2023-05-11 17:56:30
ኒቃቧን አወለቀች
⁼⁼⁼⁼⁼
↝❪ልብ የሚነካ አስተማሪ ታሪክ❫
➩የሃይስኩል ተማሪ እያለች ነበር ኒቃብ የለበሰችው፡፡ ያውም በአንድ ቀን ደዕዋ፡፡ ቀኑና ጊዜውን ለማስታወስ በትዝታ ወደኋላ ርቃ ሄደች፡፡ ዕለቱ ጁሙዓ ነበር፡፡ ከሶላት በኋላ ስለ ሒጃብ ደዕዋ ያደረገው ኡስታዝ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፤ በተለይ ሴቶች ጆሮ እንዲሰጡት ይወተውታል። ‹ሴት ልጅ ዐውራ ናት፣ ፈፅሞ ፎቷ መታየት የለባትም፣ ፊት ያልተሸፈነ ምን ሊሸፈን!፣ ኒቃብ ግዴታ ነው፤ ሴቶቻችን አላህን ፍሩ፣ ኒቃብ ልበሱ፤ ወላጆችም እንድታለብሱ …› እያለ ይመክራል፡፡
እዚያው እያለች ወሰነች፡፡ ወደ ቤቷ ገባች፡፡ ለወላጆቿ ነገረች፡፡ ኒቃብ መልበስ አለብኝ አለች፡፡ ከብዙ ክርክር በኋላ አሳመነቻቸው፡፡ ትምህርት ብትጨርስም ውጤት አልመጣላትም፡፡ በግል ኮሌጅ አካውንቲንግ ተማረች፡፡ ውጤቷ ጥሩ ነበር፡፡ ሥራ ፈለገች፡፡ ግን በኒቃቧ ምክንያት ተገፋች፡፡ ተቆጨች፣ ተናደደች….
↳ዕድሜዋ ሲገፋ ይታወቃታል፡፡ ከአሥራ ቤት ወጥቶ ሀያ ገብቶ ወደ ሰላሳም ተጠግቷል፡፡ በዚህ በኩል የሥራ ማጣት፣ በወዲያ ከትዳር መዘግየት አስጨነቃት፡፡ ወንድ አትቀርብም፤ ወንዶችም ሊቀርቧት ይፈራሉ፡፡ የለበሠችው በልጅነት በመሆኑ ቀይ ትሁን ጥቁር፤ ቆንጆ ትሁን መልከ ጥፉ በአካል አያውቋትም፡፡ ብቻ በሩቅ ይሸሿታል፡፡ አንድም ኢማናቸውን ንቀው አሊያም ታጠብቃለች፣ አክራሪ ናት ብለው በመፍራት፡፡ ሁለት ፈተና በአንድ ጊዜ ወጥሮ ያዛት፡፡ የለፋችበት ትምህርት ቆጫት፤ የምትመኘው ትዳር ራቃት፡፡ ብዙ ጓደኞቿ ሥራ አገኙ፡፡ በዕድሜ ታናሾቿ ተራ በተራ አገቡ፡፡ ሒጃብን ለሥሙ ብቻ ጣል የሚያደርጉት ጥሩ ትዳር ያዙ፡፡
➺አላህ እሱን ለማይፈሩት ነው እንዴ የሚያደላው! አለች፡፡ ጥሩዎች ሲጎዱ መጥፎዎች ሲጠቀሙ አየች፡፡ ታዘበች፣ አሰበች፡፡ ኢማኗ እየደከመ መጣ፣ በራስ መተማመኗ ቀነሰ፣ ሌሎች የሚያወሩላት ወሬ ሸረሸራት፡፡ ከራሷ ጋር ታገለች፡፡ ኡስታዞችንና ዓሊሞችን ጠየቀች፡፡ ‹ልጅ ሆኜ ስለ ዲን ብዙም ሳላውቅ ነበር በችኮላ የለበስኩት፤ አሁን ማውለቅ እችላለሁ?› አለች፡፡ አውልቂ የሚላት ጠፋ፡፡ ወደ ራሷ ተመለሰች፡፡ ከሁለት ያጣች እንደሆነች ታወቃት፡፡ ኒቃብ ከሥራም ከትዳርም እየከለከላት እንደሆነ ሸይጧን ሹክ አላት፡፡ ደስ እያላት ባለመልበሷ ምክንያት ምንም አጅር እንደማታገኝም ነገራት፡፡
ወረደች፣ ተጠራጠረች፣ ግራ ታጋባች... በጥርጣሬ ዉስጥ ከምዋልል ለምን አላወልቀውም አለች፡፡ ከብዙ ትግል በኋላ አወለቀች፡፡ የመጀመሪያ ሰሞን እርቃኗን የሆነች ያህል ተሰማት፡፡ ግና አንድ አድርጌዋለሁ ብላ ራሷን አበረታታች፡፡ ያዩዋትና የሚያውቋት ደነገጡ፡፡ እሷ ናት ወይስ ሌላ? አሉ፡፡ እሷነቷን ሲያረጋግጡ ብዙ አወሩ፣ ተሳለቁ፡፡ በወሬያቸው ይበልጥ ባሰባት፣ እልህ ተጋባች፡፡ በዚያው ሄደች፡፡ ወደ ቀደመ ቦታዋ አልተመለሠችም፡፡ እሷ የድሮ ኒቃቧን ረሣች፡፡ እነርሱም አውርተው ሲደክሙ ዘነጓት፡፡
☞ኒቃብ የለበስሽ ውድ እህቴ ሆይ!
①ኛ ስለተነገረሽ ሳይሆን አውቀሽና አምነሸበት በዝርዝር አጥንተሸና አገናዝበሽ ልበሺ፣
②ኛ ኒቃብ ስትለብሺ ዒባዳ መሆኑን አስቢ፤ ኒቃብያሽ ቀጥ ያለና የተስተካከለ ይሁን፣
③ኛ በአንድ ልብ ኑሪ፤ ሁለት ሀሳብ መሆን ላውልቅ አላውልቅ ምንዳ የለውም፤
④ኛ ጊዜው ቢረዝምም፣ ቀኑ ቢቆይም አላህ መልካም ባሮቹን ጥሎ አይጥልም፡፡
⑤ኛ ኒቃብ በማውለቅና ፎቶ በመለጠፍ የሚገኝ ትዳር የለም፤
⑥ኛ በአላህ መመካትሽ እንደ ወፍ ይሁን፣ ባዶ ሆዷን ወጥታ ሆዷን ሞልታ ትገባለች፣
⑦ኛ በአላህ አምኛለሁ በይና ቀጥ በይ፣
⑧ኛ ጥሩ መጨረሻ አላህን ለሚፈሩና ለጥንቁቆች ነው፡፡
⑨ኛ አላህ በመልካም ነገር ላይ ፅናት ይስጠን፡፡
በሐቅ ላይ ፀንተው ኖረው በሐቅ ላይ ሆነው አላህን ከሚገናኙት አላህ ያድርገን።
https://t.me/Ethio_Suna_Media
https://t.me/Ethio_Suna_Media
510 viewsAbu Umar Ibnu Sadik, 14:56