቱ ስልጣኑና ገንዘቡ ሳይሆን ህዝቡ ነው። በህዝቡ ውስጥ ደግሞ ዝም ብሎ አይደለም የገባው። በቀላል ስራ ብቻ።ስራውን አክብሮ በሀቀኝነት ስለሰራ ነው። ለምሳሌ የቱርኩን ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ብንመለከት መፈንቅለ መንግስት ሊካሄድበት ሲል እናቶች ናቸው ታንክ ስር ሆነው ነፍሳቸውን ሳይሰስቱ በመስጠት ነፍሱን ያዳኑት።ከአሜሪካ ባርነትም ህዝቡ ራሱ የሚፈልገውን መሪ በመጠበቅ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ደርሳለች። እኔም የምፈልገው ሀገሬን እንዲህ አይነት የህዝብ ልጅ የሆነ መሪ እንዲመራት ነው። የህዝቡን ደህንነት የሚጠብቅ ችግሩን በሚገባ ተረድቶ ለችግራቸው እውቅና ብቻ ሳይሆን መፍትሔ የሚለግስ መሪ እንዲኖር። የትግሌ ራዕይ ይሄ ነው። እናንተ ገና ልጆች ናችሁ ከእናንተ በታች ያሉት ደግሞ ይበልጥ ልጆች ናቸው። ሀሳባቸው የሰላም እና የምግብ እጦት መሆን የለበትም። ከማንም ጣልቃ ገብነት የተገለለች የማንም ቡችላ ነጭ እንደፈለገ ሀሳብ የማይሰጥባትን ሀገር መገንባት ነው።ለዚህም ነው ትልቅ ዋጋ የምከፍለው።"አለና ትከሻውን መታ መታ አድርጎት የምድሩን አሳንሱር ነክቶ ወደላይ ወደ አፓርትመንቱ የሚያስወጣውን ቁልፍ ተጫነ "ግን እስካሁን እኮ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውን አልጎበኘኸውም" አለ "ገና ነው የምጎበኘው አሁን አይደለም ልጅ። ጊዜው ራሱ ሲደርስ እኔ እሄዳለሁ።አሁን ከራሱና ከልጆቹ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፍ እንተወው።አሁን ከምንም በላይ የሚያስፈልገው እኔን ማወቅ ሳይሆን ልጆቹ ጋር ጊዜ ማሳለፉ ነው" በማለት ስቆ ወደ ላይ ይወጣ ጀመር።
********
መንግስት በሶሻል ሚዲያው በከፈተው አብዮት በጣም ደንግጧል።ሁሉም ነገር ሊቆጣጠረው ከሚችለው በላይ ሆኖበታል።ባሰበው መንገድ ሳይሆን ባልጠበቀበትና ጭራሽ ፈፅሞ ባልገመተው አካሄድ በመሄዱ ጭንቀት የወለደው መግለጫ በመንግሥት ኮምኒኬሽን ክፍል በኩል ተከታዩን መግለጫ ሰጠ።" የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዞቦች ከምንም እና ከማንም በላይ እናንተ ዜጎቻችን አምናችሁን በመረጣችሁን መሠረት ሀገራችንን እያገለገልነበት ባለበት በዚህ ጊዜ ለወራት የቀጠለው የግድያ ተግባር በመቀጠሉ ከምንም በላይ በሀዘን የተቀጣን ብንሆንም ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦች ደግሞ የእነዚህን አሸባሪ ሰዎች እኩይ ተግባር ለማስፈፀም የሚታትሩ እንዳሉ እናውቃለን።ወንጀለኞችንም ለፍትህ ለማቅረብ ተግተን እየሰራንበት ባለበት በዚህ አጣብቂኝ ወቅት አንዳንድ ሰዎች የመንግስትን አደረጃጀት ጥላሸት በመቀባትና ያለስም ስም በመስጠት ላይ ሲሆኑ ለዚህም ማሳያቸው በሬ ወለድ ትርክታቸው በመሆኑ ከሰሞኑም በእናንተው ልጅ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ጉዳይ የተለመደ ውሸታቸውን እና የፈጠራ ታሪካቸውን በዚህ በሶሻልሚዲያ እያስተጋቡ ይገኛሉ። የእኛ የጥበቃ ሀይሎች ከሰሞኑ የዋና ሳጅን አክሊሉ የሺህዋስ ሞት በኋላ በተፈጠረ ስጋት የኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ጉዳይም ስጋት ስለጣለን ከመንግስት ጋር በመነጋገር ልዩ ኮማንዶዎችን ለደህንነቱ በቤቱ አቅራቢያ ለጥበቃ ብናሰማራም ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ተኩስ ተከፍቶ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውንና መላ ቤተሰቡን ይዘው የተሰወሩ ሲሆን ለዚህ እኩይ ተግባራቸውም ራሳቸውን ከሳሽ አድርገው መንግስትን እየወቀሱ ይገኛሉ።ምንም እንኳ ህዝባችን ይህንን መረዳት አይችልም ብለን ባናስብም ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናልና ከዚህ የድግግሞሽ የበሬወለድ ዜና ራሳችሁን በማራቅ የተለመደውን አብሮነታችሁንና ትብብራችሁን እንፈልጋለን። መንግስትም በአሁኑ ስአት ሙሉ ሀይሉን በማሰማራት ከየአካባቢው የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን ታጋቾቹን ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውን ሁለት ልጆቹን እንዲሁም የወንድሙ ልጅ የሆነችውን ሲሐምንና ባለቤቷን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ሲሆን ለዚህም የእናንተን የህዝባችንን እርዳታ እንጠይቃለን!" በማለት ለሁሉም የሀገሪቱ ሚዲያዎች መግለጫ ሰጡ። መግለጫውም በሬዲዮዎችና በቴሌቭዥኖች ተስተጋባ።

@amba88
@amba88