Get Mystery Box with random crypto!

'ናፊባ' ክፍል ~ ሠማንያ ስድስት በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888 ይቅርታ እኔ በዚህ ስሜት ውስ | የዮቶር ልጅ - አምባዬ ጌታነህ

"ናፊባ"
ክፍል ~ ሠማንያ ስድስት
በአምባዬ ጌታነህ @Adwa_1888
ይቅርታ እኔ በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ስብሰባውን መቀጠል አልችልም!" ብሎ ከመቀመጫው ተነስቶ ወጣ። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ከመጠን በላይ እንደተናደደ ፊቱ ላይ በሚገባ ይታያል።በቃላት አልባ ጉርምርምታ ድርጊቱን የደገፉ የስብሰባው ተሳታፊዎች ቢኖሩም ከተለመደው የውስጥ ተቃውሞ ውጪ ማናቸውም ደፍረው ኢንስፔክተሩን ተከትለው የወጡ አልነበሩም። ከራሳቸው ጋር እየተሟገቱ ከራሳቸው ጋር እየተጣሉ የተቀመጡ በርካታ የስራ መኮንኖች ተቀምጠዋል። በባልስልጣናቱ ዐይን ላይ የሚያንዣብበው የቁጣ ደመና ከንሀሴ ሰማይ ይልቃል። ከብዙ የእርስ በእርስ መተያየት በኋላ "ይህን ስብሰባ መታደም የማትፈልጉ ካላችሁ የእኛን ይሁንታ ሳትጠብቁ መውጣት ትችላላችሁ!" አለ አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ሚኒስቴር በዚህን ጊዜ አንዱ እጁን አወጣና የመናገር እድል ከተሰጠው በኋላ " ስብሰባው አንዳች አቅጣጫ አያስቀምጥም። ለውጥም አምጥቶ አያውቅም። እኔ እስከማውቀው ድረስ ምንም አይነት እርምጃ አልወሰድንም።ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ያለው ልክ ነው። በዚህ ጉዳይ ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለው አመኔታ ወርዷል። በመንግሥት ምንም አይነት እምነት የለውም። ቀን በቀን የሞት ዜና እየሰማ ተላምዶት ተስፋ ቆርጧል።ከምንም በላይ ደግሞ የሞት ሞት የሚሆነው ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት ሲያጣ ነው።ስለዚህ እኔም ከይቅርታ ጋር ብወጣ ደስ ይለኛል!"አለና ወጣ። በቀሪው ተሰብሳቢ ላይ ድንጋጤንም ጥርጣሬም እየጫረ እየሄደ መሆኑን ሲያውቁ ሰብሳቢዎቹ ጎን ለጎን ተነጋገሩና ስብሰባውን ያለ አስተያየት ጀመሩ።
*************
"አሁን ጊዜው ደርሷል።ይቺን ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ነበር የምጠብቃት። አንዳንድ ነገሮች እንደገበሬው ወቅት እየተጠበቀ የሚሰሩ ስራዎች አሉ።ያለወቅት የሚዘራ እህልና ያለወቅቱ የሚፈነዳ አብዮት ግቡን አይመታም። ሁሉም ነገር በጊዜው ሲሆን መልካም ነውና አሁን የኛ ጊዜ ነው። ሜዳው ላይ እንዳሻችን የምንጫወትበት ጎል የምናስቆጥርበት ስአት። ሁሉም ሰው የእኛ ደጋፊ ይሆናል። የመንግስትን ስራዎች በሙሉ እናጋልጣለን። እጃችን ላይ ያሉ መረጃዎችን ለህዝብ እናደርሳለን።ስለዚህ ሁላችሁም ከዛሬ ጀምሮ የበረራ ወረቀት በማዘጋጀት በመላው አዲስአበባ ይበተን!!"የሚል መልዕክት አስተላለፈ። በጭብጨባ መልዕክቱን ተቀበሉ።ሁላቸውም ፊት ላይ የቁርጠኝነት መንፈስ ተሞልቷል። መተሳሰብ መደማመጥ መከባበር የተሞላበት ስነ ምግባራቸው ። እያንዳንዳቸው ስለተነገራቸው እና ለተሰጣቸው ዓላማ በቁርጠኝነት እስከመጨረሻው ለመዋደቅ ፅኑ የሆነ ፍላጎት ማሳየታቸው የሚገርም ነው። አብዝሀኛው ሰው አለማው የማይሳካው ወይ ለአላማው ቁርጠኛ አይደለም ወይም አላማው እንደሚሳካ የማያምን ነው። የብዙዎችን ሰዎች የሕይወት ዘመን ግብ ብንመለከት በተለይ ያሳኳቸውን የስኬት ማማዎች ብንመለከት።ለነዛ ስኬቶች ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ብዙዎች ደግሞ ግብ ላይ ስኬት ላይ መድረስን ይመኛሉ። ነገር ግን ለዛ ስኬት የሚያስፈልጉ መስዕዋዕቶችን መክፈል ደግሞ ተራራን የመግፋት ያህል ይቆጥሩታል።
በሀሳብ የኋሊት በትዝታ ሀዲድ ከነፈ።አመታትን ሲያስታውሳቸው ጊዚያቶቹ ሁሉ እንደ ድሮ ዘፈን black &white ሆኖ ተመለከተው። ሰከንዶች በከለር ተቀይረው የድሮውን ትቶ አሁን ያለበትን ዘመን ደግሞ በሙሉ መነፀር አሳየው። ጉዳዩ የዘመን መሸጋገር ብቻ አይደለም። አንዳች ትርጉም እና አንድምታ ይዟል። ጊዜ ታማኝ ነው።እንደ ጥበብ ሸማ ተሸምኖ በስአቱ ይደርሳል ወቅቶች ለዘመናቸው ታማኞች ናቸው።እየተቀባበሉ የሰውን ልጅ ህይወትም በፅሞና ይዘውራሉ። እያንዳንዷ ቀን ትርጉም አላት።ምንም ሳትሰራባት ካለፈች ትነጉዳለች። ጊዜ እነደ ወራጅ ውሃ ነው።ዝም ብሎ ይሄዳል። ነገር ግን እየሄደም አንተ ከሰራህበትና ለሕይወትህ ወሳኝ ግቦችን ለማሳካት የምትጥርበት ከሆነ የባከነ ጊዜ አይኖርህም።"የሚል ፍልስምናውን ከራሱ ለራሱ እያጣቀሰ ከቢሮው ወጥቶ ወደ አውቶብስ ተራ ወደ ሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ለመሄድ ወደ መኪናው ሲገባ ስልኩ ላይ ተደወለ። በፍጥነት አነሳው "አለቃ ዛሬ ጠዋት ላይ ምኒስቴሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናት በሞተው ዋና ሳጅን አክሊሉ የሺህዋስ ላይ ስብሰባ አድርገው ነበር። እናም ስብሰባውን እርባናቢስ የማይጠቅም ብሎ ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ረግጦት ወጥቷል። እናም ከጠቅላይ ምኒስቴሩ በተሰጠ ትዕዛዝ ኢንስፔክተር እንዲታፈን ውሳኔ ተላልፎበታል። ይህ መረጃ የጠላት ቡድናችንም ጋር ሳይደርስ አይቀርም!" አለ። ቶሎ ከመኪናው በፍጥነት ወረደና ተመልሶ ወደቢሮው በመግባት ሁሉንም ነገር በጥሞና ከሰማ በኋላ "በጣም ጥሩ አሁኑኑ ቡድን እስክልክልህ ድረስ ቀጥታ ወደ ኢንስፔክተር ቤት ሄደህ ተከታተል። በዚህ ፍጥነትና በዚህ ስአት ለማፈን አይሞክሩም" የሚል ምክረሀሳብ አቅርቦለት ቀጥታ ወደሌሎች ስልኮች ደወለ
*******
አንዳችም ሰው እንዳይረብሸው ስልኩን አጥፍቶ ለበርካታ ጊዜ የጠረጠራቸውን ሀሳቦች እየነቀሰ በሚገባ በወረቀት እየደረደረ እያስቀመጠ ባለበት ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ደረሰ። "እስካሁን ምንም ነገር አላገኘኽም? "አለ ችኮላና ንዴት በተቀላቀለበት አነጋገር። "እስካሁን ይሄን ነገር አውጥቻለሁ ከዛ ውጪ የማውቀውጰነገር የለም።እስኪ ደግሞ አንተ ተመልከትና አመሳጥር"ብሎ ተሕሚድ ቦታ ለቀቀለት። "ምን አይነት ኤሊቶች እንደተሰበሰቡ አላውቅም። ሁሌም በንፁሀን ደም ላይ ቆመው በሆደሰፊነት ማውራት የማይሰለቻቸው" ብሎ በንዴት ተቀምጦ ላፕቶፑን ጠጋ አደረጎ ማስታወሻውን ገልበጥ ገልበጥ አድርጎ ይመለከት ጀመር። "ኢንስፔክተር ጥሩ ስሜት ላይ ካልሆንክ አረፍ በል"አለ ተሕሚድ ጥሩ ስሜት ላይ እንዳልሆነ በሚገባ በንግግሩና በሁኔታው በመረዳት። ኢንስፔክተር ሸዋንግዛው ለትሕሚድ የሐዘኔታ ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ ዝም ብሎ ተሕሚድ የፃፋቸውን ፊደሎች በአፀንኦት ይመለከታቸዋል።የተፃፉትን ፊደላት ከናፊባ መፅሐፍ ጋር በስሱ ያመሳስል ጀመር። አንዳቹም ሀረግ ከተደረደሩት ፊደሎች የመነጨ ሀሳባዊ አልነበረም።የሁለቱም የሀሳብ ቅኔ ለየቅል ነው።ወደ ጎን ደርድሮ አንዳች ፍች ይሰጣሉ ብሎ ቢያነባቸውም ከተራ አልፋቤት ድምፀት በቀር ወደ አንድ ተስፋ ወደሚያጭር ትርጉም አልተቀየሩለትም። በውስጡ የባለስልጣናቱ ደንዳናነትን እያሰበ በጎን በኩል ደግሞ የብዙ ንፁኅንን ሰዎች ሕይወት የቀጠፈውን ወይም የቀጠፈችውን ለማግኘት ከልቡ ሽቶ ነፍሱ እስክትወጣ በመፈለግ ላይ ነው። ልክ እንደ ፓይታጎረስና ሲግመንድ ሁሉ የብዙሀኑ የፍልስምና ሊቆች ሙከራህን ቀጥል (keep trying) እንደሚሉት የማግኘት ሙከራውን በየቀኑ እየሞከረ ነው።ቢሆንም ከሚደራረቡበት ችግሮች አንፃር እየደከመው በቶሎ እንዲያበቃለት እንደተማፅእኖም ፈጣሪን ይለማመናል።

@amba88