2022-06-11 11:54:15
እግዚአብሔር በመልአኩ አማካኝነት ስራውን መስራቱ፥ እግዚአብሔርና መልአኩ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን ያረጋግጣል። መልአኩ፥ እግዚአብሔር ስራውን የሚሰራበት intermediary ነው። በእርሱ አማካኝነት ይህን ሹመት ለሙሴ ሰጥቷል። በእርሱ አማካኝነት ስራውን ሊሰራ የቻለው ከእርሱ የተለየ አካል በመሆኑ ነው
በመጽሐፍ ቅዱስ፥ "በ" እርሱ አማካኝነት ሰራ ከተባለ፥ ያን አካል በመላክ ሊሰራ ያሰበውን ስራ ሰራ ማለት ነው። ያን ሌላ አካል ልኮ ያቀደውን ስራ ስለሚሰራ፥ "በእርሱ" ሰራ ይባላል። ለምሳሌ፦
"ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች #በእኔ_እጅ ታድን እንደ ሆነ፥"
(መጽሐፈ መሳፍንት 6:36)
በዚህ ስፍራ፥ ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንደተናገረው እስራኤልን በእርሱ እንጅ ያድን እንደሆነ ሲጠይቅ እንመለከታለን። ይህ ማለት፥ በእርሱ አማካኝነት እስራኤልን ያድን እንደሆነ እየጠየቀው ነው። እግዚአብሔር እርሱን ተጠቅሞ እስራኤልን እንደሚያድን ተናግሯልና። ይህ ማለት፥ እርሱን ልኮ እስራኤልን ያድናል ማለት ነው
" እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ #አድን፤ እነሆ፥ #ልኬሃለሁ አለው።"
(መጽሐፈ መሳፍንት 6:14)
ስለዚህ በእርሱ አማካኝነት ያድናል ማለት፥ እርሱን ልኮ ያድናል ማለት ነው። እርሱን በመላክ ሊፈጽም ያሰበውን ተግባር ይፈጽማል ማለት ነው። ይህ "በ" እርሱ አማካኝነት ሰራ ሲባል፥ ላኪና ተላኪ የሆኑ አካላት እንዳሉ የሚያረጋግጥ ነው። የላከውና የተላከው አንድ አካል ሊሆኑ አይችሉምና። ሌላ ምሳሌ፦
" #በሙሴና በአሮን #እጅ ሕዝብህን እንደ በጎች መራሃቸው።"
(መዝሙረ ዳዊት 77:20)
በዚህ ስፍራ፥ ንጉስ ዳዊት እግዚአብሔር ከግብፅ የወጣውን ሕዝቡን በሙሴና በአሮን እጅ እንደመራ ይናገራል። ይህ ማለት፥ እግዚአብሔር አሮንና ሙሴን ልኮ በእነርሱ አማካኝነት ሕዝቡን መራ ማለት ነው። እነርሱን በመላክ ሊፈጽመው ያቀደውን ተግባር አደረገ። አላማውንም በእነርሱ አማካኝነት ፈጸመ። ልኳቸዋልና። ይህ "በ" እርሱ ሰራ ሲባል ላኪና ተላኪ እንዳለ የሚያመለክት ነው። ላኪና ተላኪ ደግሞ አንድ አካል ሊሆኑ ስለማይችሉ፥ "በ" እርሱ ሰራ መባሉ የማንነት ልዩነት እንዳለ ያረጋግጣል
"ከግብጽ ምድር አውጥቼሃለሁ፥ ከባርነት ቤትም ተቤዥቼሃለሁ፤ በፊትህም #ሙሴንና #አሮንን ማርያምንም #ልኬልህ ነበር።"
(ትንቢተ ሚክያስ 6:4)
ስለዚህ እግዚአብሔር በመልአኩ አማካኝነት ሙሴን ገዢና ታዳኒ ማድረጉ፥ እግዚአብሔርና መልአኩ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን ያረጋግጣል
በሚቃጠለው ቁጥቋጦ እግዚአብሔር መልአኩን ወደ ሙሴ ላከ፥ እርሱም በእሳት አምሳል ተገለጠለት። ከዚያም በላከው መልአክ አማካኝነት ገዢና ታዳጊ አድርጎ ሾመው። በመልአኩ አማካኝነት እግዚአብሔር ስራውንና እቅዱን ፈጸመ። መልአኩን ይህን ተግባር እንዲያደርግ (ሙሴን እንዲሾመው) ላከው። ይህ እግዚአብሔርና መልአኩ የተለያዩ አካላት መሆናቸውን ያረጋግጣል።
ይህ እስጢፋኖስ፥ መልአኩ ራሱ ክርስቶስ መሆኑን ለመመስከሩ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።
ምክንያቱም ከላይ እንዳየነው፥ በተመሳሳይ አውድ የክርስቶስንም የመልአኩንም መለኮትነት መስክሯል። አሁን ደግሞ፥ በዚያው በራሱ አውድ፥ መልአኩ ልክ እንደ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር የተለየ አካል መሆኑን እየመሰከረ ነው። ልክ ክርስቶስ ከአብ የተለየ መለኮታዊ አካል መሆኑን እንደመሰከረው ሁሉ፥ መልአኩም ከአብ የተለየ መለኮታዊ አካል መሆኑን መስክሯል። ይህ በማያሻማ ሁኔታ መልአኩ ራሱ ክርስቶስ መሆኑን ያሳያል።
በዚያው በራሱ አውድ፥ መልአኩ ልክ እንደ ክርስቶስ ሁለተኛ መለኮታዊ አካል መሆኑን መመስከሩ፥ ያ ለሙሴ የተገለጠው መልአክ ራሱ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያረጋግጣል። ምክንያቱም፥ በዙሪያው ባለው አውዱ ሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ሌላ ሁለተኛ መለኮታዊ አካል የለምና። የክርስቶስንም የመልአኩንም አምላክነት ከመሰከረ በኋላ፥ መልአኩ ልክ እንደ ኢየሱስ ሁለተኛ መለኮታዊ አካል መሆኑን የመሰከረበት ምክንያት ይህ ነው። መልአኩ ራሱ ጌታ ኢየሱስ ነውና
እግዚአብሔር ሙሴን በልጁ/መልአኩ በኩል የሾመው፥ በእርሱ አማካኝነት ስራውን ስለሚሰራ ነው።
መጽሐፍ ቅዱሳችን እንደሚያስተምረን፥ እግዚአብሔር ሊፈጽመው ያሰበውን ነገር በልጁ አማካኝነት ይሰራል።
ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን #በፈጠረበት #በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤
(ወደ ዕብራውያን 1:2)
በዚህ ስፍራ፥ እግዚአብሔር አለማትን የፈጠረው በልጁ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይህ ማለት ይህን ተግባር (አለምን መፍጠር) አብ የሰራው በልጁ አማካኝነት ነው ማለት ነው። ይህ እግዚአብሔር በልጁ አማካኝነት ስራውን እንደሚሰራ ያሳያል።
እግዚአብሔር #በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር #ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።
(2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 5:19)
በዚሁም ስፍራ እንዲሁ እግዚአብሔር አለሙን በክርስቶስ እንደታረቀ ይናገራል። ይህ ማለት እግዚአብሔር ልጁን ወደ ምድር በመላክ (1ዮሐ 4:10) አለምን ከራሱ ጋር አስታረቀ። የመታረቁን ስራ የሰራው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው። ይህ አብ ያቀደውን ነገር በልጁ አማካኝነት እንደሚሰራ ያረጋግጣል
ስለዚህ ሙሴንም ገዢና ታዳጊ አድርጎ የሾመው በዚሁ አኳሃን ነው። ልጁን/መልአኩን በመላክ ነው። በእርሱ አማካኝነት ገዢና ታዳጊ አድርጎ ሾመው። መለኮት የሆነውን ልጁን ልኮ ቤዛና ዳኛ አድርጎ ሾመው
በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር በተደጋጋሚ በልጁ/መልአኩ አማካኝነት ስራውን ሰርቷል። በእርሱ የይሁዳን ሕዝብ ከአሦራዊያን አድኗል (2 ዜና 32:21-22 ሆሴ 1:7) በእርሱ ኢየሩሳሌምን ሊያጠፋ ነበር (1 ዜና 21:15) ይህ እግዚአብሔር ስራውን በልጁ/መልአኩ እንደሚሰራ ያረጋግጣል። ስለዚህ፥ ሙሴንም ገዢና ታዳጊ አድርጎ የሾመው በዚህ አኳሃን ነው። በልጁ/መልአኩ አማካኝነት
እስጢፋኖስ መልአኩ ልክ እንደ ክርስቶስ፥ ከአብ የተለየ መለኮታዊ አካል መሆኑን መመስከሩ፥ ያ ለሙሴ የተገለጠው መልአክ ራሱ ልጁ ኢየሱስ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ይህም ክርስቶስ/መልአክ በአባቱ ተልኮ ሙሴን ገዢና ታዳጊ አድርጎ የሾመው ጌታ ነው።
ሌላው ሊስተዋል የሚገባው ነገር፥ እስጢፋኖስ በሚሞትበት ሰአት ስለ ክርስቶስ የተናገረው ነገር ነው።
እስጢፋኖስ በሚሞትበት ሰአት፥ ክርስቶስ የወጋሪዎቹን ኀጢአት እንዳይቆጥር ሲማጸነው አይተናል። እስጢፋኖስ በሰማይ ያለውን ክርስቶስን ኀጢአታቸውን አትቁጠር ብሎ ሊለምን የቻለው፥ ክርስቶስ በኀጢአት ጉዳይ ላይ ስልጣን ያለው አምላክ በመሆኑ ነው።
ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን #ኃጢአት #አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ። ሳውልም በእርሱ መገደል ተስማምቶ ነበር።
(የሐዋርያት ሥራ 7:60)
ክርስቶስ ኀጢአትን የመቁጠርና ያለመቁጠር ስልጣን ያለው ኀጢአትን የመማር ስልጣን ስላለው ነው። ኀጢአትን የመማርና የመቁጠር ስልጣን ስላለው በሰማይ ሆኖ ይህ ሊባልለት ቻለ። በኀጢአት ጉዳይ ላይ መለኮታዊ ስልጣን አለውና
ከአብ የተለየ ማንነት የሆነው ክርስቶስ፥ በኀጢአት ጉዳይ ላይ ባለስልጣን መሆኑ በብሉይ ኪዳን ይገለጥ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው
ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናጠና ከአብ የተለየ ማንነት ሆኖ ሳለ፥ በኀጢአት ጉዳይ ላይ ባለስልጣን የሆነው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን እንረዳለን፦
157 viewsedited 08:54