Get Mystery Box with random crypto!

'ናፊባ' ክፍል ~ ሠማንያ ዘጠኝ በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888 'እኔ ምን አውቃለሁ ወንድሜ | የዮቶር ልጅ - አምባዬ ጌታነህ

"ናፊባ"
ክፍል ~ ሠማንያ ዘጠኝ
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
"እኔ ምን አውቃለሁ ወንድሜ እኔ ራሱ ግራ ገብቶኝ የምናገረው ነገር ጠፍቶብኛል"አለ ሸዋንግዛው እጁን አፉ ላይ ጭኖ። "ይሄ ቦታ ግን ይስማዕከ ዴርቶጋዳ ላይ ያስቀመጠው ና የገለፀው የምድር ከተማ ጋር ይመሳሰላል።የምር እዛ ድርሰት ውስጥ በምናብ የገባሁ ያህል ነው የተሰማኝ"አለ ተሕሚድ ዴርቶጋዳ ላይ የተገለፀውን የዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም ምድራዊ ከተማ በምናቡ እያስታወሰ። "በጣም ነው የሚገርመው"ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ ከፊታቸው ሆኖ ሲመራቸው የነበረው ሰው "ደርሰናል" ብሎ ቦታ ሲለቅላቸው በሩ ለሁለት ተከፈተ። "አባዬ " ብሩክታዊትና ኤሌዘር እየተንደረደሩ እላዩ ላይ ተከመሩበት።ሸዋንግዛው ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖት እያለቀሰ ሁለቱንም በየተራ አቅፎ ሳማቸው።ሲሐምም ተሕሚድ ላይ ተሳፍራ የደስታ እንባ ታለቅስ ያዘች። ሁላቸውም ጋር ዝብርቅርቅ ስሜት ውስጥ ሆነው ለረጅም ስአት ከተቃቀፉ በኋላ ተቀመጡ። ሸዋንግዛው ዙሪያ ገባውን ሲያማትር ይህ ቀረው የማይባል ቦታ ነው ያለው።ሁሉም የተሟላለት ክፍል ነው።ልጆቹን እያቀያየረ ከሳመ በኋላ እቅፍ አድርጓቸው ወደ ኋላ ተለጥጦ ተኛ። በልጆቹ እስትንፋስ የአለምን ሁለንተና ግርግር ለመርሳት አሸለበ። የሰላም አየር ወደ ውስጡ እያስገባ እንቅልፍ ወሰደው። ተሕሚድ የሸዋንግዛውን በቅፅበት እንቅልፍ መወሰድ እየተመለከተ በሀዘኔታ "ኡፍ ምን አለ ሁሉም ሰው እንደ አንተ በሀቀኝነት ለገባበት ስራ ቢፋለም!" አለና ወደ ሲሐም በመዞር "እንዴት ወደዚህ አመጧችሁ?"አለ ተሕሚድ "ተወው እሱን በጣም ነበር የፈራሁት።ነገር ግን ልጆቹ ፍፁም እኛ ሰላማዊ ሰዎች ነን።ለእናንተ ደህንነት ስንል ነው። ኢንስፔክተር ና ፍቅረኛሽም ይመጣሉ ብለው።እነ ኤሌዝን ደግሞ መጣወቻ ገዝተው ምናምን ነው ያመጡን። እኔማ እኔን አግተውኝ የነበሩት ሰዎች መልሰው የያዙኝ መስሎኝ ቀጣም ፈርቼ ነበር።ግን ከመጣን በኋላ በቃ ፍፁም ሰላማዊ ነበሩ።እንደመጣን ሌላ ክፍል አሳረፉን። ከዛ የተወሰነ እንቆዬን ወደዚህ አመጡን እና ምንም ሳንፈራ የምንፈልገውን እንድንጠይቅ ነገሩን" አለች። ተሕሚድም በረጅሙ እፎይ ብሎ ተነፈሰ።የነፃነት ትርጉሟ ብዙ ነው ለነፃነት የሚከፈል ዋጋ ትልቅ ቢሆንም ውጤቱ ግን እጅግ ከማርና ከወይን የጣፈጠ ነው። እንደወይን የጣፈጠ የነፃነት አለም ለመፍጠር ብዙዎች መከራ ደርሶባቸዋል ታስረዋል ተገርፈዋል።በመጨረሻ ግን በእነሱ ግርፋት ና ስቃይ ብዙዎች ያለ ሀሳብ እንዲተነፍሱና እንዲኖሩ ምክንያት ሆነዋል።
********
ብዛት ያለው ሀይል ወደ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው መኖሪያ ቤት ቢገባም በቤት ውስጥ ባለመገኘቱ ታላቅ ብስጭት በባለስልጣናት ላይ ታዬ። ንዴታቸውን ማስታገሻ ይሆናቸው ዘንድም የፖሊስ ኮሚሽነሩን ሀላፊን ጨምሮ ኮማንደር በርናባስ ይገዙን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራቸውን አሐዱ አሉ። ጉዳዩ እስከ ጠቅላይ ምኒስቴሩ ጋር በመሄዱ አንዳች ቁጣንና መከፋፈልን በመካከላቸው አስርፆል።ያሳሰባቸው ምን አይነት ሀይልና ቡድን ነው ኢንስፔክተር ሸዋንግዛውን በዛች ቅፅበት ያስመለጡት? እነማን ናቸው? የሚለው ከፍተኛ ጥያቄ ሆኗል። ለዚህም እልባት ለማግኘት አስቸኳይ ስብሰባ በየ ኃላፊነት መስክ ላይ የተቀመጡትን ትላልቅ ባለስልጣና ወደ ቤተመንግስት በስአታት ውስጥ አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥበት በጠቅላይ ምኒስቴር ፅህፈት ቤት ተጠራ። የዋና ሳጅን አክሊሉ የሺህዋስ ሞት ርዕስ በነበረባት ከተማ ሌላ ትርምስ ስለመፈጠሩ የሚያሳይ ችግር እንደተስተዋለ በህዝቡ ላይም ለመረዳት ጊዜ አልፈጀባቸውም።ስለዚህ የህዝቡን ቀልብ ለመሳብ ወይም ሀሳቡን እንዳይሰበስብ ግራ የማጋባት ስራ መስራት እንዳለባቸው የውሸትና የማስተባበያ ሀሳብ መፍጠር እንዳለባቸው አምነዋል።
"አሁን የሚያሳስበው የባለፈው የሶሻል ሚዲያ አቢዮት እንዳይከፈት ነው። ኢንስፔክተር የሆነ ነገር ሆኗል ቢባል ማንም ዝም አይልም።የመንግስታችን ተስፋ ሰጪነት የታየው በእሱ ጠንካራ ስራ ነው። በሸዋንግዛው ትልቅ እምነት አላቸው።ስለዚህ ይሄ ነገር ህዝቡ ጋር ከመዳረሱ በፊት እኛ ቀድመን ሸዋንግዛው እንደታፈነና ህብረተሰቡ አስፈላጊውን እርዳታ እንዲያደርግ መጠየቅ እንዳለባቸው ሀሳብ ያነሳሉ። ሀሳቡ የሚደገፍ በመሆኑ አስቸኳይ ተሰብሳቢ ምኒስቴሮች ሀሳቡን አፅድቀው በፍጥነት ለሚዲያ አካላት መግለጫ መስጠት እንዳለባቸው ከተስማሙ በኋላ ቀጣዩ ደግሞ የሸዋንግዛው አጋቾችን ማወቅና መመርመር። ምክንያቱም እርሱን የፈለጉበት ስለ ፓርቲያችን በርካታ ምስጢሮችን ስለሚያውቅ እኛን ለማጥቃት በቀላሉ እንዲመቻቸው ነው።ስለዚህ ይህ ጉዳይም ጊዜ የሚያስፈልገው ባለመሆኑ ይህንንም በሚገባ ማጣራት ይኖርብናል"በሚል አቅጣጫ በሁለቱ ነጥቦች ላይ ድምፅ ሰጥተው ስብሰባው ተበተነ።
*******
"አሁን ሙሉለሙሉ በሚባል ደረጃ በሁሉም የከተማችን ቦታዎች ማለትም ሰዎች ይሰበሰቡበታል በሚባሉ ሁሉ ፍላየሮችን በትነናል። የአዲስ አበባ መንገዶች በእነዚህ ውብ እና ድንቅ ቢራቢሮ በመሰሉ ወረቀቶች ጎዳናዎቿ ሳይቀሩ አጊጠዋል።"አለ በፈገግታ "በጣም ጥሩ። አሁን ደግሞ የሚቀረው በሶሻል ሚዲያ የኢኔስፔክተር ሸዋንግዛውን መታገት የሚገልፅ መረጃ መውጣት አለበት። የመንግስትን ስራ ከስር ከስሩ የሚነቅፉትን አክቲቢስቶች ታግ አድርጋቸው መረጃውንም ቀድመህ ስጣቸው"አለ ወረቀቱን እየሰጠው "ሁሉንም ነገር እዚህ ላይ ፅፌዋለሁ። ይሄ ተለቆ በከተማዋ ላይ የተበተነው ፍላዬር ጋር ሲዳመር የምንፈልገውን ግብ ይመታልናል። "መንግስት የንፁሀንን ደም ባፈረሱ ሰዎች ላይ ፍትህ ያሰፍናል ወንጀለኞቹንም ለፍርድ ያቀርባል ብለን ስንጠብቅ ነገር ግን በደንታቢስነት ከነገ ዛሬ እያለ እዚህ ደረሰ። ሞቱ ከንፁሀን ዜጎች ባለፈ በታማኝ የህዝብ ልጆች በሆኑ ቅን መርማሪ ፖሊሶች ላይም የደረሰ ሲሆን ለዚህም ከኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ጎን በመሆን ገዳዮችን ለፍርድ ለማቅረብ በከፍተኛ ሀቀኝነት እየሰራ የነበረው ዋና ሳጅን አክሊሉ የሺህዋስም በግፍ መገደሉ የአገዛዙ አቅመቢስነትን የሚገልፅ ሲሆን ይህ አልበቃው ብሎ ደግሞ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ለምን የመንግስትን አካሄድ ትቃወማለህ በሚል አፈና ተፈፅሞበታል። ለዚህም በቤቱ ስራውን እየሰራ በነበረበት በርካታ ቁጥር ያለው የመንግስት ሀይል በመሄድ ከቤቱ አውነው ይዘውት እንደሄዱና እስካሁን የት እንዳደረጉት አይታወቅም። የህዝብን እምባ በማበስ ፋንታ የህዝብን አለኝታ የሆኑ ታማኝ ሰዎችን ማፈን ራሱ ለህዝቡ ያለውን ግዴለሽነት ያሳያልና ህዝቡ ይሄን አፀያፊ የመንግስትን ድርጊት በነቂስ ወጥቶ ሊያወግዝ ይገባል።"የሚል ፅሁፍ ነበር በወረቀት የሰጠው። ይሄን ሀሳብ የያዘ ፅሁፍን ነው ወደ ሶሻልሚዲያ በመለጠፍ የአቢዮት ሀሽታግ የሚጀመረው።ወረቀቷን ወስዶ በሚገባ በወርድ ከፃፈ በኋላ ወደ ስለሰኩ በመላክ ይታወቃሉ ወደሚባሉ የማህበረሰብ አንቂዎች በውስጥ መስመር ተላከላቸው።ከአንድ ፍላዬር ጋር በማድረግ ለሁሉም እንዲዳረስ አደረገ።

@amba88
@amba88