Get Mystery Box with random crypto!

#አድዋ 1888-2014 #126 .....አንድ ቀን ንጉሥ አዋጅ አስነገረ፡፡ ይህ አዋጅ ሀገር ሊ | All Art 2

#አድዋ 1888-2014
#126

.....አንድ ቀን ንጉሥ አዋጅ አስነገረ፡፡ ይህ አዋጅ ሀገር ሊቀማ የመጣ ወራሪ እንደፍልፈል ምድራችንን እየሰረሰረ አድብ ቢባል አልሰማ ያለ ነው የሚል ነበር፡፡
የንጉሡን ኣዋጅ ሀገር ሁሉ ሰማ፡፡ ያኔውኑ የሸዋ ሰው ጥቅምት ሲጋመስ ወረኢሉ ገባ፡፡ ያኔ በኢትዮጵያ ምድር የሆነው የአባቶቻችን ገድል እንዲህ ነው፡፡ ከጠረፍ ሀገር ለሚነሱ አባቶቻችን የደዴሳ ወንዝ ሙላት ስጋት አልነበረም፡፡ ከበርሃ ለሚመጡ አባቶቻችን የጥምና የሀሩር ጉልበት ፈተና አልነበረም፡፡
እባቶቻችን እሾህና አሜኬላን ረግጠው፣ በባዶ እግር ሙሉ ሀገር ሊያስረክቡን መንገድ ዠመሩ፡፡ በአራቱም አቅጣጫ እንዲኽ ሆነ፡፡
የንጉሠ ነገሥታችንን ጥሪ የሰማው ሠራዊት ብዙ ነበር፡፡ ክተት ብሎ የተነሳው ሠራዊት ከጉልበቱ ይልቅ ፈጣሪውን የታመነ ኾነ፡፡ ግቤ ሸለቆን በዱአ ተከዜን በጸሎት የተሻገረው ሠራዊት ለሀገሩ ፍቅር ቁጥሩ ለአብረሃም እንደተገባለት ቃል ኪዳን ከምድር አሸዋ በዝቶ ወደ ስሜን የሚፈስ የሰው ጎርፍ ሆነ፡፡
አባቶቻችን ለንጉሣቸው ቃል ታመኑ፡፡ ብዙቋንቋ፤ በምልክት የሚግባባ፡ በመንፈስ የሚናበብ አንድ ህዝብ ሆነ፡፡ ጠላት እንደ ሰናዖር ሰዎች ኣንዱ ከሌላው ቃሉ ተደበላልቋል ብሎ ሲል በኣንድ ድምጽ በአንድ ቃል ኢትዮጵያ ሲባሉ አቤት ብለው የወጡት ኣባቶቻችን ታላቅ ገድል ይኽ ነው፡፡
በየካቲት ጊዮርጊስ ሌሊት አስራ አንድ ሰዓት የጠላት ጦር ተኩስ ኣሰማ፡፡  የትግራይ ጦር ብጽኑ ተዋጋ፡፡ ይህ ጦርነት በአድዋ ተራሮች ግርጌ ነበር፡፡
ብዙ ተጋድሎ ተደረገ፡፡ አባቶች ለሀገር ክብር ተዋደቁ፡፡ ከወገን ጣር ይልቅ በርታ የሚለውን አዝማሪ መሰንቆና ዜማ የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ወታደር ብዙ ነበር፡፡ ሞት ከአንድ ሽክና ጠላ ቀለለች፡፡ ለሀገር መሞት ትንሳዔ ሆነ፡፡ ከየት ነህ? ያለመባባል ከአንድ ኢትዮጵያ አንድ ኢትዮጵያን ብሎ የተሰለፈው የንጉሠ ነገሥት ጦር ከካሌብ የናግራን ጦርነት በጀመረው የቀደሙት አያቶቹ ክብር ለሀገር መፋለምን አሳየ፡፡
አስቀድሞ በዶጋሊ፣ በጉርዓና በጉንደት እንደሆነው ያለ ለሀገር የተከፈለ መስዋዕትነት መካን ያልሆነች ምድር እንዳለችን አሳመነ፡ይኼ እንደ ኢዛና ጦርነት በድንጋይ የታተመ የድል ታሪክ አልነበረም፡፡ ብራና ፀሐፊዎችም ሞላውን አላስቀሩትም፡፡ ይልቁንስ ሰማይና ምድር ለነጻነት የተከፈለን የጥቁር ህዝብ ተጋድሎ ተመለከቱ።
በአድዋ ተራሮች የኾነው፤ የእኛ ኢትዮጵያውያን ኩራት ብቻ አይደለም፡፡ ጥቁር ሁሉ ይኮራ ዘንድ የተፈጸመ የአያቶቻችን ገድል ነው፡፡ የአድዋ ተራሮች ከዳሞታ እስከ ጉጌ፣ ከዳቲ ወለል እስከ ካራ ማራ፣ ከበላያ እስከ ሙሳ ዓሊ፣ ተራሮቻችን ሁሉ የገድል ሰሌዳ ሆነው የአባቶቻችን ገድል አትመውታል፡፡

የአባቶቻችን ገድል እንዲህ ነው፡፡ ለሀገር በአንድነት ተጋድለዋል፡፡ ሞት በፊታቸው ሸሽቷል፡፡ በመሞት ህይወት ሰጥተውናል፡፡ እንደ ዛሬው ያይደለ፤ አብሮ መብላት ከባድ ሳይሆን፤ አብሮ መሞት ቀላል ሆኖ የድል ቀለም ምሳሌ አድርገውናል፡፡
የአባቶቻችን ገድል በእድል ሳይሆን በሞት የተጻፈ ነው፡፡ የአባቶቻችን ድል ለቂም ሳይሆን ለነጻነት በተከፈለ መስዋዕትነት የተገኘ ነው፡፡

#ምንጭ፦ #ሀገሬን መፅሐፍ
#በተጓዡ_ጋዜጠኛ_ሄኖክ_ስዩም

#የካሌብ_ጽሑፎች
@AllArtLove
@AllArtLove
@AllArtLove